ኢየሱስ የሚያዝና የሚገደል ከሆነ “ትፈልጉኛላችሁ ግን አታገኙኝም፤ ወዳለሁበትም ልትመጡ አትችሉም” ማለቱ ትርጉም አልባ አልሆነምን?
-
የዮሐንስ ወንጌል 7፡33-34 “ኢየሱስም እንዲህ አለ ከእናተ ጋር የምቆየው ጥቂት ግዜ ነው ከዛም ወደ ላከኝ እሄዳለሁ፤ ትፈልጉኛላችሁ ግን አታገኙኝም ወዳለሁበት ልትመጡ አትችሉም፡፡” ይላል፡፡ ኢየሱስ “ከእናንተ ጋር የምቆየው ጥቂት ጊዜ ነው፤ ከዛም ወደ ላከኝ እሄዳለሁ፡፡” አለ እንጂ “ከዚያም በኋላ ይዛችሁ ትሰቅሉኛላችሁ፤ ከዚያም በሶስተኛ ቀን እነሳለሁ፤ ከዚያም ወደ ላከኝ እሄዳለሁ” እንዳላለ ልብ ብለዋልን? ምን አናልባት “ከዚያም ወደ ላከኝ እሄዳለሁ” ብቻ ማለቱ ፍፃሜውን በአጭሩ ለመግለፅ ነው የሚል የዋህ ክርክር ሊነሳ ይችላል፡፡ ኢየሱስ ተይዞ፣ ተፈርዶበት፣ ተሰቅሎ ሞቶ፣ ከዚያም ወደ ላከው የሚሄድማ ከሆነ “ትፈልጉኛላችሁ ግን አታገኙኝም፤ ወዳለሁበትም ልትመጡ አትችሉም” ማለቱ ትርጉም አልባ አልሆነምን? ወይስ ኢየሱስ እንደሚያዝ አያውቅም ነበር?
ኢየሱስ እንደሚያዝ ያውቅ ነበር፡፡ ይህንን ደግሞ በብዙ ቦታዎች ላይ ተናግሯል፡፡ ለአብነት ያህል ተከታዮቹን ጥቅሶች ይመልከቱ፡- (ማቴዎስ 12፡38-40፣ 16፡21፣ 17፡22-23፣ 20፡18-10፣ 21፡33-46፣ 26፡21-32፣ 26፡36-40፣ 26፡61-62፣ ማርቆስ 8፡31፣ 9፡9፣ 9፡30-31፣ 10፡33-34፣ 10፡45፣ 12፡1-12 14፡18-28፣ 14፡32-40፣ ሉቃስ 9፡22፣ 11፡29-30፣ 13፡32-33፣ 20፡9-19፣ 22፡15-20፣ 22፡39-46፣ ዮሐንስ 3፡13-14፣ 8፡28፣ 12፡32-34)፡፡ ኢየሱስ በነዚህ ቦታዎች ሁሉ ላይ ስለ ሞቱ ተናግሮ ሳለ በዚህ በአንድ ጥቅስ ውስጥ ሞቱን ሳይጠቅስ ከእርገቱ በኋላ አይሁድ ፈልገው እንደማያገኙት መናገሩ ላለመሞቱ ማስረጃ ሊሆን የሚችለው እንዴት ሆኖ ነው? የአሕመዲን አዕምሮ ኢየሱስ እንዳልተሰቀለ በሚያስተምረው የክህደት ንፅረተ ዓለም ስለታወረ ለማስረጃዎች ሁሉ ዝግ ነው፡፡ ኢየሱስ ስለ ስቅለቱ የተናገረባቸውን እነዚህን ሁሉ ጥቅሶች ካነበበ በኋላ ስለ እርገቱ ብቻ የተናገረበትን አንድ ወይም ሁለት ጥቅሶች በመጥቀስ ሞቱን ለመካድ የሚሞክር ሰው በቃላት በማይገለፅ የክህደትና የጨለማ ዓለም ውስጥ መኖሩ እርግጥ ነው፡፡