ኢየሱስ ዓለምን የማዳን ተልዕኮ ይዞ ከተሰቀለ ከሦስት ቀናት በኋላ እንደሚነሳ እያወቀ ያ ሁሉ መሸሽና መሸበር ይገባው ነበርን?

 


  1. ኢየሱስ ከአብረሃም ልጅ ያንሳልን? አምላክ አብረሃምን ልጅህን እረድ ሲለው ታዛዥ ሆኖ ሊታረድ ቀረበ፡፡ ኢየሱስ ዓለምን የማዳን ተልዕኮ ይዞ ከተሰቀለ ከሦስት ቀናት በኋላ እንደሚነሳ እያወቀ ያ ሁሉ መሸሽና መሸበር ይገባው ነበርን?

አብርሃም ልጁ ይስሐቅን ሊሰዋ በወሰደው ጊዜ ምን እየሆነ እንደነበር ይስሐቅ አላወቀም ነበር (ዘፍጥረት 22፡7-8)፡፡ ቢያውቅ ኖሮ መፍራቱ ግድ ነው፡፡ የአብርሃም ልጅ ለመስዋዕትነት እየተወሰደ መሆኑን እያወቀ እንደ ስሜት አልባ ሮቦት አባቱን ተከትሎ እንደሄደ የሚናገረው እስላማዊ ታሪክ ተዓማኒነት የለውም፡፡ ኢየሱስ ከፊቱ ያለውን መከራ በዝርዝር ያውቅ ስለነበር ተጨንቋል ነገር ግን ቀደም ሲል እንደተመከለትነው በፈቃዱ ራሱን አሳልፎ ሰጠ እንጂ አልሸሸም፡፡ አሕመዲን የመስቀል መከራ ለምን ይሆን እንዲህ የቀለለባቸው? ምናልባት ስለ ስቅለት ዝርዝር ሂደት መረጃ ስለሌላቸው ይሆናል፡፡ አንድ ሰው ከመሰቀሉ በፊት በከባድ ሁኔታ ይገረፋል፡፡ ኢየሱስ በሮማውያን እጅ ብቻ ሳይሆን በአይሁድ ሸንጎም ተገርፏል፡፡ አይሁድ 40 ጅራፍ ነው የሚገርፉት፡፡ ከ40 አልፈው ህጉን እንዳይተላለፉ ምናልባት የቆጠራ ስህተት ካለ በሚል 39 ላይ ያቆማሉ፡፡ ሮማውያን ደግሞ የፈለጉትን ያህል ነው የሚገርፉት፡፡ አለንጋዎቹ ብዙ ቅርንጫፎች ያሏቸው ሲሆኑ በየአንጓዎቹ ላይ የብረት እና የአጥንት ጉጠቶች ይሰካሉ፡፡ ጅራፎቹ በተገራፊው ጀርባ ላይ ሲያርፉ ብረቶቹና አጥንቶቹ ቆዳውንና ሥጋውን ቦጭቀው ያነሳሉ፡፡ ከጥቂት ጅራፎች በኋላ የሰለባው የላይኛው ቆዳ ተገፎ ከስር ያለው ጡንቻ ይከፈታል፡፡ ግርፋቱ ሲቀጥል ጡንቻዎቹ ተበጣጥሰው የደም ስሮች መቆራረጥ ይጀምራሉ፤ ከተቆራረጡት ስሮች ውስጥ ደም ይንዶለዶላል፡፡ ብዙ ጊዜም የተገራፊዎቹ ሆድ ተከፍቶ አንጀታቸው እስከመውጣት ይደርሳል፡፡ ከዚህ የተነሳ ብዙዎቹ እዚያው ይሞቱ ነበር፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ ወደ መሰቀያ ቦታ ተወስደው እጆቻቸውና እግሮቻቸው ሰባት ኢንች በሚረዝሙ ሚስማሮች በእንጨት ላይ ይቸነከራሉ፡፡ የእጅ መዳፎች የአንድን ሰው ክብደት መሸከም ስለማይችሉ ሚስማሮቹ ከመዳፍ ከፍ ብለው በክንድ አጥንቶች መካከል ይመታሉ፡፡  በዚህ ጊዜ ሚስማሮቹ የእጅ ነርቮችን በጣጥሰው ስለሚያልፉ ሰለባዎቹ ለከፍተኛ የሥቃይ ስሜት ይዳረጋሉ፡፡ ወደ ላይ ቀጥ ተደርገው ስለሚሰቀሉ መተንፈስ በእጅጉ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ተወጥረው ከተሰቀሉ ወዲያውኑ ታፍነው ስለሚሞቱ እግሮቻቸው ትንሽ አጠፍ ተደርገው ይቸነከራሉ፡፡ ለመተንፈስ በእግሮቻቸው ላይ በተሰካው ሚስማር ላይ ቆመው ወደ ላይና ወደ ታች እንደ ፓምፕ መንቀሳቀስ ያስፈልጋቸዋል፡፡ አየር ለማስገባት እግሮቻቸውን አጥፈው ወደ ታች ዝቅ ይላሉ፡፡ ለማስወጣት ደግሞ እግሮቻቸውን ወጥረው ወደ ላይ ይላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የተሰቀሉበት ደረቅ እንጨት በግርፋት የቆሰለውን ጀርባቸውን ይፈቀፍቃቸዋል፡፡ እንቅስቃሴውን ለአፍታ ካቆሙ ወዲያውኑ ታፍነው ይሞታሉ፡፡ ለዚህ ነው ከኢየሱስ ጋር የተሰቀሉትን ወንበዴዎች ቶሎ እንዲሞቱ ለማድረግ ጭኖቻቸውን የሰበሩት፡፡[2] ይህንን ስቃይ ለማስታገስ ሮማውያን ብዙ ጊዜ ሀሞት፣ ከርቤና የወይን ጠጅ የተቀላቀለበትን አደንዛዥ መጠጥ ይሰጧቸው ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ግን ይህንን መጠጥ በመጠጣት ህመሙን ከማስታገስ ይልቅ ሙሉ ሥቃዩን በመቀበል መሞትን መረጠ (ማርቆስ 15፡23፣ ማቴዎስ 27፡34)፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ለሦስት ሰዓታት ያህል በእንዲህ ዓይነት ሥቃይ ውስጥ በማለፍ ነበር የመጨረሻ እስትንፋሱን የተነፈሰው፡፡ የዓለምን ሁሉ ኃጢአት መሸከም ደግሞ ምን ያህል ለሥቃይ እንደሚዳርግ ከእርሱ በስተቀር ማን አየው? እንግዲህ ጠያቂው እንዲህ ዓይነቱን መከራ እንደሚያስተናግድ በማወቁ ምክንያት ኢየሱስ መጨነቁ ተገቢ አልነበረም የሚል የሞኝ ሙግት ነው የገጠሙት፡፡