አምላክ አዳምን እንዲሁ መማር እየቻለ ለምን የኢየሱስ ደም እንዲፈስ ፈለገ?

 


  1. አምላክ አዳምን እንዲሁ መማር እየቻለ ለምን የኢየሱስ ደም እንዲፈስ ፈለገ? ደም ማፍሰስ የፈጣሪ ባህሪ ነውን?

በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የኃጢአት ውጤቱ ሞት ነው (ምሳሌ 10፡16፣ ሮሜ 6፡23)፡፡ እግዚአብሔር የፍቅር አምላክ የሆነውን ያህል የፍትህም አምላክ ነው (ኢሳይያስ 28፡17፣ 61፡8፣ ምሳሌ 24፡12፣ ሮሜ 1፡18-32፣ 2፡5)፡፡ የፍትህ አምላክ የሆነው እግዚአብሔር ያለ ቅጣት ኃጢአተኛን ማሰናበት ከባሕርዩ ጋር ይጣረሳል፡፡ ነገር ግን የፍቅር አምላክ እንደመሆኑ መጠን ደግሞ የሰው ልጆች ለዘለዓለም ከእርሱ ተለይተው እንዲጠፉ አልፈለገም፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር ፍትህ ባለዕዳዎች የሆንነውን እኛን እዳችንን በመክፈል ነፃ የሚያወጣንን ቤዛ በማዘጋጀት ፍትሃዊ ባሕርዩን ሳይጣረስ ፍቅሩን ገለጠልን፡፡ የክርስቶስ ደም እንዲፈስስ ማድረጉ እግዚአብሔር ደም አፍሳሽ የሆነ ባሕርይ እንዳለው እንድንናገር አያስችለንም፡፡ ለምሳሌ ያህል አንድ ሕግ አስፈፃሚ የሞት ፍርድ የተፈረደበትን ሰው እንዲገደል ሲያደርግ ፍትህን ለማስፈፀም ያንን ይፈፅማል እንጂ ደም ማፍሰስ ባሕርዩ ስለሆነ አይደለም፡፡ ፍርድ በተላለፈበት ሰው ላይ ፍትህን ተፈፃሚ ማድረጉ እንደ ትክክለኛ እርምጃ የሚቆጠር እንጂ ደም ማፍሰስ የሰውየው ባሕርይ እንደሆነ በመናገር ሰውየውን አያስወቅስም፡፡