ዮሐንስ 6፡14 ላይ “ወደ ዓለም የሚመጣው ነብይ በእርግጥ ይህ ነው አሉ” ይህን የተናገሩ ሰዎች አማኞች ናቸው ወይስ ከሀዲ?
-
ዮሐንስ 6፡14 እንዲህ ይላል “ሰዎቹም ኢየሱስ ያደረገውን ተአምራዊ ምልክት ካዩ በኃላ ወደ ዓለም የሚመጣው ነብይ በእርግጥ ይህ ነው አሉ፡፡” ይህን የተናገሩ ሰዎች አማኞች ናቸው ወይስ ከሀዲ? ኢየሱስን ያዩት ሰዎች ነብይ ነው ብለው አመኑ፡፡ ልክ እንደ መስሊሞቹ ታዲያ ክርስቲያኖች ይህንን ለምን ተቃርነው አምላክ ነው አሉት?
ክርስቲያኖች ኢየሱስ ነቢይ መሆኑን አያምኑም ያለው ማነው? የአገራችን የሥነ መለኮት ሊቅ የነበሩት መሠረት ስብሐት ለአብ የኢየሱስን ነቢይነት በተመለከተ እንዲህ ብለዋል፡- “በመሲህነቱ ፍጹም ጠባቂ ታላቅ ነቢይና ዓይነተኛ ሊቀ ካህናት ዘለዓለማዊም ንጉሣችን የሆነ በአንዲት ተዋሕዶ ህላዌ የሚሰገድለት ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡”[1]
ኢየሱስ አምላክም ሰውም ከሆነ አምላክም ነቢይም መሆን የማይችልበት ምክንያት የለም፡፡ ነገር ግን የነቢይነት አገልግሎት ቢፈፅምም መለኮታዊ ወልደ እግዚአብሔር ነው፡፡ ጠያቂው ለክርስቲያናዊ አስተምህሮ ፍፁም እንግዳ መሆናቸው ግልፅ ነው፡፡