የአል-መሲህ መሰቀል ከአምላክ ፍትህ ከእዝነቱ ከኃይሉና ከጥበቡ ጋር የሚጣጣም ነው ወይ?

 


36. አብያተ ክርስቲያናት በሚያምኑበት መንገድ የአል-መሲህ መሰቀል ከአምላክ ፍትህ ከእዝነቱ ከኃይሉና ከጥበቡ ጋር የሚጣጣም ነው ወይ?

ኢየሱስ መሰቀሉ የእግዚአብሔር ፍትህ ከፍቅሩ ጋር ሳይጣረስ ይቅር እንዲለን አስችሎታል፡፡ እስልምናን ጨምሮ ከክርስትና ውጪ የሚገኝ የትኛውም ሃይማኖት የፈጣሪ ምህረት ፍትሃዊ ባሕርዩን ሳይጣረስ ለሰው ልጆች የኃጢአት ይቅርታ ሊገኝ የሚችልበትን መንገድ ማቅረብ አይችልም፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር ስላዘነልን እንዳንጠፋ ሲል አንድያ ልጁ በቅዱስ ደሙ ይዋጀን ዘንድ ላከልን፡-

“ገና ደካሞች ሳለን ክርስቶስ ዘመኑ ሲደርስ ስለ ኃጢአተኞች ሞቶአልና፡፡ ስለ ጻድቅ የሚሞት በጭንቅ ይገኛልና፤ ስለ ቸር ሰው ግን ሊሞት እንኳ የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል፡፡” (ሮሜ 5፡6-8)፡፡

በሐዋርያት ዘመን እንኳ የመስቀሉን መልዕክት እንደ ድካም እና እንደ ሞኝነት የሚቆጥሩ ሰነፎች ነበሩ፡፡ የሚጠፉት ሰዎች እንደ ድካም በሚቆጥሩት በዚህ ክስተት ውስጥ የሰው ልጆችን ሁሉ ኃጢአት ማስወገድ የሚችል ታላቅ የሆነ የእግዚአብሔር ኃይል ተገልጧል፡፡ ልበ-ዕውራን እንደ ሞኝነት በሚቆጥሩት በዚህ ክስተት ውስጥ የዓለም ጠቢባን ሁሉ ቢሰበሰቡ መድኃኒት ሊያገኙለት የማይችሉትን ወደ ዘለዓለም ሞት የሚወስደውን የኃጢአት በሽታ የሚፈውስ መድኃኒት ተገልጧል፡፡

“የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና፡፡ የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ ተብሎ ተጽፎአልና፡፡ ጥበበኛ የት አለ? ጻፊስ የት አለ? የዚች ዓለም መርማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን? በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች፥ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአልና፡፡ መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፥ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፥ ለተጠሩት ግን፥ አይሁድ ቢሆኑ የግሪክ ሰዎችም ቢሆኑ፥ የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው፡፡” (1ቆሮንቶስ 1፡18-24)