“ወደ ኢየሱስ በሄዱ ጊዜ ግን እርሱ ቀደም ብሎ እንደ ሞተ አይተው ጭኑን አልሰበሩም” ከተባለ የሞተ ሰው ቢወጋ ደም ይፈሰዋልን?
-
በዮሐንስ 19፡32 -36 ላይ “ስለዚህ ወታደሮቹ ሄደው ከኢየሱስ ጋር የተሰቀሉትን ሰዎችን ጭን ሰበሩ፤ ወደ ኢየሱስ በሄዱ ጊዜ ግን እርሱ ቀደም ብሎ እንደ ሞተ አይተው ጭኑን አልሰበሩም፡፡ ነገር ግን ከወታደሮቹ አንዱ ጎኑን በጦር ወጋው፡፡ ወዲያውም ከጎኑ ደምና ውሃ ወጣ፡፡ ይህንን ያየ እናንተ እንደምታምኑ መሰከረ፡፡ ምስክርነቱም እውነት ነው፡፡ የሚናገረውም እውነት እንደሆነ እርሱ ያውቃል፡፡ ይህም የሆነው “ከእርሱ አንድ አጥንት እንኳ አይሰበርም” የሚለው የመፅሐፍ ቃል እንዲፈፀም ነው” ይላል፡፡ “ትንቢት” የተባለው የሚከተለው ነው “ደግ ሰው በብዙ መከራ ይፈተናል፤ እግዚአብሔር ግን ከዚህ ሁሉ ያድነዋል፡፡ እግዚአብሔር በጥንቃቄ ስለ ሚጠብቀው ከአጥንቶቹ አንዱ እንኳ አይሰበርም» (መዝሙር 34: 19-20)፡፡
ሀ). የሞተ ሰው ቢወጋ ደም ይፈሰዋልን?
የሞተ ሰው ልቡ አካባቢ ከተወጋ የተጠራቀመ ደም ይፈስሳል፡፡ ወታደሩ ኢየሱስን ሲወጋው ደም ብቻ ሳይሆን ደምና ውኀ ተለያይቶ ነበር የፈሰሰው፡፡ ይህ በሁለት ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል፡፡ የመጀመርያው ሰው ሲሞት ደም ስለሚረጋ ከውኀ ይለያል፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ልብ አካባቢ ውኀ መሳይ ፈሳሽ ስላለ የሞተ ሰው ሲወጋ ይህ ፈሳሽ ከደም ተለይቶ ይወጣል፡፡ በዚህም ሆነ በዚያ ደምና ውኀ መውጣቱ የኢየሱስን መሞት መቶ በመቶ ያረጋገጠ ክስተት ነበር፡፡[5] ይህንን ጉዳይ ያጠኑ የጤና ተመራማሪዎች የጥናታቸውን ውጤት ማርች 21፣ 1986 ዓ.ም. በታተመው Journal of the American Medical Association ላይ ያሰፈሩ ሲሆን ደምና ውኀ መውጣቱ ኢየሱስ በጦር ከመወጋቱ በፊት መሞቱን መቶ በመቶ ያረጋገጠ ክስተት መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡[6] የተሰቀለ ሰው ከመስቀል ላይ ከመውረዱ በፊት ጭኑን በመስበር ወይም ልቡን በጦር በመውጋት ሞቱን ማረጋገጥ የሮማውያን ልማድ ነበር፡፡ ጠያቂው ይህንን ክስተት ኢየሱስ ላለመሞቱ እንደ ማስረጃ መጠቀማቸው ዓለም ከደረሰበት መረጃ ምን ያህል የራቁና ወደ ኋላ የቀሩ መሆናቸውን ያመለክታል፡፡
ለ). ትንቢቱ “እግዚአብሔር ግን ከዚህ ሁሉ ያድነዋል” ይላል፡፡ ግና በተቃራኒው ክርስትና እንደሚለው ኢየሱስ ሳይድን ሞቷል፡፡ ታድያ ጸሐፊው ለምን ያለመሞቱን ትቶ የአጥንቱን አለመሰበር ብቻ ተረከልን?
ሐ). ወይስ ትንቢቱ በትክክል ሳይፈፀም ቀረ?
ትንቢቱ በትክክል ተፈፅሟል ነገር ግን ጠያቂው “እግዚአብሔር ግን ከዚህ ሁሉ ያድነዋል” የሚለውን ሐረግ “ደግ ሰው በብዙ መከራ ይፈተናል” ከሚለው ለይተው በማንበባቸው ምክንያት ለጥቅሱ የተሳሳተ ትርጓሜ በመስጠት ግራ ተጋብተዋል፡፡ ይህ ጥቅስ ቅዱሳን ሰዎች በብዙ መከራ እንደሚፈተኑ ይናገራል፡፡ ብዙ የእግዚአብሔር ሰዎች እስከ ሞት ድረስ በብዙ መከራ መፈተናቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል (ዘፍጥረት 4፡3-8፣ ዮሐንስ 16፡1-4፣ የሐዋርያት ሥራ 14፡19-22፣ ፊልጵስዩስ 1፡29፣ 2ጢሞቴዎስ 3፡10-13፣ ዕብራውያን 11፡32-38፣ ራዕይ 6፡9-11)፡፡ እግዚአብሔር ለቅዱሳኑ በመከራ ውስጥ የሚፀኑበትን አቅም በመስጠትና ካለፉ በኋላ ንፅህናቸውን በተዓምራቱ በማረጋገጥ እንዲሁም ደማቸውን በመበቀል ድልን ይሰጣቸዋል፡፡ የጠያቂው መመርያ የሆነው ቁርኣን እንኳ በመከራ ውስጥ ያለፉና የተገደሉ ነቢያት ስለመኖራቸው ይናገራል (ሱራ 2፡87፣ 2፡91)፡፡ ኢየሱስ በብዙ መከራ ውስጥ በማለፍ ቢፈተንም ነገር ግን በትንሳኤው አማካይነት መከራውን ድል ነስቷል፡፡ የክርስቶስ ምሳሌ የሆነው የፋሲካው በግ አጥንት እንዳይሰበር እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ውስጥ ትዕዛዝን በመስጠቱ ምክንያት የክርስቶስ አጥንት ቢሰበር ኖሮ የፋሲካውን መስዋዕት መስፈርት ስለማያሟላ ቤዛችን መሆን ባልቻለም ነበር (ዘጸአት 12፡46፣ ዘኁልቁ 9፡12፣ 1ቆሮንቶስ 5፡7)፡፡ “ከእርሱ አጥንት አይሰበርም” የሚለው ቃል በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ ከሚገኘው ትንቢት ይልቅ ይኸኛውን ትዕምርታዊ ትንቢት እንደሚያመለክት ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ይስማሙበታል፡፡