ኢየሱስ መስቀል ላይ ሆኖ “አምላኬ አምላኬ ስለምን ተውከኝ” ብሎ ሲለምን አምላክ ነበር ወይስ ሰው?

 


8. ኢየሱስ መስቀል ላይ ሆኖ “አምላኬ አምላኬ ስለምን ተውከኝ” ብሎ ሲለምን አምላክ ነበር ወይስ ሰው? ሰው ከሆነ የሞተው ኢየሱስ የተባለው ግለሰብ ነበር ማለት ነው፡፡ እንዴትስ አምላክ ሌላ አምላክ ይለምናል? የማይሞተው እግዚአብሔር አምላክ ሞተ ይባላልን?

ይህ ጥያቄ በምዕራፍ 1 ቁጥር 8 ላይ ከተመለሰው ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ ስለዚህ በዚያ ቦታ የተመለሰውን እዚህ ስለማንደግም አንባቢ አስቀድሞ ያንን ምላሽ ይመለከት ዘንድ እናበረታታለን፡፡

ጠያቂው ላቀረቡት ጥያቄ በብዙ ክርስቲያኖች ዘንድ የታወቀ መልስ ቢኖርም እኔ ግን ኢየሱስ “አምላኬ አምላኬ ስለምን ተውከኝ” ሲል ስለ እርሱ የተተነበየውን ትንቢት ለመጠቆም እንጂ ለመጸለይ እንዳልሆነ አምናለሁ፡፡ በዚያ ቦታ የተከናወኑት ነገሮች ሁሉ እርሱ በጠቀሰው መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ 22 ውስጥ በዝርዝር የተተነበዩ ሲሆን ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ በጸለየው በዚያ ጸሎት ውስጥ የክርስቶስን መከራ የተመለከቱ ብዙ ዝርዝር ጉዳዮች ተተንብየዋል፡፡ በዚያ የቆሙት ሰዎች ያላግጡበት እንደነበር (ሉቃስ 23፡35)፣ ልብሶቹን መከፋፈላቸውን (ዮሐንስ 19፡23)፣ በእጀ ጠባቡ ላይ ዕጣ መጣጣላቸውን (ዮሐንስ 19፡24)፣ ወዘተ. ከሁሉ በላይ ደግሞ ሰዎችን በመስቀል ላይ ቸንክሮ መግደል ባልተጀመረበት በዳዊት ዘመን እጆቹና እግሮቹ ስለመቸንከራቸው የተነገረው ትንቢት በእጅጉ አስደናቂ ነው (ቁ. 16)፡፡ በክፍሉ ውስጥ የተነገሩት አንዳንድ ነገሮች ክርስቶስን የተመለከቱ ባይሆኑም ነገር ግን በጣም ግልፅ የሆኑ ትንቢቶች በውስጡ ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ ክርስቶስ ጌታችን በመስቀል ላይ ሆኖ የመጀመርያውን ስንኝ መናገሩ ትንቢቱ የተነገረበትን ክፍል ለማመልከት እንጂ ለመጸለይ አልነበረም፡፡ “የኃጢአታችንን የመጨረሻ ቅጣት ለመክፈል በአብ እና በእርሱ መካከል መለያየት እንደተፈጠረ (አብ እንደተወው)” የሚናገሩ ወገኖች የላከው አብ ብቻውን እንደማይተወው ኢየሱስ አስቀድሞ መናገሩን ማስታወስ ያሻቸዋል (ዮሐንስ 8፡29)፡፡ የላከው አብ ብቻውን እንደማይተወው ከተነገረ “አሁን ደግሞ ትቶታል” ብሎ ማለት የመጀመርያውን ስለሚጣረስ ትክክለኛ ትርጓሜ ሊሆን አይችልም፡፡