ሥላሴ እና የኒቂያው ጉባኤ ጉዳይ!

 


  1. የሥነ-መለኮት ምሁር የሆኑት ዶክተር ፓውል እንዝ “ታሪካዊ ሥነ-መለኮት አመጣጡና ትንተናው” በሚለው መጽሐፋቸው ላይ “የኒቅያው (Nicea) ጉባኤ በ 325 ዓ.ም ታሪካዊውን አስተምህሮ-ሥላሴ አፀደቀ፡፡ በዚህም መሠረት ክርስቶስ ከአብ ጋር የባሕርይ እኩልነት ያለው መሆኑ ግንዛቤ አገኘ፡፡” ሲሉ ጽፈዋል፡፡ በኒቅያው ጉባኤ መሠረት “ክርስቶስ ከአብ ጋር የባሕሪይ እኩልነት ያለው መሆኑ” ግንዛቤ ሳያገኝ በፊት ቤተክርስቲያን የሥላሴን እምነት ሳይሆን የአንድን አምላክ ኃያልነትና ብቸኝነት ስታስተምር ተሳስታ ነበርን? ከኒቂያ ጉበኤ በፊት የነበሩት አማኞችና ሐዋርያትና የኢየሱስን በባህሪ ከአብ ጋር መስተካከል ሳይረዱትና ግንዛቤውን ሳያገኙ ቆይተው በኒቅያ ጉበኤ ተገኝተው በድምጽ ብልጫ የወሰኑት 300 ጳጳሳት ግንዛቤውን አገኙን? እምነት የሚጸድቀው እንደ ፖለቲካ ፓርቲ በጉባኤ ነው ወይስ በአምላክ ትእዛዝ?

የኒቅያ ጉባኤ የተደረገው አርዮስ የተሰኘ የአሌክሳንደርያ ሰው የኢየሱስን ዘለዓለማዊነትና ፍፁም አምላክነት ክዶ በማስተማር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የፈጠረውን ክፍፍል መርምሮ ለማውገዝ ነበር፡፡ ጉባኤው እንዲደረግ ያስገደደው የአርዮስ ትምህርት በቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ምዕመናን መካከል መስፋፋቱ እንጂ በሥላሴ አስተምህሮ ላይ ከዚያ ቀደም ጥርጥር ኖሮ አይደለም፡፡ በአንደኛውና በሁለተኛው ክፍለ ዘመን ሥላሴን የተመለከተ አስተምህሮ እንደ ችግር ሆኖ አልተዘከረም፡፡[1] የአርዮስ ትምህርት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክፍፍል ማስነሳቱና የጉባኤ ምክንያት መሆኑ በራሱ ትምህርቱ አዲስ እንደነበረና ከዚያ ቀደም ከነበረው የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ጋር የሚጣረስ መሆኑን ያመለክታል፡፡ አርዮስ የኢየሱስን ፈጣሪነት ያልካደ ሲሆን በአብ “የተፈጠረ ፈጣሪ” መሆኑን ነበር ያስተማረው፡፡ ይህንን ትምህርት እንዲቀበል የኖስቲሳውያን አስተምህሮ ተፅዕኖ አሳድሮበታል፡፡[2]

ዶ/ር ፓውል “ክርስቶስ ከአብ ጋር የባሕርይ እኩልነት ያለው መሆኑ ግንዛቤ አገኘ” ሲሉ ከዚያ ቀደም የማይታወቅ አዲስ ነገር መሆኑን ለመናገር ፈልገው አይደለም፡፡ ጠያቂው ጽሑፉን ቆርጠው ስለጠቀሱት ነው እንጂ ሙሉ ሐሳባቸው እንደርሱ አይልም፡፡ ጠያቂው ከጠቀሱት ክፍል አንድ መስመር ከፍ ብለው “አስተምህሮ-ሥላሴም አርዮስ ከተባለ ሰው ተግዳሮት ገጠመው” በማለት አስተምህሮተ ሥላሴ ቀደም ሲል የነበረ ትምህርት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ኢየሱስ ከአብ ጋር በባሕርዩ የተካከለ መሆኑና የሥላሴ አስተምህሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተደጋጋሚ የተጠቀሱ እውነታዎች ናቸው፡፡ ቅድመ ኒቅያ በነበሩት የአበው ጽሑፎች ውስጥም እናገኛለን፡፡ ይህንን በተመለከተ ጠያቂው የጠቀሱት መጽሐፍ ገፅ 19 “የሐዋርያት አባቶች ትምህርተ እግዚአብሔር” በሚለው ንዑስ ርዕስ ስር እዲህ ይላል፡- “በሥላሴዎች የማመኑ ጉዳይ የጸና ነው፤ ቀለሜንጦስ የሥላሴን እኩልነት ሲገልጥ፡- ‹‹እግዚአብሔር አብ ሕያው እንደሆነ ጌታ ኢየሱስም ሕያው ነው፤ መንፈስ ቅዱስም እንዲሁ፤ እነርሱ የምርጦቹ እምነትና ተስፋ ናቸው፤ የአጥናፈ ዓለሙ ፈጣሪና ጌታ፤ እግዚአብሔር ነው›› ብሏል፡፡”[3] ይህ የሮማው ቀለሜንጦስ መልዕክት የተጻፈው በ97 ዓ.ም. ነበር፡፡[4] “የሐዋርያት አባቶች ትምህርተ ክርስቶስ” በሚለው ንዑስ ርዕስ ስር ደግሞ እንዲህ ይላሉ፡- “ስለ ክርስቶስ ያሉት እምነቶች የፀኑና የሚደነቁ ናቸው፡፡ አግናጢዎስ የክርስቶስን መለኮትነት አስመልክቶ ታላቅ ቁምነገሮችን ተናግሯል፡፡ ወደ ሮምና ወደ ኤፌሶን በጻፋቸው ደብዳቤዎቹ ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ የኛ አምላክ›› ብሏል፡፡ በአማኞች ስለማደሩ ደግሞ ‹‹እርሱ ራሱ እንደ አምላካችን በእኛ ውስጥ ይኖር ዘንድ›› ካለ በኋላ ክርስቶስ የአብ ‹‹አሳብ››፣ ‹‹የእግዚአብሔር ጥበብ›› እንደሆነና ‹‹ዓለም ሳይፈጠር በፊት ከአብ ጋር እንደነበር›› እንዲሁም ‹‹ወልድነቱን›› ገልጧል፡፡ ፖሊካርፕ የተባለው ሌላ ጸሐፊ ደግሞ ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ የኛ አምላክና ጌታ›› ብሏል፡፡ ቀለሜንጦስ እንዲሁ ‹‹ኢየሱስ ከአብ የተላከ›› መሆኑን ገልጧል፡፡”[5] የኢግናጢዎስ መልዕክት በ100 ዓ.ም.[6] የፖሊካርፕ 108 ዓ.ም.[7] የተጻፉ ናቸው፡፡

እምነት የሚጸድቀው እግዚአብሔር በቃሉ ውስጥ ባስቀመጠው መልዕክት ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን መልዕክት ሰዎች ሊገባቸው በሚችል እና ለስህተት አስተማሪዎች ክፍተት ሊሰጥ በማይችል መልኩ በእምነት መግለጫ መልክ ለማስቀመጥ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ኦፊሴላዊ ጉባኤ ማድረጋቸው ስህተቱ ምኑ ላይ ነው?