አብ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ ሦስቱም እኩል ከሆኑ እንዴት ወልድ ላይ የሚነገረው ክፉ ይቅር ሲባል በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚነገር ይቅር አይባልም?

 


6. ማቴዎስ ወንጌል 12:32 “ማንም ሰው በሰው ልጅ ላይ የሚናገረው ክፉ ቃል ይቅር ይባላል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚናገረው ክፉ ቃል ግን በዚህም ሆነ በወዲያኛው ዓለም ይቅር አይባልም” ይላል፡፡ የሥላሴ አቀንቃኞች እንደሚሉት አብ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ ሦስቱም አምላክም እኩልም ከሆኑ እንዴት በሰው ልጅ (ወልድ) ላይ የሚነገረው ክፉ ይቅር ሲባል በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚባለው ንግግር ይቅርታ የሌለው ሆነ? ምኑ ላይ ነው ታድያ እኩልነታቸው?

ኢየሱስ በሥጋ የተገለጠ አምላክ እንደመሆኑ መጠን በምድር ላይ የተመላለሰው እንደ ሰው ነበር፡፡ በወቅቱ ሲመለከቱት የነበሩት ሰዎች ማንነቱን ሳይረዱት በመቅረት በእርሱ ላይ ቃል ቢናገሩ እንደ ማንኛውም ኃጢአት ይቅር ይባልላቸዋል፡፡ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መሳደብ (በዚህ አውድ ውስጥ አይሁድ እንዳደረጉት የመንፈስ ቅዱስን ሥራ እንደ ሰይጣን ሥራ በመቁጠር መቃወም) ይቅርታ የሌለው ኃጢአት ነው፡፡ ለዚህ ነው አሕመዲን ጀበልን የመሳሰሉት ሐያሲያን ዛሬ የሚናገሩት ቃል ነፍሳቸውን እንዳያስከፍላቸው መጠንቀቅ የሚገባቸው፡፡