በአፈታሪክ ከሚወሩት ከነባከስ አፖሎ አዶኒስ ሆረስ በስተቀር ከኢየሱስ ጋር የሚነጻጸር አለ ወይ?

 


  1. በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በአፈታሪክ ከሚወሩት ከነባከስ አፖሎ አዶኒስ ሆረስና ከሌሎችም ጥንታውያን አማልክት በስተቀር ከኢየሱስ ጋር የሚነጻጸር አለ ወይ?

እነዚህ የአረማውያን አማልክት ከኢየሱስ ጋር እንደሚያመሳስላቸው የሚነገርላቸው አንዱ ከድንግል ተወልደዋል የመባላቸው ጉዳይ ነው፡፡ አሕመዲን ጀበል የኢየሱስ ታሪክ ከእነርሱ ጋር “መመሳሰሉ” ጥያቄ ከፈጠረባቸው ዒሳ ከድንግል መወለዱ በቁርኣን ውስጥ ስለተነገረ በራሳቸውም ሃይማኖት ላይ ጥያቄ አላቸው ማለት ነው፡፡ ሰውየው ክርስትናን ለማጣጣል ሲታገሉ የራሳቸውን ሃይማኖት ውድቅ አድርገውት አረፉ!

ኢየሱስን ከአረማውያን አማልክት ጋር የማመሳሰል እንቅስቃሴ በአሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን በጀርመን ለዘብተኛ የሥነ መለኮት ሊቃውንት የተጀመረ ሲሆን እንቅስቃሴው ብዙም ሳይቆይ ከሽፏል፡፡ የዚህ እንቅስቃሴ መሠረቱ የጀመርመኖች የፀረ ሴማዊነት አስተሳሰብ በመሆኑ አይሁዳዊ ኢየሱስን “በአረማዊ ኢየሱስ” የመተካት እኩይ ዓላማን ያነገበ ነበር፡፡ ይህ አመለካከት በአሁኑ ወቅት በበይነ መረብ (ኢንተርኔት) ላይ በሚሰብኩ አምላክ የለሾች (Internet Infidels) መካከል በስፋት የሚለፈፍ ሲሆን በታሪክም ሆነ በሥነ መለኮት ሊቃውንት መካከል ምንም ዓይነት ተቀባይነት የለውም፡፡ የዚህ ምክንያቱ ሁለት ነው፡፡ የመጀመርያው እነዚህ አፈ ታሪኮች ከክርስትና በኋላ የተፈጠሩ መሆናቸው የተረጋገጠና ከክርስትና በፊት ስለመኖራቸው ምንም ማስረጃ የሌላቸው መሆኑ ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ኢየሱስን ከመጀመርያው ክፍለ ዘመን የአይሁድ እምነት በማውጣት በእነዚህ የአረማውያን አፈታሪኮች አውድ ማየት ትርጉም የሚሰጥ ባለመሆኑ ነው፡፡ ጠያቂው ይህንን ርዕስ ወደ መድረኩ ማምጣታቸው በተዘዋዋሪ የራሳቸውን ሃይማኖት ውድቅ ከማድረግ ባለፈ መሠረት የለሽ ወሬ መሆኑ ተረጋግጦ ከአንድ ምዕተ ዓመት በፊት በሊቃውንት የተጣለውን ሙግት መጠቀማቸው ዕውቀታቸውንና አስተማማኝ መረጃ የመስጠት ብቃታቸውን እንድንጠራጠር ያደርገናል፡፡