ኢየሱስ የአምልክ አጋልገይና ሕዝቡ ስለ አምላክ እንዲያውቅ ማድረግ ተግባሩ ከሆነ(ዮሐንስ 17፡26) እንዴት ራሱ አምላክ ሊሰኝ ይችላል?

 


  1. ዮሐንስ 17፡26 ላይ ምጽሐፍ ቅዱስ “ለእኔ ያለህ ፍቅር በእነርሱ እንዲሆን፤ እኔም በእነርሱ እንዲሆን፤ አንተን እንዲያውቁ አድርጌአለሁ፤ እንዲያውቁህም አደርጋለሁ፡፡” ይላል፡፡ ኢየሱስ “አንተን እንዲያውቁ አድርጌአለሁ” ሲል ነቢይ እንደመሆኑ የርሱ ተግባር ስለ አምላክ ለሕዝቡ ማሳወቅ መሆኑን ገለጸ፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ወደ ፊትም ስለ አምላክ የማሳወቁን ሥራ እንደሚቀጥልበት “እንዲያውቁህም አደርጋለሁ፡፡” ሲል የአምላክ ታማኝ አገልጋይ መሆኑን አረገግጧል፡፡ ታዲያ ኢየሱስ የአምልክ አጋልገይና ሕዝቡ ስለ አምላክ እንዲያውቅ ማድረግ ተግባሩ ከሆነ እንዴት ራሱ አምላክ ሊሰኝ ይችላል?

ኢየሱስ አብን ያሳወቀው ነቢያት ባሳወቁት መንገድ ባለመሆኑ የእርሱ ማንነት፣ ሥልጣንና ኃይል ከነቢያት በእጅጉ የላቀ የሆነውን ያህል ተልዕኮውም ከእነርሱ የላቀ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ እርሱ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ ነው (ዮሐንስ 3፡16)፡፡ ከአብ ጋር ሲኖር ስለነበር አብን አይቶታል (ዮሐንስ 6፡46)፡፡ እርሱ በአብ አብም በእርሱ እንደመኖሩ መጠን እርሱን ያየ ሰው አብን አይቶታል (ዮሐንስ 14፡9)፡፡ ከእርሱ በስተቀር አብን በትክክል የሚያውቅ የለም፤ እርሱ ሊገልጥለት ከወደደው በስተቀር፤ ማለትም ያለ እርሱ በጎ ፈቃድ አብን ማወቅ የሚችል ማንም የለም (ሉቃስ 10፡22)፡፡ የእግዚአብሔር የመጨረሻው መገለጥ የሆነው ኢየሱስ እንደሌሎች ነቢያት ሳይሆን ሁሉን ወራሽ፣ የዓለማት ፈጣሪና የእግዚአብሔር ልጅ ነው፡- “ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፡፡” (ዕብራውያን 1፡1-2)፡፡ ኢየሱስ አብን ያሳወቀበት መንገድ መለኮታዊነቱን የሚያረጋግጥ በመሆኑ ጠያቂው የጠቀሱት ጥቅስ ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጋር ሲገናዘብ እሳቸው የተረዱትን ሳይሆን ተፃራሪውን የሚያረጋግጥ ነው፡፡