አምላክ ኢየሱስን የሚያደርገውን ቢያሳየውምና ተዓምር ቢያደርግ ምን ይገርማል? ዮሐንስ 5፡20
-
ዮሐንስ 5፡20 “አብ ወልድን ስለሚወድ የሚያደርገውን ሁሉ ያሳየዋል፤ ትደነቁም ዘንድ ከእነዚህም የሚበልጥ ነገር ያሳየዋል” ይላል፡፡ ታድያ አምላክ ኢየሱስን የሚያደርገውን ቢያሳየውምና ተዓምር ቢያደርግ ምን ይገርማል? አምላክ ከዚህ በላይ ማድረግ አይችልምን? በግልጽ ለኢየሱስ አምላክ “የሚያደርገውን ሁሉ ያሳየዋል” ተብሎ የለምን?
እግዚአብሔር በፍጡራን ተጠቅሞ ተዓምራትን እንደሚያደርግ እንጂ ለፍጡራን ተዓምራትን እንዲያደርጉ እንደሚያሳያቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተነገረም፡፡ በዚህ ቦታ ግን አብ ለኢየሱስ የሚያደርገውን እንደሚያሳየውና ኢየሱስም ያንኑ እንደሚያደርግ ተጽፏል፡፡ ኢየሱስ አብ የሚያደርገውን ሁሉ ማድረግ እንደሚችል አሕመዲን የዘለሉት ቀዳሚ ጥቅስ ይናገራል፡- “ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና” (ቁ.19)፡፡
በዚህ ክፍል ኢየሱስ አብ ሲያደርግ ያየውን እንጂ ከራሱ ምንም ማድረግ እንደማይችል መናገሩ ለአሕመዲን ክርክር እሳቸው ከጠቀሱት ክፍል ይልቅ ጠቃሚ ነበር፡፡ ነገር ግን የጥቅሱ ሁለተኛው ክፍል አብ ማድረግ የሚችለውን ሁሉ ወልድም ማድረግ እንደሚችል ስለሚናገር የኢየሱስን አምላክነት በማረጋገጥ ሐሳባቸውን ያፈርሳል፡፡ ስለዚህ ሊጠቅሱት አልወደዱም፡፡ በሥላሴ ውስጥ የማቀድ የሥራ ድርሻ የአብ ነው፡፡ የጥንት ክርስቲያኖች አብ ልብ መሆኑን፣ ወልድ ቃል መሆኑንና መንፈስ ቅዱስ ደግሞ እስትንፋስ መሆኑን የተናገሩት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ የማቀድ የሥራ ድርሻ የአብ በመሆኑ ወልድ የሚፈፅመው በአብ የታቀደውን ነው፡፡ ስለዚህ አብ ሲሠራ ያየውን እንጂ ከራሱ አንዳች ማድረግ እንደማይችል መናገሩ በሥላሴ አካላት መካከል የሚገኘውን ፍፁም የሆነ መስማማት የሚያመለክት እንጂ የኃይል እጥረት እንዳለበት አያመለክትም፤ ምክንያቱም ሁሉን ቻይ የሆነው አብ የሚያደርገውን ሁሉ ማድረግ እንደሚችል በዚሁ ቦታ ተናግሯልና፡፡ እንደ አብ እርሱም ሁሉን ቻይ ካልሆነ አብ የሚያደርገውን ሁሉ ማድረግ እንዴት ይቻለው ነበር?
ኢየሱስ በዚሁ ምዕራፍ ውስጥ አምላክነቱን የሚያረጋግጡ ብዙ ንግግሮችን ተናግሯል፡-
- “አብ ሙታንን እንደሚያነሣ ሕይወትም እንደሚሰጣቸው፥ እንዲሁ ወልድ ደግሞ ለሚወዳቸው ሕይወትን ይሰጣቸዋል፡፡” (ቁ. 21)፡፡ በገዛ ውዴታው ሕይወትን መስጠት የሚችል ከአምላክ በስተቀር ማንም የለም፡፡
- “ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ፥ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም፡፡” (ቁ. 22)፡፡[7] ኢየሱስ አምላክ ባይሆን ኖሮ ሰዎች አብን በሚያከብሩት በዚያው ሁኔታ መከበር እንደሚገባው ባልተናገረ ነበር፡፡
- “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ፡፡” (ቁ. 25)፡፡ ሕይወት አልባ ሙታን ድምፁን እንዲሰሙ ማድረግ የሚችልና በድምፁ ብቻ ሕይወትን መስጠት የሚችል ከአምላክ በስተቀር ማንም የለም፡፡
- “በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ፡፡” (ቁ. 28-29)፡፡ በመጨረሻው ቀን ሙታንን የማስነሳት ኃይል እና ሥልጣን ያለው ከአምላክ በስተቀር ማንም ሊሆን አይችልም፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ነጥቦች ከግምት ውስጥ ሲገቡ ኢየሱስ ከአብ ተነጥሎ መስራት እንደማይችል መነገሩ በሥላሴ አካላት መካከል የሚገኘውን ፍፁም መስማማት የሚገልፅ እንጂ መለኮትነቱን የሚፃረር አለመሆኑን እንገነዘባለን፡፡