ኢየሱስ አስገራሚ ተአምር ሲያደርግ ኢየሱስ ሰው ብለው ካአመኑ እንዴት አምላክ ይሆናል?

 


2. ማቴዎስ 9፡8 “ሕዝቡም ይህን ባዩ ጊዜ በመደነቅ በፍርሃት ተሞልተው፥ እንደዚህ ያለ ሥልጣን ለሰው የሰጠውን እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡” ኢየሱስ አስገራሚ ተአምር ሲያደርግ ኢየሱስ ምንድነው ብለው አመኑ? ተዓምሩስ የማን ነው? አድራጊውስ ማን ነው? ጥቅሱ “እንደዚህ ያለ ሥልጣን ለሰው የሰጠውን እግዚአብሔርን አመሰገኑ” ይላል፡፡ ታድያ ክርስቲያኖች ለምን ኢየሱስን ተዓምራትን ሲያሳይ በስፍራው ከተገኙት አማኞች ተቃራኒ እምነት ያዙ?

በሌላ ጊዜ ደግሞ ይኸው ሕዝብ ኢየሱስ በብኤል ዜቡል ኃይል ተዓምራትን እንደሚያደርግ ተናግሮ ነበር (ሉቃስ 11፡15፣ ዮሐንስ 8፡48)፡፡ በአንድ ወቅት የገዛ ዘመዶቹ “አብዷል” ብለው ሊይዙት መጥተው ነበር (ማርቆስ 3፡21)፡፡ ቅዱስ ጳውሎስና በርናባስ ተዓምር ሲያደርጉ ያዩ ሕዝቦች “አማልክት ናቸው” በማለት ሊሰውላቸው ደርሰው ነበር (የሐዋርያት ሥራ 14፡11)፡፡ የጠያቂው አመክንዮ ትክክል ከሆነ የእነርሱን ድምዳሜ ልንቀበል ነው፡፡ ነገር ግን አስተምህሯችንን መመስረት ያለብን ክርስቶስ እራሱና በእርሱ የተመረጡት ሐዋርያቱ ስለ ማንነቱ ባስተማሩት ትምህርት ላይ እንጂ ብዙ ጊዜ በመሳሳት በሚታወቀው በሕዝብ አስተያየት ላይ መሆን የለበትም፡፡