ኢየሱስ አምላክ ከሆነ ኃጢአትን ይቅር የማለት ስልጣን ለምን ተሰጠው?

 


12. ክርስቲያኖች “ኢየሱስ ኃጢአትን ይቅር ማለት ስለሚችል አምላክ ነው” ይላሉ፡፡” በዮሐንስ 20፡23 ላይ “ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ “ኃጢያታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው፡፡” ይላል ታዲያ በዚህኛው ጥቅስ ላይ ደቀመዛሙርቱ ኃጢያትን ይቅር ማለት እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡ ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱንም አምላክ ልንላቸው ይሆን?” አይደለም! ለደቀ መዛሙርቱ ይህን ስልጣን የሰጠው ኢየሱስ ነው! ” ሊሉ ይችላሉ፡፡ ግን ይህንን ጥቅስ አላነበቡምን? “ኢየሱስም ደቀመዛሙርቱ ወዳሉበት ቀርቦ እንዲህ አላቸው ፤ ”ስልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል፤” ይላል (ማቴዎስ 28፡18)፡፡ ስልጣን የራሱ ቢሆን ኖሮ ግን “ስልጣን ተሰጠኝ” ሳይሆን “ስልጣን አለኝ ” ነበር የሚለው ስለዚህ ለኢየሱስ ስልጣን የሰጠው አምላክ መሆኑን እንረዳለን፡፡

ከአምላክ በስተቀር ማንም ኃጢኣትን ይቅር የማለት ሥልጣን እንደሌለው እስልምናም ሆነ ክርስትና ይስማሙበታል፡፡ ስለዚህ አሕመዲን የሐዋርያት ኃጢኣትን ይቅር የማለት ችሎታ ማግኘት ከእምነታቸው ጋር የሚጣረስ በመሆኑ ሐሳቡን ከመቃወም ይልቅ ጥቅሱን በመጠቀም የኢየሱስን አምላክነት መሞገት አልነበረባቸውም፡፡ ከዚህ የምንረዳው አንድ ነገር ቢኖር አሕመዲን የኢየሱስን አምላክነት አጠራጣሪ ለማድረግ ያላቸው ጉጉት በራሳቸው እምነት መሠረት ክህደት የሆነውን ጉዳይ እንዲደግፉ እንዳደረጋቸው ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ጥቅስ ሐዋርያት በገዛ ፍቃዳቸው “ይቅር ብለናችኋል!” በማለት ሰዎችን ከኃጢኣታቸው እንደሚያነፁ እንደሚናገር ማሰብ ስለ ኃጢኣት ይቅርታ ከሚናገረው አጠቃላዩ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ጋር የሚጣጣም ባለመሆኑ የአሕመዲንን ሐሳብ የሚደግፍ አይደለም፡፡ ሐዋርያቱም ለአፍታ እንኳ ቢሆን እንዲህ ያለውን ሥልጣን ሲለማመዱም ሆነ ይህ ሥልጣን እንዳላቸው ሲናገሩ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም፡፡ በዚህ ቦታ ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ኃጢኣትን ይቅር እንዲሉ ሥልጣን እንደሰጣቸው የተነገረው ሐዋርያት እንደ እርሱ የኃጢኣት ይቅርታ ምንጭ መሆን እንደሚችሉ ለማመልከት ሳይሆን የኃጢኣት ይቅርታ ምክንያት የሆነውን የእርሱን ወንጌል በማስተማር ለሰዎች የኃጢኣትን ይቅርታ እንደሚያስገኙ ለማመልከት ነው (ሉቃስ 24፡45-48)፡፡ ጌታችን ሐዋርያት ወንጌልን ማስተማር ያለባቸው ለሚሰሟቸው ሰዎች መሆን እንዳለበት ነግሯቸዋል (ማቴዎስ 10፡14-15፣ ማርቆስ 6፡11፣ ሉቃስ 9፡5-6፣ 10፡11-12)፡፡ ስለዚህ በአንድ አካባቢ የሚደርስባቸውን ስደት ታግሶ በመቆየት የኃጢአት ይቅርታን የሚያስገኘውን ወንጌልን ማስተማር በሐዋርያት ፍላጎት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ወንጌልን በመስበክ የኃጢአት ይቅርታን ማስገኘትም ሆነ ለማይቀበሏቸው ሰዎች ባለመስበክ ኃጢአታቸው እንዳይሰረይ የማድረግ ሥልጣን አላቸው፡፡  ሐዋርያት ለመታከም ፈቃደኛ የሆኑ ህመምተኞችን በማከም እንደሚፈውሱ ዶክተሮች ሲሆኑ መድኃኒቱ ደግሞ ክርስቶስ ነው፡፡ ዶክተሮቹ መድኃኒቱን በመስጠት ይፈውሳሉ፡፡ መድኃኒቱ ከሌለ ግን ዶክተሮቹ መፈወስ አይችሉም፡፡ ዶክተሮቹ መድኃኒት በመስጠት መፈወሳቸው የፈውስ ምንጭ አያደርጋቸውም፡፡ የፈውሱ ምንጭ ዶክተሮቹ ሳይሆኑ መድኃኒቱ ነው፡፡ ሐዋርያት ኃጢኣትን ይቅር እንዲሉ፣ ማለትም የኃጢኣት ይቅርታ ምንጭ የሆነውን ክርስቶስን ለሰው ልጆች እንዲሰብኩ ሥልጣን የሰጣቸው ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመሆኑ ሥልጣኑ የገዛ ራሳቸው እንዳልሆነና የክርስቶስ ሥልጣን እንደሆነ ያሳያል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰዎችን የኃጢአት ይቅርታ በማወጅ ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን እንዳለው በተደጋጋሚ አሳይቷል (ማርቆስ 2፡5-9፣ ሉቃስ 7፡46-49)፡፡ ይህ ደግሞ የፈጣሪ የብቻው ስልጣን ነው፡፡

