ለሰው ኃጢአት የተሰዋው አምላክ ከሆነ እንዴት አምላክ ራሱን ለራሱ ይሰዋል?

 


  1. ለሰው ኃጢአት የተሰዋው አምላክ ከሆነ እንዴት አምላክ ራሱን ለራሱ ይሰዋል? ወይስ ከሦስቱ አንዱ ነው ለሁለቱ የሚሰዋው?

ሰው ኃጢአትን ሲሠራ የእግዚአብሔር ፍትህ ባለ ዕዳ ስለሚሆን መስዋዕቱ የሚቀርበው ለእግዚአብሔር ፍትሃዊ ባሕርይ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው ለሌላው ቤዛ ሆኖ ለእግዚአብሔር ወጆ መክፈል እንደማይችል ይናገራል፡-

“የሌላውን ሕይወት መቤዠት የሚችል ሰው፣ ወይም ለእግዚአብሔር ወጆ የሚከፍልለት ማንም የለም፡፡ የነፍስ ቤዛ ውድ ነውና፤ በቂ ዋጋም ከቶ ሊገኝለት አይችልም” (መዝሙር 49፡7-8 አ.መ.ት.)፡፡

ሰው ሁሉ ኃጢአተኛ ስለሆነ ለሌላው ቤዛ መሆን ይቅርና ራሱን እንኳ ማዳን አይችልም (ሮሜ 3፡9-10፣ 3፡23)፡፡ ለዚህ ነው ፍፁም ቅዱስና ፃድቅ የሆነ፣ የሰው ልጆችን ኃጢአት በሙሉ የመሸከም ብቃት ያለው ቤዛ ያስፈለገው፡፡ ነቢዩ ዳዊት ለዚህ የሚበቃውና የሌላውን ነፍስ መቤዠት የሚችለው እግዚአብሔር እንደሆነ ይናገራል፡-

“እግዚአብሔር ግን ነፍሴን ከሲኦል እጅ ይቤዣታል፤ በእርግጥም በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት አለኝ” (መዝሙር 49፡15 አ.መ.ት.)፡፡

ከሦስቱ የሥላሴ አካላት መካከል አንዱ የሆነው ወልድ ወደ ምድር በመምጣት ስለ ኃጢአታችን ሲል ራሱን ለአብ መስዋዕት አድርጎ በማቅረብ እዳችንን ከፈለ፤ ከኃጢአት ባርነትም ነፃ አወጣን፡-

“ክርስቶስም ደግሞ እንደ ወደዳችሁ ለእግዚአብሔርም የመዓዛ ሽታ የሚሆንን መባንና መሥዋዕትን አድርጎ ስለ እናንተ ራሱን አሳልፎ እንደ ሰጠ በፍቅር ተመላለሱ፡፡” (ኤፌሶን 5፡2)

“ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን?” (ዕብራውያን 9፡14)

ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ፡፡ ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ፡፡ (1ዮሐንስ 2፡1-2)

ክርስቶስ ጌታችን የእኛን ኃጢአት ተሸክሞ እኛ መቀጣት የሚገባንን ቅጣት ተቀጣልን፡፡ አብ የክርስቶስን መስዋዕትነት ተቀበለ፤ በእኛ ላይ መፈፀም የነበረበት የእግዚአብሔር ፍትሃዊ ቁጣ ኃጢአታችንን በተሸከመው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ስለተፈፀመ ከቁጣው ዳንን (ሮሜ 3፡25-26፣ ዕብራውያን 2፡9-18)፡፡ ይህ ጉዳይ በዕውቀቱ፣ በጥበቡና በባሕርዩ ከእኛ እጅግ ከላቀው ከቅዱስ እግዚአብሔር ዕይታ አኳያ የተከናወነ በመሆኑ ሚስጥሩን ውሱን በሆነው አዕምሯችን መርምረን ልንደርስበት እንደምንችል በማሰብ ስህተት መስራት የለብንም፡፡ እኛ ማወቅና መረዳት የምንችለው በቃሉ ውስጥ በተገለጠልን መጠን ብቻ እንጂ የእግዚአብሔርን ሥራ በተገደበው አዕምሯችን መርምረን ልደርስበት አንችልም፡፡ የእግዚአብሔርን ሥራ ሙሉ በሙሉ መረዳት የሚችል አዕምሮ እንዳለን በትዕቢት በማሰብ በቃሉ ውስጥ የተገለጠውን እውነት በመፃረር እንዳንጠፋ መጠንቀቅ ያስፈልገናል፡፡

ነገር ግን ጠያቂያችን አላህ የአይሁዶችንና የክርስቲያኖችን ነፍስ መስዋዕት በማድረግ ከገሃነም እንደሚቤዣቸው ስለሚያምኑ ችግር ውስጥ ሊገቡ ነው፡፡ በተከታዩ ሐዲስ መሠረት አላህ መስዋዕቱን የሚከፍለው ለማነው?

“አቡ ቡርዳ አባቱን ዋቢ በማድረግ እንዳስተላለፈው የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) እንዲህ ብለዋል፡- ከሙስሊም አንድም አይሞትም አላህ በእርሱ ፋንታ አይሁዳዊ ወይም ክርስቲያን በገሃነም ውስጥ የሚጥል ቢሆን እንጂ፡፡” [4]