የብሉይ ኪዳን ነቢያት በፍርድ ቀን ፈራጅ ኢየሱስ መሆኑን ካላስተማሩ ዳኛው ኢየሱስ ሆኖ ሲያገኙት ምን ይመስላቸዋል?

 


15. ከኢየሱስ በፊት የነበሩት ነብያት አምላክ አንድ መሆኑን ፣ ብቸኛና ኃያል መሆኑን ሰብከዋል፤ ሕዝቡም ተቀብሎ አምኗል፡፡ ምእመናን ደግሞ አምላክ በትንሣኤ እለት ለፍርድ እንደሚመጣ ተምረው ተቀብለዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም አምላክ እግዚአብሔር እንደሚፈርድ በመዝሙር 75፥2 ላይ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- “ፍርዱ የሚሰጥበት ጊዜ ወስኛለሁ፤ በዚያን ጊዜ በቅንነት እፈርዳለሁ” እንዲሁም በመዝሙር 75፥7 ላይ ፡- “በአንዱ ላይ የሚፈርድ ሌላውን ነጻ የሚያወጣ ቅን ፈራጅ እግዚአብሔር ነው፡፡” ሲል ይገልጻል፡፡ ስለዚህ እርሱ እንደሚፈርድ አምነው ተቀብለውታል፡፡ በአዲስ ኪዳን ግን ኢየሱስ የተባለ “የአምላክ ልጅ” መኖሩንና እርሱም እንደሚፈርድ ወዘተ. ጳውሎስ አስተምሯል፡፡ ታዲያ ነገ በትንሣኤ ከኢየሱስ በፊት የነበሩት አማኞች የአምላክን ፍርድ ለማየት ሲጠባበቁ ዳኛው ሌላና ኢየሱስ የተባለ ሰው ሆኖ ሲያገኙት ምን ይመስላቸዋል? ያስተማሩዋቸውን ነብያት “ሐሰተኛ” ሊሉ ነውን? ኢየሱስ በማን አስተምሮት ነው የሚፈርድባቸው?

ጠያቂው የኢየሱስን የእግዚአብሔር ልጅነት እና ፈራጅነት ሐዋርያው ጳውሎስ ብቻ ያስተማረ በማስመሰል ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ልጅነቱንም ሆነ ፈራጅነቱን ኢየሱስ ራሱና ሌሎች ደቀ መዛሙርቱ በተደጋጋሚ በአፅንዖት አስተምረዋል (ስለ ልጅነቱ፡ ማቴዎስ 14፥33፣ 16፡16፣ 16፡27፣ 26፡63-64፣ 27፡43፣ ማርቆስ 1፡1፣ 9፡7-9፣ 12፡6፣ 14:61-62፣ 15፡39፣ ሉቃስ 1፡35፣ 4፡41፣ 8፡28፣ ዮሐንስ 1፡34፣ 1፡50፣ 3፡18፣ 5፡25፣ 6፡40፣ 6፡69፣ 10፡36፣ 11፡4፣ 11፡27፣ 17፡1-2፣ 19፡7፣ 20፡31፣ 1ዮሐንስ 3፡9፣ 4፣15፣ 5፡5፣ 5፡10-13፣ 5፡20፣ 2ዮሐንስ 1፡3፡፡ ስለ ፈራጅነቱ፡ ማቴዎስ 16፡27፣ 25፡31-32፣ ማርቆስ 16፡62፣ ዮሐንስ 5፡27)፡፡

መገለጥ ርምደታዊ (Progressive) እንደመሆኑ ከብሉይ ኪዳን ይልቅ በአዲስ ኪዳን ውስጥ እግዚአብሔር ራሱን በሙላት ገልጧል፡፡ በዘመነ ብሉይ የእግዚአብሔር ሥላሴነት ለቅዱሳን ነቢያት ግልፅ ቢሆንም ለአንድነቱ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ ብሉይ ኪዳን ይበልጥ አጽንኦት በመስጠት የሚናገረው ስለ እግዚአብሔር አንድነት ቢሆንም በአንድነቱ ውስጥ ብዝኃነት መኖሩንም የሚናገሩ የተለያዩ ጥቅሶች አሉ፡፡ ለምሳሌ በእብራይስጥ ኤሎሂም የሚለው የእግዚአብሔር መጠርያ ነጠላ ቁጥርን ሳይሆን ብዙ ቁጥርን የሚያመለክት ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ስለ እግዚአብሔር አንድነት ከሚናገሩ ጥቅሶች ሁሉ ዋነኛው ዘዳ. 6፡4-5 ላይ የሚገኘው ሲሆን አይሁዶች ይህንን “ሼማ” በማለት ይጠሩታል፡፡ ይህ ጥቅስ በእብራይስጥ ቋንቋ ሲነበብ “ሼማ ይስራኤል ያሕዌ ኤሎሂኑ ያሕዌ ኢኻድ” ይላል፡፡ የእግዚአብሔርን አንድነት አፅንኦት በመስጠት የሚናገር ቢሆንም ነገር ግን በአንድነቱ ውስጥ ብዝኃነት መኖሩንም ይጠቁማል፡፡ እብራይስጥ “አንድ” ለሚለው ቃል “ያኽድ” እና “ኢኻድ” የሚሉ ሁለት ቃላት አሉት፡፡ “ያኽድ” ነጠላ አንድነትን የሚያመለክት ሲሆን “ኢኻድ” የሚለው ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በአመዛኙ የብዙ አንድነትን ለማመልከት ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ በዚህ ቦታ ላይ የተጠቀሰው ቃል የብዙ አንድነትን የሚያመለክተው “ኢኻድ” የሚለው ቃል ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የባልና የሚስትን አንድነት ለመግለፅ ይህንኑ ቃል ተጠቅሟል (ዘፍ. 2፡24)፡፡

  • የእግዚአብሔርን ሥላሴነት የሚናገሩ ጥቂት የማይባሉ የብሉይ ኪዳን ክፍሎች አሉ (ዘፍ 1፡26፣ 3፡22፣ 11፡7፣ ኢሳ 6፡8)፡፡
  • አንዱ የእግዚአብሔር አካል ለሌላው ሲናገር በተለያዩ ትንቢታዊ ጥቅሶች ውስጥ እናያለን፡፡ ለምሳሌ፡- ኢሳ 48፡16፣ ዘካ 2፡7-11
  • የሥላሴን ጽንሰ ሐሳብ ለመረዳት የአዲስ ኪዳን እገዛ ያስፈልገናል ምክንያቱ ደግሞ ብሉይ ኪዳን በአዲስ ኪዳን ሙሉ ስለሚሆን ነው፡፡

አሕመዲን የጠቀሷቸው በብሉይ ኪዳን ውስጥ የሚገኙ የእግዚአብሔርን ፈራጅነት የሚናገሩ ጥቅሶች ከሥላሴ አካላት መካከል አብን ብቻ ለይተው እንደሚያመለክቱ ወይም ደግሞ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስን ያገለሉ ስለመሆናቸው ማስረጃ አልሰጡም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር” ሲል አንዱን ግፃዌ መለኮት ወይም ከሥላሴ አካላት መካከል አንዱን ሊያመለክት ይችላል፡፡ በተደጋጋሚ እንደታየው አሕመዲን እስላማዊ መነጽራቸው መጽሐፍ ቅዱስን በትክክል እንዳይረዱ ደንቃራ ሆኖባቸዋል፡፡

 

 

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች የተሰጠ መልስ ማውጫ