ኢየሱስ ሲጠመቅ ከሰማይ የተሰማው ድምጽ የአምላክ ነውን? አምላክ ልጅ አለኝ ይላልን?

 


  1. ማቴዎስ 3፡17 “እነሆ፣ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” የሚል ድምጽ ከሰማይ ተሰማ” ይላል፡፡ እውን ይህ ከሰማይ የተሰማው ድምጽ የአምላክ ነውን? አምላክ ልጅ አለኝ ይላልን?

ነቢያት ያሕዌ እግዚአብሔር ልጁን እንደሚልክ ተንብየዋል፡፡ ሐዋርያት የልጁን መምጣት መስክረዋል፡፡ ልጁ ከመጣ ከ 600 ዓመታት በኋላ መካ ውስጥ የኖረ ስለ ቅዱሳት መጻሕፍት ዕውቀት ያልነበረው ሰው እግዚአብሔር ልጅ እንደሌለው ስለተናገረ ይህ እውነት አይለወጥም፡፡ እኛ ሕያው የሆነውን በባሕርይ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መንፈሳውያን ልጆቹ ያደረገንን አምላከ እስራኤልን እንጂ መካን አምላክ ስለማንከተል እንዲህ ያለውን ክህደት አንቀበልም፡፡

 

አሕመዲን ይቀጥላሉ፡- “ይህ ከሰማይ የተሰማው ድምጽ” የአምላክ ድምጽ አለመሆኑ እንዴት ይታወቃል? ኢየሱስን “የምወደው ልጄ” እያለው? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ኢየሱስ ከዚህ ክስተት በኋላ በዮሐንስ 5፡37 እንዲህ ብሏል፦ የላከኝ አብ ራሱ ስለ እኔ መስክሮአል፤ እናንተ ከቶ ድምጹን አልሰማችሁም፤ መልኩንም አላያችሁም፡፡” ኢየሱስ እንዳለው የአብን (የአባቱን) ድምጽ ካልሰሙ ያ ድምጽ እውን ተሰምቷልን? ከሆነስ የማን ድምጽ ነው? የአሳሳቹ ሳይጣን ቢሆንስ?

የጠያቂው ሙግት እግዚአብሔር ልጅ እንዳለው ሊናገር አይችልም የሚል ሆኖ ሳለ በማቴዎስ 3፡17 ላይ ኢየሱስ ልጁ መሆኑን የተናገረው እግዚአብሔር አለመሆኑን ለማረጋገጥ ኢየሱስ እግዚአብሔርን “አብ” በማለት የጠራበትን ጥቅስ ጠቅሰዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት እርስ በርሱ የሚጠፋፋ ሙግት መጠቀማቸው ለክህደት ትምህርታቸው መጽሐፍ ቅዱስ ምንም ዓይነት ክፍተት ባለመስጠቱ ተስፋ መቁረጣቸውን ያመለክታል፡፡

ኡስታዙ ኢየሱስ ልጁ መሆኑን ከሰማይ የተናገረው እግዚአብሔር ሳይሆን ሰይጣን ሊሆን ይችላል የሚል ዘግናኝ ክህደት “አከብረዋለሁ፣ እውነተኛ ነቢይ ነው” በሚሉት በኢየሱስ ላይ ተናግረዋል፡፡ ኢየሱስ በዚያ ቆሞ ሳለ “ሰይጣን ከሰማይ ሆኖ ‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው› አለው” ሲባል የሚሰሙ ሙስሊሞች ይህንን ስድብ እንዴት ያዩት ይሆን? እንዲህ ዓይነቱን ክህደት በጌታችን ላይ ሊናገር የሚደፍረው ገሃነም መግባቱን ያረጋገጠው ዲያብሎስ ብቻ ነው፡፡ አሕመዲን የአውሬው አፍ በመሆን ይህንን ስድብ በእግዚአብሔርና በአንድያ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ተናግረዋል፡፡ ዳሩ ግን “እግዚአብሔርንም ለመሳደብ ስሙንና ማደሪያውንም በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ” ተብሎ እንደ ተጻፈ ስለምናውቅ አንደነቅም (ራዕይ 13፡6)፡፡ ሰውየው ግን ይህንን ድፍረት በመናገር በእግዚአብሔር የቁጣ እጅ በመውደቃቸው እናዝንላቸዋለን፡፡

ማቴዎስ ከሰማይ ድምፅ መምጣቱን እንጂ አይሁድ ድምፁን ስለመስማታቸው ስላልተናገረ ጠያቂው እንደ ልማዳቸው ያልተጻፈውን እያነበቡ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ በእርግብ አምሳል የመውረዱ ምልክት የተሰጠው ለመጥምቁ ዮሐንስ በመሆኑ (ዮሐንስ 1፡33) ድምፁንም እርሱና ኢየሱስ ብቻ ሰምተው ሊሆን ይችላል፡፡ ኢየሱስ ሲጠመቅ በዚያ የነበሩት አይሁድ ድምፁን ሰምተዋል ቢባል እንኳ በዮሐንስ 5 ላይ ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገሩ የነበሩት ያኔ በቦታው ላይ የነበሩት አይሁድ ስለመሆናቸው እና ሌሎች ስላለመሆናቸው ተሳዳቢው ኡስታዝ ምን ማስረጃ አላቸው?