ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ባይሰጠው ይሰቀል ነበርን? ኢየሱስን አሳልፎ መስጠቱ ወንጀል ነውን?
-
ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ መስጠቱ ወንጀል ነውን? ለመሆኑ ማን እንደ ይሁዳ መልካም ሰራ? እርሱ ኢየሱስን አሳልፎ ባይሰጠው ይሰቀል ነበርን? ታድያ በኢየሱስ መሰቀል ክርስትያኖች “ዳንን” ይሉ የለ? ይህ ሁሉ ክርስቲያን “ገነት እንዲገባ” ምክንያት የሆነው የይሁዳ ስራ አይደለምን? ታዲያ ይወገዝ ወይስ ይወደስ? እንደ ክርስትና አስተሳሰብ ሰው ሁሉ የዳነው እና ከገሀነም ነፃ የሆነው በኢየሱስ መሰቀል ነው፡፡ ታዲያ እንደ ክርስትና አስተምህሮት ክርስቲያን ሁሉ በይሁዳ ትከሻ ላይ አይደል ገነት የገባው?
ይህ ጥያቄ በምዕራፍ 1 ቁጥር 2 ላይ ከተነሳው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ የአንድ ሰው ምግባር ጥሩነት የሚለካው በውጤቱ ብቻ ሳይሆን በፍላጎትና በዓላማውም ጭምር ነው፡፡ ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ሲሰጠው ኢየሱስን በማጥፋት ገንዘብ ለማትረፍ እንጂ የኢየሱስን ተልዕኮ ከግብ በማድረስ ዓለምን ለማዳን አልነበረም፡፡ ይሁዳ ለክፋት ያሰበውን እግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ዕቅዱን ለማስፈፀም መጠቀሙ ይሁዳን ከወንጀሉ ነፃ አያደርገውም፡፡ የጠያቂው አመክንዮ ትክክል ከሆነ በየዘመናቱ የእግዚአብሔርን አገልጋዮች በመግደል እና በማስገደል ለተሻለው የሰማዕትነት ክብር እንዲበቁ ምክንያት የሆኑ ክፉ ሰዎች ሁሉ ሊሸለሙ ይገባል ማለት ነው፡፡ ለምን ቢሉ እነዚያ ሰዎች ባይገድሏቸውና ባያስገድሏቸው ኖሮ ለሰማዕትነት ክብር በመብቃት የተሻለውን ሽልማት ባልተቀበሉ ነበር፡፡ አሕመዲን ይህንን የወደቀ ሙግት በመጠቀም የኢየሱስን ስቅለት ለማጣጣል መሞከራቸው በገዛ ሃይማኖታቸው ምን ያህል ተስፋ እንደቆረጡ ያሳያል፡፡