ኢየሱስ ራሱ ሥልጣን እንደተሰጠው መናገሩ ይህ ሥልጣን የራሱ አለመሆኑንና አምላክ አለመሆኑን አያመለክትምን? ይህንን ጥያቄ የሚጠይቁ ሰዎች እግዚአብሔር አንድ አካል ብቻ እንዳለው ቅድመ ግንዛቤ የያዙ ናቸው፡፡ የሥሉስ አካላት አንዳቸው ከሌላቸው የመቀበላቸውና አንዳቸው ለሌላቸው የመገዛታቸው እውነታ መታየት ያለበት አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ የአንዱ ግፃዌ መለኮት አካላት መሆናቸውን በሚናገረው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ መሠረት እንጂ በነጠላ አሃዳዊነት መሠረት መሆን የለበትም፡፡ ጸሐፊው ግን ከሞላ ጎደል በእያንዳንዱ ጥያቄያቸው ውስጥ ይህንን መሠረታዊ ሃቅ በመዘንጋት የራሳቸውን ቁርአናዊ እምነት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለመጫን ሲሞክሩ ይስተዋላሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ከአብ እንደሚቀበል ብቻ ሳይሆን ለአብ እንደሚሰጥም ጭምር ይናገራል፡- “በኋላም፥ መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ አለቅነትንም ሁሉና ሥልጣንን ሁሉ ኃይልንም በሻረ ጊዜ፥ ፍጻሜ ይሆናል” (1ቆሮንቶስ 15፡24)፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር በመለኮት አንድ ቢሆንም በአካል ግን ሦስት በመሆኑ አንዱ የሥላሴ አካል ከሌላው መቀበሉ ከአንዱ ግፃዌ መለኮት ውጪ ከሚገኝ ሌላ አካል እስካልተቀበለ ድረስ አምላክነቱን ሊያጠራጥር አይችልም፡፡ ሌላው መረሳት የሌለበት ነጥብ በባሕርዩ ፍፁም አምላክ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክብሩን ጥሎ የባርያን መልክ በመያዝ ወደ ምድር መምጣቱ ነው (ዮሐንስ 6፡38፣ ማቴዎስ 20፡24-28፣ ፊልጵሲዩስ 2፡5-8)፡፡ ስለዚህ ተልዕኮውን ከፈፀመ በኋላ አብ አክብሮታል፡-

“በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው” (ፊልጵሲዩስ 2፡9-11)፡፡

በማቴዎስ 28፡18 ላይ የሚገኘውን ቃል በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ከተመለከትን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን ለአባቱ ታዞ በራሱ ፈቃድ ትቶት የመጣውንና መለኮታዊ መብቱ የሆነውን ሥልጣን መልሶ ተቀበለ እንጂ የእርሱ ያልሆነውን ስላልተቀበለ ይህ አባባል አምላክነቱን አጠራጣሪ ለማድረግ ምክንያት አይሆንም፡፡ በሦስተኛ ደረጃ መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር ከተሠግዎ በፊት ጌታችን ፍፁም አምላክ እንደነበረና ከተሠግዎ በኋላ ግን አምላካዊ ባሕርዩ ሳይለወጥ ፍፁም ሰው መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ክብሩ የተመለሰው ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ ሆኖ ነው፡፡ የአባቱን ፈቃድ ያለ ምንም እንከን ከዳር በማድረሱ መለኮታዊ ባሕርዩ ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊ ባሕርዩም ጭምር ክብርን ተቀዳጅቷል፡፡ ይህ ደግሞ በስሙ የሚያምኑት ቅዱሳን የርስቱ ወራሽ እና የግዛቱ ተካፋይ ስለመሆናቸው ማረጋገጫ ነው (ሉቃስ 22፡29-30፣ ዮሐንስ 17፡24፣ ሮሜ 8፡17፣ ራዕይ 2፡26-27፣ ራዕይ 3፡21)፡፡

አሕመዲን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣንን ከአብ መቀበሉን የሚናገረውን ቃል ብቻ ነጥለው ጠቀሱ እንጂ ሙሉ አውዱን ቢያነቡት ኖሮ የኢየሱስን አምላክነት አሻሚ ባልሆነ ሁኔታ በተመለከቱ ነበር፡፡ እስኪ በክፍሉ አውድ ውስጥ የሚገኙትን ደምቀው የተጸፉትን ቃላት ልብ ብለን እንመልከት፡-

“አሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ግን ኢየሱስ ወዳዘዛቸው ተራራ ወደ ገሊላ ሄዱ፥ ባዩትም ጊዜ ሰገዱለት፤ የተጠራጠሩ ግን ነበሩ፡፡ ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ፡፡ እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴዎስ 28፡16-20)፡፡

በዚህ ቦታ ላይ ሐዋርያት ለኢየሱስ ሰግደዋል፡፡ የአሕመዲን ሃይማኖት አጥብቆ እንደሚያስተምረው ኢየሱስ ሰው ብቻ ቢሆን ኖሮ ሌሎች ቅዱሳን ሰዎችና መላዕክት እንዳደረጉት ሐዋርያቱ እንዳይሰግዱለት በነገራቸው ነበር (የሐዋ. ሥራ 10፡25-26፣ ራዕይ 22፡8-9)፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ አንድም ጊዜ ያንን አድርጎ አያውቅም፡፡ ኢየሱስ በሰማይና በምድር ሥልጣን ሁሉ እንደተሰጠው ተናግሯል፡፡ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ እና ወራሽ ባይሆን ኖሮ አብ እንዴት በሰማይና በምድር ሥልጣንን ሁሉ ይሰጠው ነበር? የጥምቀቱ ደግሞ ከሁሉም በላቀ ሁኔታ አምላክነቱን ይገልጣል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የእግዚአብሔር ስም ባሕርዩን ይወክላል (ዘፀአት 33፡17-23፣ 34፡5-7)፡፡ የእግዚአብሔርን ስም ማመስገን ማለት እግዚአብሔርን ማመስገን ማለት ነው (መዝሙር 7፡17)፡፡ የእግዚአብሔር ስም ረዳታችን እንደሆነ መናገር እግዚአብሔር ረዳታችን እንደሆነ መናገር ነው (መዝሙር 124፡8፣ 121፡2)፡፡ በእግዚአብሔር ስም መምጣት ማለት በእግዚአብሔር ኃይል መምጣት ማለት ነው (1ሳሙኤል 17፡45፣ ዮሐንስ 5፡43)፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔርና ስሙ አይነጣጠሉም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀት የገዛ ስሙ ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ እኩል እንዲጠቀስ በማዘዝ አንድ ስም እንዳላቸው ግልፅ አድርጓል፡፡ ይህም ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በባሕርይም ሆነ በአገዛዝ አንድ መሆኑን ያሳያል፡፡ ማንም ፍጡር እንዲህ ዓይነት ነገር ቢናገር በእውነተኛው አምላክ ላይ ክህደትን መፈፀም በመሆኑ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ አሁንም በዚሁ ስፍራ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ዓለም ፍፃሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደሚሆን በመናገር በሁሉም ቦታ መገኘቱን አስታውቋል፡፡ በእርግጥ በሁሉ ቦታ መገኘት መቻሉን ሲናገር ይህ ለመጀመርያ ጊዜ አይደለም (ማቴዎስ 18፡20 ይመልከቱ)፡፡ ማንም ሰው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥልጣን ከአብ መቀበል በዚህ አውድ ውስጥ በማንበብ መረዳት ያስፈልገዋል እንጂ ከአውዱ ገንጥሎ በማውጣት የተለየ ትርጉም መስጠት የለበትም፡፡ አሕመዲን እና መሰሎቻቸው ይህንን ሐሳብ በደንብ መረዳት ይችሉ ዘንድ እስኪ በዚህ ጥቅስ ውስጥ በኢየሱስ ፋንታ መሐመድን እናስቀምጣቸውና ይቀበሉት እንደሆን እንይ፡-

“ከሰሃባዎች[5] መካከል አስራ አንዱ ግን መሐመድ ወዳዘዛቸው ተራራ ሄዱ፥ ባዩትም ጊዜ ለመሐመድ ሰገዱለት፤ የተጠራጠሩ ግን ነበሩ፡፡ መሐመድም ቀረበና እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ፡፡ እንግዲህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ በአላህ በመሐመድ እና በጂብሪል[6] ስም እየገረዛችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው አስልሟቸው፤ እነሆም እኔ መሐመድ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ፡፡

ከላይ የሰፈረው ሐሳብ ከእስልምና አስተምህሮ ጋር በእጅጉ ስለሚጣረስ መቼም ቢሆን እንዲህ ዓይነቱን አባባል የሚቀበል ሙስሊም አይኖርም፡፡ አሕመዲን ሦስት ምርጫ ብቻ ነው የሚኖራቸው፡፡ የኢየሱስን ንግግር በመቀበል አምላክ መሆኑን አምነው መጠመቅ፣ ኢየሱስ ተሳስቷል ብሎ በመደምደም ከእስልምናም ሆነ ከክርስትና ጋር መጣላት ወይም ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ተበርዟል የሚለውን ማስረጃ የሌለውንና ጊዜ ያለፈበትን መዝሙራቸውን እየዘመሩ በሃይማኖታቸው መፅናት፡፡

 

 

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች የተሰጠ መልስ ማውጫ