የተፈረደበት ሰው በመስቀል ላይ ለመሞት ጥቂት ቀናት ይወስዳል፡፡ ታድያ በኢየሱስ ሁኔታ ለምን ጥቂት ሰዓታትን ብቻ ወሰደ?

 


  1. የተፈረደበት ሰው በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እስኪሞት ድረስ ምን ያህል ጊዜ ወሰደ አስተማማኝ በሆኑ ታሪካዊ ምንጮች መሠረት (ቻምበርስ ኢንሳይክሎፒዲያ 1950 ስለመስቀሉ የተጻፈውን አንቀጽ ይመልከቱ) በመስቀል ላይ እንዲሞት የተፈረደበት ሰው ለመሞት ጥቂት ቀናት ይወስዳል፡፡ ታድያ ይህ ድርጊት ጥቂት ቀናትን መጠየቁ የተለመደ ሁኔታ ሆኖ ሳለ በኢየሱስ ሁኔታ ለምን ጥቂት ሰዓታትን ብቻ ወሰደ?

ሙሉ ከሆነ የሮማውያን ስቅለት በሕይወት የተረፈ አንድም ሰው ስለመኖሩ በታሪክ አልተመዘገበም፡፡ ጆሲፈስ ፍላቪየስ (ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን) የተሰኘ ሮማዊ አይሁድ ጸሐፌ ታሪክ በዘገበው ታሪክ ውስጥ በመስቀል ላይ የተሰቀሉ ሦስት ጓደኞቹን ባለ ሥልጣናትን በማግባባት እንዴት ከመስቀል ላይ እንዲወርዱ እንዳደረጋቸው የሰፈረ ታሪክ እናገኛለን፡፡ ሰዎቹ ለአጭር ጊዜ ተሰቅለው ከወረዱ በኋላ በወቅቱ የነበረው ከፍተኛ ኅክምና ቢደረግላቸውም ነገር ግን ከሦስቱ ሁለቱ ወዲያውኑ ሲሞቱ አንዱ ብቻ ነበር በሕይወት መትረፍ የቻለው፡፡[11] ኢየሱስ ግን ለሦስት ሰዓታት ያህል ነበር በመስቀል ላይ የቆየው፡፡ ከመሰቀሉ በፊት በአይሁድ ተገርፏል፤ ብዙዎችን ለሞት ይዳርግ በነበረው የሮማውያን ግርፋት ውስጥ አልፏል፤ የእሾህ አክሊል በመድፋት በመቃ ተቀጥቅጧል፤ መስቀሉን ተሸክሞ ከፕራይቶርዮን እስከ ጎልጎታ ድረስ እንዲሄድ ተደርጓል፡፡ በዚህ ሁሉ ስቃይ ውስጥ አልፎ የሰውነቱን ክብደት በሙሉ በሚስማር በተቸነከሩት እጆቹና እግሮቹ ላይ ተሸክሞ ለሦስት ሰዓታት ያህል ወደ ላይ እና ወደ ታች እያለ መተንፈስ ነበረበት፡፡ በመጨረሻም መሞቱን ያዩት ወታደሮች ጎኑን በጦር ወግተውታል፡፡ እንግዲህ አንድ ሰው ጀርባው እስኪከፈት ድረስ ተገርፎ፣ እጆችና እግሮቹ ተቸንክረው፣ በመስቀል ተሰቅሎ፣ ጎኑ በጦር ተወግቶ፣ ከመስቀል ላይ ወርዶ ደግሞ እንደ ሲሞንቶ በሚያጣብቅ 100 ፓውንድ ቅመም ቢታሸግ – በዚያ ውስጥ አልፎ በሕይወት መኖር መቻል ከትንሳኤ ጋር የሚተካከል ተዓምር የሚጠይቅ ነው!

 

ሁለቱ ደቀመዛሙርቶች እያሉ እርሱ ለምን ተሰቅሎ “ሞተ”? ምድርን በሙሉ ለሦስት ሰዓት የሸፈነው ጨለማ ጉዳይስ? (ማቴዎስ 27፡45፣ ማርቆስ 15፡33 ሉቃስ፣ 23፡44)፡፡

ጠያቂው “ሁለቱ ደቀ መዛሙርቶች” ሲሉ ምን ለማለት እንደፈለጉ ግልፅ አይደለም፡፡ ምድርን ለሦስት ሰዓታት የሸፈነው ጨለማ ከአዲስ ኪዳን ውጪ በሚገኙት የታሪክ መዛግብት የተረጋገጠ ነው፡፡ ይህን ጉዳይ የሚጠቅስ አስደናቂ የታሪክ መረጃ በ55 ዓ.ም አካባቢ እንደተጻፈ ምሑራን ይናገራሉ፡፡ ታሉስ የተባለ ሮማዊ ጸሐፌ ታሪክ በክርስቶስ ስቅለት ወቅት በምድር ላይ ስለወደቀው ጨለማ ጽፎ የነበረ ሲሆን ነገር ግን በእርሱ የተጻፈው ቀዳሚ ሰነድ በመጥፋቱ የተነሳ ያለን መረጃ ጁሊየስ አፍሪካኑስ የተባለ ክርስቲያን የታሪክ ጸሐፊ (160-240 ዓ.ም) የእርሱን ጽሑፍ በመጥቀስ የጻፈው ነው፡፡ አፍሪካኑስ እንዲህ በማለት ጽፏል፡- “በሦስተኛው የትረካ (መጽሐፉ) ታሉስ ይህንን ጨለማ የፀሐይ ግርዶሽ በማለት ይጠራዋል፤ ይህ ለኔ ስህተት መስሎ ይታየኛል፡፡”

ጁሊየስ አፍሪካኑስ የታሉስን ጽሑፍ የጠቀሰው ክርስቶስ የተሰቀለው ሙሉ ጨረቃ በምትታይበት በፋሲካ ዋዜማ በመሆኑና በሙሉ ጨረቃ ጊዜ ደግሞ የፀሐይ ግርዶሽ የማይከሰት በመሆኑ በክርስቶስ ስቅለት ወቅት በምድር ላይ የወደቀው ጨለማ የፀሐይ ግርዶሽ እንደነበረ ታሉስ በመጽሐፉ ውስጥ ማስፈሩ ትክክል እንዳልሆነ በሚገልጽበት ክፍል ነው፡፡[12]

ተሰቃዩን በሌላ ተሰቃይ የመለወጡ ወይም የመተካቱ አፈጻጸም በጨለማውና በትርምሱ ጊዜ በሐምራዊ መጎናጸፊያ ሽፋን ስር ተፈጽሞ ይሆናል ወይ?

አሕመዲን ሆይ፤ በግምት እና በመሰለኝ መናገር አይበቃዎትም ወይ? የመጎናፀፍያውን ቀለም እንኳ እስከመገመት ያደረስዎትን እስከ ዛሬ ድረስ ዓለም ያላወቀውን እርሶና ጥያቄዎቹን በማስኮረጅ ያገዙዎት ዶ/ር ሐሙዳ አብዱል ዓጢ ብቻ የሚያውቁትን ሚስጥራዊ መረጃ ሊነግሩን ይችላሉ ወይ? ተሰቃዩ በሌላ ተሰቃይ ተተክቷል የሚል ደካማ ግምት ሲያስቀምጡ ኢየሱስ እንዳልተሰቀለ ከሚናገረው የቁርኣን ጥቅስ ጋር እየተጋጩ እንደሆነ አስተውለዋል ወይ? ማስረጃ አልባ ግምትና ጥርጣሬስ አሳማኝ ሙግት ይሆናል ወይ?