ኢየሱስ ከሞት በተነሳ ጊዜ ከመቃብር ወጥተው ወደ ከተማ ገቡ የተባሉ ሰዎች በኋላ የት ገቡ?
-
ማቴዎስ 27፡52-53 “መቃብሮችም ተከፍተው ሞተው ለነበሩት ብዙ ቅዱሳን ሰዎች ከሞት ተነሱ፡፡ ከመቃብርም ወጡና ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ወደ ቅድስት ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም ገቡ፤ በዚያም ለብዙ ሰዎች ታዩ፡፡” ይላል፡፡ እነዚህ ሰዎች በኋላ የት ገቡ? ይህን እጅግ አስገራሚ ትዕይንት ሊሆን የሚችል ነገር ለምን ሌሎች ወንጌል ጸሐፊዎች ሳይጽፉት ቀሩ? ይህ ክስተት ተፈፅሞ ቢሆን ኖሮ ከኢየሱስ ተዓምር ይተናነስ ነበርን? በዚሁ ሰበብ ብቻ ከከሀዲያን የሚያምን ሰው ሁሉ አልነበረምን? ሰዎችስ ሞትና ወዲያኛው ዓለም ምን እንደሚመስል ይጠይቋቸው አልነበረምን? ይገልጹስ አልነበረምን? ሰዎች በትንሳኤ ከሙታን ይቀሰቅሳሉ የተባለው ሳይደርስ መቀስቀሳቸውን ለሰው እንዴትስ አብራሩት?
ይህንን ክስተት የዘገበው ማቴዎስ ብቻ በመሆኑ ምክንያት ብዙ ሰዎች ታሪካዊነቱን አጠያያቂ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ የተቀሩት ወንጌላት ለምን እንዳልዘገቡት እርግጠኛ ሆኖ መናገር ባአይቻልም የማቴዎስ ወንጌል የተጻፈው የመስቀሉ ትውልድ ከማለፉ በፊት በመሆኑ እውነት መሆን አለመሆኑን መመስከር የሚችሉ ሰዎች ባሉበት ሁኔታ እንዲህ ዓይነቱን ታሪክ ፈጥሮ መጻፍ የማይታሰብ ነው፡፡ ጠያቂው ያቀረቧቸው የተቀሩት ጥያቄዎች ይህ ክስተት ታሪካዊ አለመሆኑን የሚያሳዩ አይደሉም፡፡ እነዚህን ቅዱሳን ሰዎች አይተው ያመኑ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ሰዎችም ስለ ሞትና ስለ ወዲያኛው ዓለም ጠይቀዋቸው እነርሱም ተናግረው ሊሆን ይችላል፤ ከመጨረሻው ዘመን በፊት እንዴት ከሙታን ሊነሱ እንደቻሉ ተናግረውም ሊሆን ይችላል፡፡ ስላልተጻፈ ብቻ እነዚህ ሁሉ ነገሮች አልተከሰቱም ልንል አንችልም፡፡ ነገር ግን ከተጻፈው በማለፍ መናገርም ተገቢ አይደለም፡፡ ጠያቂው ሙስሊም እንደመሆናቸው እንዲህ ያለውን ጥያቄ ማንሳታቸው በእጅጉ አስገራሚ ነው፡፡ ቁርኣን ሱራ 2፡259 እና 18፡25 ላይ የተወሰኑ ወጣቶች ከውሻቸው ጋር ለ 300 ዓመታት ያህል በእንቅልፍ እንዳሳለፉና እንደነቁ ይናገራል፡፡ ይህ ታሪክ እውነት ቢሆን ኖሮ ስለምን በሌሎች የታሪክ መዛግብት ተጽፎ አላገኘነውም? ዳሩ ግን ይህ ታሪክ እውነተኛ ባለመሆኑና በ 521 ዓ.ም. ገደማ በሦርያ ከተጻፈ የተረት መጽሐፍ ላይ የተወሰደ በመሆኑ በተዓማኒ የታሪክ መዛግብት ውስጥ እንዲገኝ አንጠብቅም፡፡[3] ሙሐመድ ጨረቃን ለሁለት የመግመስ ተዓምር እንዳደረጉ በእስላማዊ ምንጮች ውስጥ ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ሱራ 54፡1 ላይ የሚገኘው ቃል ስለዚያ ክስተት እንደሚናገር ብዙ ሙስሊም ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ ይህ ክስተት በእውነት የተፈፀመ ቢሆን ኖሮ ስለምን በሌሎች የታሪክ መዛግብት ውስጥ አልተጻፈም? ወይስ በዚያ ዘመን ጨረቃ የምትወጣው በአረብያ ብቻ ነበር?