እኔ ለኃጢአታችሁ ቤዛ እሆናለሁ ኃጢአታችሁን በደሜ አጥባለሁ፡፡ ሲል አስተምሮ ነበርን?

 


17. የክርስትና እምነት መሠረቱ “ኢየሱስ ለኛ ኃጢአት ሲል ሞተ ለኃጢአታችን ቤዛ ሆነ፡፡” ነው፡፡ ነገር ግን “ቤዛ” ተብየው በራሱ እኔ ለኃጢአታችሁ ቤዛ እሆናለሁ ኃጢአታችሁን በደሜ አጥባለሁ፡፡ ሲል አስተምሮ ነበርን? የሚል ጥያቄ ቢነሳ ምላሹ አሳፋሪ ነው፡፡ አንዴም አላስተማረም፡፡ ይህ የጳውሎስ ፈጠራና ተጽዕኖ ብቻ ነው፡፡ እንድያውም እንዳይያዝና እንዳይገደል ሲፀልይ፣ ሲደበቅና ሲጨነቅ ነበር፡፡ አልነበረምን?

በዚህ ዓይነት ጠያቂው ኢሳይያስ 53 እና ዳንኤል 9ን የመሳሰሉትን ስለ መሲሁ ሞት እና ቤዛነት የሚናገሩትን የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች “ጳውሎስ ነው የጻፈው!” ከማለት ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ሰው አንዴ ኅሊናውን ጨቁኖ መቀጣጠፍ ከጀመረ ምን ማቆሚያ ይኖረዋል? የተወደደው ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ከኢየሱስ ዕርገት በኋላ ነበር ክርስቲያን የሆነው (የሐዋርያት ሥራ 9)፡፡ ስለ ኢየሱስ ትንሳኤና ቤዛነት የሚሰብኩትን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሲያሳድድ የነበረ ሰው ይህንን ትምህርት እንደፈጠረ መናገር በእጅጉ አስቂኝ ነው፡፡ አሳፋሪ የሆነውን የኡስታዙን አለማወቅ የሚያጋልጡ፣ ኢየሱስ ለሰው ልጆች ነፍሱን ቤዛ ለማድረግ ወደ ምድር እንደመጣና በደሙ የሰው ልጆችን ኃጢአት እንደሚያጥብ መናገሩን የሚገልፁ ሁለት ጥቅሶችን እንጠቅሳለን፡-

“እንዲሁም የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም” (ማቴዎስ 20፡28)፡፡

ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ፦ ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው፡፡” (ማቴዎስ 26፡26-28)፡፡

የኢየሱስን መጨነቅ በተመለከተ አንባቢያንን በድጋሜ ወደ ቁጥር 50 እንመራለን፡፡ ነገር ግን “ኢየሱስ እንዳይያዝ ሲጸልይ፣ ሲጨነቅ እና ሲደበቅ ነበር” የሚለው አባባል የከፋ እብለት ነው፡፡ ኢየሱስ ፅዋው ከእርሱ እንዲያልፍ መጸለዩ እውነት ቢሆንም ነገር ግን እንደ አብ ፈቃድ እንጂ እንደ እርሱ ፈቃድ እንዳይሆን በመጸለይ የአብን ፈቃድ ለመፈጸም ዝግጁ መሆኑን አሳይቷል (ሉቃስ 22፡42)፡፡ ኢየሱስ ጊዜው ሲደርስ አልተደበቀም፡፡ ብዙ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደሚሆንበት የአትክልት ቦታ ነበር የሄደው፡፡ ይሁዳ ያንን ቦታ ያውቀዋል፡፡ መደበቅ ቢፈልግ ኖሮ ወደዚያ ባልሄደ ነበር (ዮሐንስ 18፡1-2)፡፡ ሊይዙት ሲመጡም ከመሸሽ ይልቅ እነርሱ ወዳሉበት በመሄድ ማንን እንደሚፈልጉ ጠየቃቸው፡፡ “የናዝሬቱ ኢየሱስን” ሲሉት “እኔ ነኝ” በማለት በፈቃዱ ራሱን አሳልፎ ሰጠ (ዮሐንስ 18፡4-8)፡፡ ጠያቂው በግምት እና በስሜታዊነት ከሚጽፉ ማስረጃዎችን ካጤኑ በኋላ ተረጋግተው ቢጽፉ ኖሮ ትዝብት ላይ ባልወደቁ ነበር፡፡