አምላክ ፍትሃዊ ከሆነ “እኛን ሊያድን ኢየሱስን መስዋዕት አደረገው” የሚለው አባባል የፍትህን ፅንሰ ሀሳብ አይፃረርምን?
34. አምላክ ፍትሃዊ ነው፡፡ ፍትህ ደግሞ በአንዱ ኃጢአት ሌላውን ያለመቅጣትን ይጠይቃል፡፡ “አምላክ እኛን ሊያድን ኢየሱስን መስዋዕት አደረገው” የሚለው አባባል የፍትህን ፅንሰ ሀሳብ አይፃረርምን? አንድ ሰው ሌላውን ገድሎ ወይም ወንጀል ፈፅሞ ፍርድ ቤት ቢቀርብና ዳኛው እርሱን በቅጣት ፋንታ ልጃቸውን ቢቀጡ ፍትሃዊነት ይሆናልን?
ከላይ የተጠቀሰውን ዓይነት ጥያቄ የሚጠይቅ ሙስሊም ስድስት መሠረታዊ እውነታዎችን ዘንግቷል
I. ሰዎችን በመስዋዕት አማካይነት ከኃጢአታቸው ማንፃት በአዲስ ኪዳን የተጀመረ ሥርኣት አለመሆኑን
በዘመነ ብሉይ ሰዎች እንስሳትን በመሰዋት ኃጢአታቸው ይሸፈንላቸው ነበር፡፡ እግዚአብሔር ለሙሴ የመስዋዕትን ሕግ ከመስጠቱ በፊት ይህንን ሥርኣት ሲፈፅሙ የነበሩ ቅዱሳን ሰዎች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ያህል አቤል (ዘፍጥረት 4፡3-5)፣ ኢዮብ (መጽሐፈ ኢዮብ 1፡5) ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ የፋሲካው በግ መስዋዕትም ቢሆን እግዚአብሔር በሌዋውያን አማካይነት የሚፈፀመውን የመስዋዕት ሥርኣት ለሙሴ ከመስጠቱ በፊት የተደረገ በመሆኑ ከሕጉ በፊት እንደተፈፀመ ሥርኣት ይቆጠራል (ዘጸአት 12፡1-30)፡፡ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር በእንስሳት መስዋዕት አማካይነት ሕዝቡን የማንፃት ሥርኣት ሰጠ (ዘሌዋውያን 6፡1-7፣ 16፡15-22)፡፡ ይህ ሥርኣት ከክርስቶስ እርገት በኋላ ለተወሰኑ ዓመታት ቢቆይም በ70 ዓ.ም. ከቤተ መቅደሱ መፍረስ ጋር ተያይዞ ቀርቷል፡፡ ነቢዩ ኤርምያስ እግዚአብሔር አዲስ ቃል ኪዳን ከሕዝቡ ጋር እንደሚያደርግ ተንብዮ ነበር (ኤርምያስ 31፡31-34)፡፡
II. ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መስዋዕትነት አስቀድሞ በብሉይ ኪዳን ትንቢት መነገሩን
መሲሁ መስዋዕት ሆኖ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው እንደሚዋጃቸው አስቀድሞ የተነገረ በመሆኑ ሐዋርያት ወይም ከእነርሱ በኋላ የተነሱት ክርስቲያኖች የፈጠሩት ትምህርት አይደለም (ኢሳይያስ 53)፡፡
III. ክርስቶስ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ለመዋጀት በገዛ ፈቃዱ መምጣቱን
ጌታችን ወደ ምድር የመጣው እና ራሱን ስለ እኛ ቤዛ ያደረገው በገዛ ፈቃዱ እንጂ በማንም አስገዳጅነት አልነበረም (ዮሐንስ 10፡11፣ 10፡15፣ 10፡17-18 15፡13፣ ማርቆስ 10፡45)፡፡ ራስን ስለሌላው መስዋዕት ማድረግ ደግሞ የሚያስመሰግን እንጂ የሚያስወቅስ ተግባር አይደለም፡፡ የሚከተሉትን ተግባራት የፈፀሙ ሰዎች መጥፎ ሥራ እንደሠሩ መናገር ይቻል ይሆን?:-
