ቀደምት ነቢያትም ሆኑ ኢየሱስ ስለ ሥላሴ አስተምረው ከነበረ ቤተክርስቲያን እንዴት ግልፅ የሆነ ግንዛቤ አልነበራትም?

 


3. የክርስቲያን ምሁራን ስለ ሥላሴ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፡፡ “አስተምህሮተ ሥላሴን አስመልክቶ የነበረው ዋነኛ ችግር ብሉይ ኪዳናዊው የአሃዳዊነት እምነት ነበር፡፡ ቤተክርስቲያን እግዚአብሔር አንድ ነው ከሚለው ትምህርቷ ጋር የክርስቶስን መለኮትነት እንዴት ነው የምትቀበለው? የሚለው ጥያቄ ዋና ነበር፡፡ቤተ ክርስቲያን ገና ከጅማሬዋ የሥላሴን አስተምህሮት በሚመለከት ግልጽ የሆነ ግንዛቤ አልነበራትም፡፡(ዶክተር ፓውል እንዝ ፣ ታሪካዊ ሥነ- መስኮት አመጣጡና ትንተናው ፣ ገጽ 33-34)

“ክርስቲያኖች እንደሚሉት ቀደምት ነቢያትም ሆኑ ኢየሱስ ስለ ሥላሴ አስተምረው ከነበረ ቤተክርስቲያን እንዴት ግልፅ የሆነ ግንዛቤ አልነበራትም? ክርስቲያኖች ቤተክርስቲያን “በኢየሱስና በሐዋርያት ነው የተመሠረተችው” ይሉ የለ? እነርሱም ግልጽ ግንዛቤ አልነበራቸውም ማለት ነው?

ቤተ ክርስቲያን ግልፅ የሆነውን ትምህርተ ሥላሴ ያገኘችው ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ የተጻፈው በነቢያትና በሐዋርያት ነው፡፡ እነርሱ ስለ ሥላሴ ግልፅ ግንዛቤ ባይኖራቸው ኖሮ ቤተ ክርስቲያን ትምህርቱን ከእነርሱ ማግኘት ባልቻለች ነበር፡፡ የመጀመርያዋ ቤተ ክርስቲያን እስከ ቆስጠንጢኖስ ዘመን ድረስ በስደት እና በመከራ ውስጥ ስላለፈች የተማከለ አስተዳደር አልነበራትም፡፡ ከዚህ የተነሳም ጥልቅ ትንታኔዎችን የሚሹ ሥነ መለኮታዊ ርዕሰ ጉዳዮችን እንደ ሃይማኖት መግለጫ ለማስቀመጥ የምትችልበት ሁኔታ ውስጥ አልነበረችም፡፡ በተጨማሪም በጊዜው በሥላሴ ላይ የተነሳ የጎላ ጥያቄ ባለመኖሩ በኒቅያ ጉባኤ እንደነበረው የሥላሴን አስተምህሮ በሥነ መለኮታዊ ቃላት በማዋቀር በእምነት መግለጫ መልክ ለማስቀመጥ የሚያስገድድ ሁኔታ አልተፈጠረም፡፡

“አስተምህሮተ ሥላሴን አስመልክቶ የነበረው ዋነኛ ችግር ብሉይ ኪዳናዊው የአሃዳዊነት እምነት ነበር፡፡” ይላሉ፡፡ ታዲያ ክርስቲያኖች ሊከራከሩ እንደሚሞክሩት በብሉይ ኪዳን ዘመን የሥላሴ አስተምህሮት ከነበረ እንዴት ብሉይ ኪዳናዊው አሀዳዊ እምነት ለሥላሴ እምነት ዋና ችግር ይሆናል?

የሥላሴን አስተምህሮ በብሉይ ኪዳን ላይ በመመስረት በተወሰነ መልኩ መግለፅ ቢቻልም በዘመኑ የነበሩት ሕዝቦች አስተምህሮውን በሙላት ለመገንዘብ የሚያስችላቸው አጥጋቢ መረጃ አልነበራቸውም፡፡ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ይበልጥ ጎልቶ የተቀመጠው የአብ ማንነት ሲሆን የወልድ እና የመንፈስ ቅዱስ ማንነት አጥጋቢ በሆነ ሁኔታ የተገለጠው በአዲስ ኪዳን ውስጥ ነው፡፡ መገለጥ ርምደታዊ እንደመሆኑ መጠን በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩት ሕዝቦች በተገለጠላቸው መጠን እግዚአብሔርን በማወቅ አምነው አልፈዋል፡፡ በአዲስ ኪዳን ደግሞ በብሉይ ኪዳን በመጠኑ የተገለጠው የሥላሴ ትምህርት በበቂ ሁኔታ ስለተቀመጠ ማመንና መቀበል ግድ ይለናል፡፡