ሮማውያን ባለስልጣናት በኢየሱስ (ዒሳ) ላይ የነበራቸው ቅራኔ ምንድነው? «የቄሳርን ለቄሳር” ብሎ ካስተማረ እርሱን የመሰለ ሕግ አክባሪና ታዛዥ ዜጋ ለምን ያጣሉ?
-
ሮማውያን ባለስልጣናት በኢየሱስ (ዒሳ) ላይ የነበራቸው ቅራኔ ምንድነው? ለበላይ ስልጣናቸው ተቀናቃኝ አልነበሩም፤ ለመሪ ግለሰቦችና ለቤተሰቦቻቸው ጥቅም ብዙ ነገርን ሰርተዋል፡፡ ደቀ መዛሙርቱም «የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር» እንዲሰጡ አስተምረዋል፤ ሰላምተኛ ሰባኪ የነበሩ ሲሆን በሃገር ውስጥ ህግና ስርዐትን ለማስጠበቅ ለሮማውያን ባለስልጣኖች ከፍተኛ አጋዥም ነበሩ፡፡ ታድያ ይህን ሰው ሰቅለው እርሱን የመሰለ ሕግ አክባሪና ታዛዥ ዜጋ ለምን ያጣሉ?
ኢየሱስ በእርግጥ እጅግ ሰላማዊና ሕግ አክባሪ ነበር ነገር ግን ሮማውያን ባለ ሥልጣናት ይህንን ተረድተዋል ወይ የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡ ኢየሱስን በተመለከተ በሮማውያን ባለ ሥልጣናት መካከል የአቋም ልዩነት ነበር፡፡ ጲላጦስ ከመረመረው በኋላ ንፅህናውን መስክሯል፡፡ ነገር ግን ታላቁ ሄሮድስ ኢየሱስን በልጅነቱ የመግደል ሙከራ በማድረጉ ምክንያት ዮሴፍና ማርያም ወደ ግብፅ ይዘውት ለመሰደድ ተገደዋል፡፡ ሙከራው ያልተሳካለት ሄሮድስም ዕድሜያቸው ከሁለት ዓመት በታች የሆኑትን የቤተ ልሔም ህፃናትን ጨፍጭፏል (ማቴዎስ 2)፡፡ ንጉሡ ይህንን እርምጃ የወሰደበት ምክንያት አይሁድ እንደሚወለድ ይጠብቁ የነበሩት መሲህ ሥልጣኑን የሚቀናቀን ስለመሰለው ነበር፡፡ ልጁ ሄሮድስ አንቲጳስም ሊገድለው ይፈልግ ነበር (ሉቃስ 13፡31-33)፡፡ መጥምቁ ዮሐንስንም ያስገደለው እርሱ ነበር (ማቴዎስ 14፡3-12)፡፡ ኢየሱስ ሰላማዊ ሰባኪና ሰዎች ተገቢውን ግብር ለሮማውያን እንዲከፍሉ ያስተማረ ቢሆንም ሮማውያን እርሱን እንደ ሥርአት አስከባሪ በመቁጠር መንከባከባቸው የማይመስል ነው፡፡ ኢየሱስም ደግሞ ከእነርሱ ጋር በመተባበር የፖለቲካ አጀንዳቸውን ስለማራመዱ ምንም ማስረጃ የለም፡፡ ጲላጦስ ንፅህናውን ቢያረጋግጥም በበዓል ወቅት በእርሱ ምክንያት አይሁድ ሊያስነሱት የነበረውን ሁከት በመፍራት እንዲሞት አሳልፎ ቢሰጠው አያስገርምም፡፡ ደግሞም የኢየሱስ ሞት የእግዚአብሔር ዕቅድ በመሆኑ በምንም መንገድ ሊቀር የሚችል አልነበረም፡፡