- የባንክ ሀራጅ የወጣበትን የወዳጁን ቤት እዳውን በመክፈል የታደገ ሰው፤
- የመኪናው ፍሬን በመበላሸቱ ሕዝቡን ከእልቂት ለመታደግ በራሱ አቅጣጫ ከብረት ምሰሶ ጋር አጋጭቶ በማቆም የሞተ ሾፌር፤
- ሕፃን ልጅ መሃል አስፓልት ላይ በመኪና ተገጭታ ከመሞቷ በፊት ገፍትሮ በማትረፍ የሞተ ሰው፤
- ጓደኞቹን ለማትረፍ በፈንጂ ላይ ተራምዶ የሞተ ወታደር፤
- በከባድ በሽታ የታመመ ሰው ስታክም ተበክላ ሕይወቷን ያጣች ዶክተር፤
- ጠቅላይ ሚኒስቴር እንዳይገደል በመሸፈን በጥይት ተመትቶ የሞተ አጃቢ፤
እነዚህን ድርጊቶች በፈቃደኝነት የሚፈፅሙ ወገኖች እንደ ጀግና ይወደሳሉ እንጂ አይወቀሱም፡፡ ጌታችንም እኛ ልንከፍለው የማንችለውን የኃጢአት እዳችንን በመክፈል ነፃ አውጥቶናል፡፡ እርሱ እዳችንን ባይከፍልልን ኖሮ የመዳን ተስፋ አልነበረንም፡፡ የእርሱ ተግባር እኛን ለማትረፍ በፈቃደኝነት የተፈፀመ መስዋዕትነት በመሆኑ የፍትህ ጥያቄን የሚያስነሳ አይደለም፡፡
IV. የሌላውን ሰው ዕዳ መክፈል ፍትሃዊ መሆኑን
በሰው የፍትህ ሥርአት ውስጥ አንዱ ስለሌላው የማይቀጣባቸው ብዙ ጉዳዮች ቢኖሩም ነገር ግን አንዱ ለሌላው የሚቀጣባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው ያለበትን የገንዘብ ዕዳ ራሱ መክፈል የማይችል ከሆነ ሌላ ሰው በፈቃደኝነት በመክፈል ከቅጣት ሊያተርፈው ይችላል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከጌታው ለሸሸው እና ባለ ዕዳ ለሆነው ኦናሲሞስ ለተሰኘ ባርያ ይህንን አድርጎ ነበር (ፊልሞና 1፡17-19)፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ኃጢአት ሙስሊሞች እንደሚሉት “ወንጀል” ሳይሆን መከፈል ያለበት እዳ ነው (ማቴዎስ 18፡21-35፣ ሉቃስ 7፡36-50፣ ቆላስይስ 2፡13-15)፡፡ እዳን በመክፈል ባለ እዳውን ከቅጣት ማትረፍ በምድራዊው የሰው ፍትህ ሥርአት ውስጥ እንኳ ተቀባይነት ያለው ተግባር ነው፡፡
V. እግዚአብሔር ሉኣላዊ ሥልጣን እንዳለው
ሰዎች የአንዱን ኃጢአት በራሳቸውም ሆነ በሌላ ሰው ላይ የማኖር መብትም፣ ስልጣንም ሆነ ችሎታ የላቸውም፡፡ የእግዚአብሔር ሥልጣን ግን ሉኣላዊ በመሆኑ የገዛ እዳችንን ወደ ራሱ በማስተላለፍ ሊከፍልልን ይችላል፡፡ ከሥላሴ አካላት መካከል አንዱ የሆነው ወልድ ወደ ምድር በመምጣት በኛ ምትክ ሆኖ የኃጢአት እዳችንን በመክፈል ነፃ አወጣን (2ቆሮንቶስ 5፡17-21፣ ዮሐንስ 1፡29፣ 10፡14-18፣ ገላቲያ 2፡20፣ ቆላስይስ 1፡13-23፣ 2፡13-15፣ ራዕይ 1፡5-6)፡፡ እግዚአብሔር ይህንን ማድረግ ከወደደ ስጦታውን በታላቅ አክብሮትና ምስጋና ከመቀበል ውጪ የእርሱን ሉኣላዊነት እንቃወም ዘንድ እኛ ማን ነን?
