በኢየሱስ የሚያምኑ ሰዎች ከኢየሱስ በላይ የሚያደርጉ ከሆነ ከአምላክ መብለጥ ይቻላል?

 


19. በዮሐንስ 14፡12 ላይ ኢየሱስ“እውነት እላችኋለሁ በኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ ይሰራ፤ እንዲያውም እኔ ወደ አብ ስለምሄድ፤ ከእነዚህም የሚበልጥ ያደርጋል”ብሏል፡፡ እንግዲህ ክርስቲያኖች “ኢየሱስን አምላክ ነው” እንደሚሉት ካሰብን በኢየሱስ የሚያም ሰው ከአምላክ በላይ ሥራን መስራት ሊችል ነው ማለት ነው፡፡ ታድያ ከአምላክ መብለጥ ተቻለ ማለት አይደል? ከአምላክ እንኳን ሊበልጥ ይቅርና ሊነፃፀር የሚችል ስራ ማን መስራት ይችላል?

ይህ ጥቅስ ስለ ክርስቶስ የምድር አገልግሎት የሚናገር ነው፡፡ ጌታችን በምድር ላይ በነበረበት ዘመን ብዙ ተዓምራትን አድርጓል፣ የምሥራቹንም ለብዙዎች አድርሷል፡፡ ነገር ግን ይህንን ኀላፊነትና ሥልጣን ለደቀ መዛሙርቱ በመስጠት ወደ ሰማይ አርጓል፡፡ “ከእነዚህም የሚበልጥ ያደርጋል” ሲል ሐዋርያት እርሱ በምድር ላይ በነበረበት ዘመን ከነበረው ተደራሽነት በላይ ተደራሽነት እንደሚኖራቸው ለመናገር እንጂ ከእርሱ የበለጠ ተዓምራትን የማድረግ ኃይል ይኖራቸዋል ለማለት አይደለም፡፡ ንግግሩም ብዛትን እንጂ ጥራትን የሚያመልክት አይደለም፡፡ ቀድሞውኑ ተዓምራትን እንዲያደርጉና ወንጌልን እንዲሰብኩ ሥልጣንን የሰጣቸው ራሱ ክርስቶስ ነው (ማቴዎስ 10፡1፣ ማርቆስ 6፡7፣ ሉቃስ 9፡1፣ 10፡19፣)፡፡ ይህንን የሚያደርጉት ደግሞ በስሙ እንጂ በራሳቸው ስም አይደለም (ማርቆስ 9፡39፣ ማርቆስ 16፡17፣ ሉቃስ 10፡17፣ የሐዋርያት ሥራ 3፡1-8፣ 3:16፣ 16፡16-18)፡፡ ስለዚህ ይህ የኢየሱስ ንግግር ሐዋርያት ከእርሱ እንደሚበልጡ ለማሰብ እንኳ የሚያስደፍር አይደለም፡፡

 

 

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች የተሰጠ መልስ ማውጫ