ኢየሱስ ለአይሁዶች “እኔ ወደ ምሄድበት ልትመጡ አትችሉም” ብሏል፡፡ ታድያ እንዴት ያለበት ድረስ መጥተው “ያዙት” “ሰቀሉት” ሊባል ቻለ?

 


  1. ዮሐንስ 13፡33 “ልጆቼ ሆይ! ከእናንተ ጋር የምቆየው ለጥቂት ጊዜ ነው እናተም ትፈልጉኛላችሁ፤ ለአይሁድ እኔ ወደምሄድበት ልትመጡ አትችሉም” እንዳልኳቸሁ አሁን ለእናተ ይህንኑ እላችኋለሁ” ይላል፡፡ በዚህ ጥቅስ ላይ ኢየሱስ ለአይሁዶች “እኔ ወደ ምሄድበት ልትመጡ አትችሉም” ብሏል፡፡ ታድያ እንዴት ያለበት ድረስ መጥተው “ያዙት” “ሰቀሉት” ሊባል ቻለ? ወይስ ኢየሱስ ዋሸ? አሊያም እንደሚያዝ አያውቅም ነበርን?

ገናናው ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ መዋሸት ባሕርዩ አይደለም፡፡ እንደሚያዝም ያውቅ ነበር (በዚሁ ምዕራፍ ለጥያቄ ቁጥር 26 በተሰጠው መልስ ላይ የተዘረዘሩትን ጥቅሶች ይመልከቱ)፡፡ ነገር ግን ጠያቂው ቀላሉን ጉዳይ መረዳት ተስኗቸዋል፡፡ በዚህ ቦታ ላይ ለአይሁድ የተናገረውን በመድገም ለደቀ መዛሙርቱ እየተናገረ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ለአይሁድ የተናገረው ቃል በዮሐንስ 7፡33 ላይ ተጽፏል፡፡ ወዴት እንደሚሄድም ግልፅ አድርጓል፡- ኢየሱስም፦ ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር እቆያለሁ ወደ ላከኝም እሄዳለሁ፡፡ ትፈልጉኛላችሁ አታገኙኝምም፤ እኔም ወዳለሁበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም አለ፡፡” (ዮሐንስ 7፡33-34)፡፡

አይሁድ ኢየሱስን ፈልገው ሊያገኙ የማይችሉበትና እርሱ ወዳለበት ሊመጡ የማይችሉበት ምክንያት ኢየሱስ ወደ ላከው ወደ አብ ስለሚሄድ ነው፡፡ ኢየሱስ ከትንሳኤው በኋላ ወደ አብ ሄዷል፡፡ አሁን መሲሁን ቢፈልጉ ሊያገኙት አይችሉም፡፡ እርሱ ወዳለበትም መሄድ አይችሉም፡፡