VI. በመስዋዕት መቤዠት በክርስትና ብቻ ሳይሆን በእስልምና ሃይማኖትም ውስጥ የሚገኝ መሆኑን
በብሉይ ኪዳን ውስጥ የሚገኘውን የመስዋዕት ሥርኣትም ሆነ የኢየሱስ ክርስቶስን ቤዛነት በመቃወም የሚጽፉና የሚሰብኩ ሙስሊሞች በገዛ መጻሕፍታቸው ውስጥ ተመሳሳይ ትምህርቶች ሰፍረው መገኘታቸውን አለማወቃቸው የሚያስገርም ነው፡፡ አላህ አብርሃምን ልጁን እንዲሰዋ እንዳዘዘው ቁርኣን ናገራል፡፡ አብርሃም የታዘዘውን በማድረግ ፈተናውን ማለፉን ካረጋገጠ በኋላ ልጁ እንዳይገደል እንዴት እንዳተረፈው ሲናገር፡- “በታላቅ ዕርድም (መስዋዕት) ተቤዠነው” ይላል (ሱራ 37፡106)፡፡ በመስዋዕት መቤዠት ለዘመናችን ሙስሊም ሰባኪያን እንግዳ ቢሆንም ላለፉት 14 ክፍለ ዘመናት በቁርኣን ውስጥ ተጽፎ የተቀመጠ ትምህርት ነው፡፡ በሌላ ቦታ ላይ ቁርኣን መስዋዕትን የማቅረብ ትዕዛዝ ከሙስሊሞች በፊት በነበሩት ሕዝቦች ሁሉ ላይ እንደተደነገገ ይናገራል፡- “ለሕዝብም ሁሉ (ወደ አላህ) መስዋዕት ማቅረብን ደነገግን፡፡” (22፡34)፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ እንዲህ ዓይነት ትምህርት ባለመሰጠቱ ይህ ጥቅስ “ለሕዝብም ሁሉ” በማለት ክርስቲያኖችን በማካተት የተሳሳተ መረጃ ቢያስተላልፍም ነገር ግን መስዋዕት ማቅረብ ከአምላክ የተሰጠ ትዕዛዝ መሆኑን በመመስከር የዘመናችን ሙስሊሞች የሚያስተምሩትን ትምህርት ውድቅ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሙስሊሞች ወደ ገነት መግባት ይችሉ ዘንድ አላህ የእነርሱን ኃጢአት በአይሁድ እና በክርስቲያኖች ላይ በማስቀመጥ ወደ ገሃነም እንደሚልካቸው እስላማዊ ሐዲሳት በብዙ ቦታዎች ላይ ያስተምራሉ፡- “አቡ ቡርዳ አባቱን ዋቢ በማድረግ እንዳስተላለፈው የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) እንዲህ ብለዋል፡- ከሙስሊም አንድም አይሞትም አላህ በእርሱ ፋንታ አይሁዳዊ ወይም ክርስቲያን በገሃነም ውስጥ የሚጥል ቢሆን እንጂ፡፡”[8] በሌሎች ዘገባዎች ደግሞ በእለተ ትንሣኤ ሙስሊሞች ተራራ የሚያካክሉ ኃጢአቶቻቸውን ተሸክመው እንደሚመጡና አላህ ይቅር ብሏቸው በእነርሱ ፋንታ አይሁድ እና ክርስቲያኖችን ወደ ገሃነም እንደሚልክ ተጽፏል፡፡[9] ሙስሊሞች በኢየሱስ ቤዛነት ባያምኑም የእርሱ የሥጋ ዘመዶች በሆኑት በአይሁዳውያንና የእርሱ ተከታዮች በሆኑት በክርስቲያኖች ቤዛነት ያምናሉ ማለት ነው፡፡ ፍፅምና የሌላቸው አይሁድ እና ክርስቲያኖች የኃጢአት እዳቸውን መክፈል እንደሚችሉ ለማመን ያልከበዳቸው ሙስሊም ወገኖቻችን ንፁህና ቅዱስ የሆነው የእግዚአብሔር ልጅ የኃጢአታቸውን ዕዳ የመክፈል ብቃት እንዳለው ማመን ለምን ይሆን የከበዳቸው?
እንዲህ ዓይነት ትምህርቶችን የተሸከሙ መጻሕፍትን ታቅፈው ክርስትናን ለሚተቹ አሕመዲንን ለመሳሰሉት ሰባኪያን አጸፋ መመለስ አስፈላጊ በመሆኑ እንዲህ በማለት እንጠይቃቸዋለን፡- “አምላክ እኛን ሊያድን አይሁድና ክርስቲያኖችን መስዋዕት ያደርጋል” የሚለው የሙስሊሞች ተስፋ የፍትህን ፅንሰ ሀሳብ አይፃረርምን? አሕመዲንና መሰሎቻቸው መልስ እንዲሰጡን እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን መልስ እንደሌላቸው እናውቃለን፡፡