ኢየሱስም አምላክ ከሆነ፣ “አብ ለራሱ ለይቶ የቀደሰውንና ወደ ዓለም የላከውን” ሲል እንዴት አምላክ ይቀደሳል?

 


20. ዮሐንስ 10፡36 ላይ “ታዲያ፤ “የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ” ስላልሁ፣ አብ ለራሱ ለይቶ የቀደሰውንና ወደ ዓለም የላከውን፣ ተሳድበሀል ብላችሁ ለምን ትወነጅሉኛላችሁ?” ይላል፡፡ ኢየሱስም “አምላክ ነው” ከተባለ ፣ እንዴት አምላክ ይቀደሳል? ኢየሱስ ተለይቶ ከመቀደሱ በፊት ምን ነበር? እንዴትስ አምላክ ይባላል?

ጠያቂው የክርስቶስን አምላክነት በግልፅ ከሚናገረው ከዚህ ምዕራፍ ውስጥ አምላክነቱን የሚቃወም ሐሳብ ለመፈለግ መሞከራቸው በእጅጉ አስገራሚ ነው፡፡ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ የሚከተሉትን ነጥቦች ግልፅ አድርጓል፡-

  • የዘለዓለምን ሕይወት ይሰጣል (ቁ. 28)
  • በጎቹን (ምዕመናንን) ማንም ከእጁ መንጠቅ አይችልም (ቁ. 28)
  • እነርሱን የሰጠው አባቱ ከነጣቂዎቹ ሁሉ ይበልጣል፤ እርሱና አብ ደግሞ አንድ ናቸው (ቁ. 29 እና 30)
  • አብ በእርሱ ነው እንዲሁም እርሱ በአብ ነው (ቁ. 38)

እነዚህን ሁሉ ነገሮች ከሰሙ በኋላ አይሁድ ኢየሱስ አምላክ መሆኑን እየተናገረ እንደሆነ በማሰብ ሊወግሩት መፈለጋቸው አያስገርምም፡- “አይሁድም፦ ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም፤ ስለ ስድብህ፤ አንተም ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ስለ ማድረግህ ነው እንጂ ብለው መለሱለት” (ቁ. 38)፡፡ እርሱም ንግግራቸውን ከመቃወም ይልቅ ከብሉይ ኪዳን ጥቅስ በመጥቀስ አምላክነቱን ሲያረጋግጥላቸው እናያለን፡- “ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦ እኔ፦ አማልክት ናችሁ አልሁ ተብሎ በሕጋችሁ የተጻፈ አይደለምን? መጽሐፉ ሊሻር አይቻልምና እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን አማልክት ካላቸው፥ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ እናንተ አብ የቀደሰውን ወደ ዓለምም የላከውን፦ ትሳደባለህ ትሉታላችሁን?” (ቁ. 34-36)፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዝሙረ ዳዊት 82 ላይ የተጠቀሱት ሰብዓውያን ባለ ሥልጣናት “አማልክት” የሚል ማዕርግ ከተሰጣቸው አብ ከሌሎች በተለየ ሁኔታ ያከበረውና ወደ ዓለም የላከው አንድያ ልጁ አምላክ ቢባል ምን ያስገርማል? እያለ ነው፡፡ በሌላ አባባል እነዚህ ሰብዓውያን ምፀታዊ በሆነ ሁኔታ “አማልክት” የሚል መጠርያ ቢሰጣቸውም እርሱ ግን የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ በመሆኑ ምክንያትና አብ በእርሱ ውስጥ እርሱም በአብ ውስጥ እንደመኖሩ አምላክ መባሉ ተገቢ መሆኑን እየተናገረ ነው፡፡ ወደ አሕመዲን ጥያቄ ስንመጣ ስህተታቸው የመነጨው “መቀደስ” ማለት “መለየት” ማለት መሆኑን ካለማወቅ ነው፡፡ “ሀጊያዞ” የሚለው የግሪኩ አቻ ቃል በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ ተጠቅሷል፡፡ ለምሳሌ ያህል ጌታችን ባስተማረው ጸሎት ውስጥ “ስምህ ይቀደስ” ተብሏል፡፡ በቀጥታ ከተተረጎመ የእግዚአብሔር ስም ቅዱስ ስለሆነ እኛ ልንቀድሰው አንችልም፡፡ “ስምህ ይቀደስ” ስንል የእግዚአብሔርን ስም እንደሌሎች ስሞች እንደማንመለከትና ተገቢውን ክብር እንደምንሰጥ ለመናገር ነው፡፡ 1ጴጥሮስ 3፡15 ላይ “ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት” ይላል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ቅዱስ በመሆኑ እርሱ ይቀድሰናል እንጂ እኛ ልንቀድሰው አንችልም፡፡ ይህ ቃል በልባችን ጌታችን ኢየሱስ ልዩ መሆኑን እውቅና መስጠት እንደሚገባን የተነገረ እንጂ እኛ ለእርሱ ቅድስናን መስጠት እንችላለን ለማለት የታለመ አይደለም፡፡ በተመሳሳይ “አብ የቀደሰውን ወደ ዓለምም የላከውን” ሲል የሰው ልጆችን ለመዋጀት ተልዕኮ እግዚአብሔር አብ አንድያ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደመረጠና ወደ ዓለም እንደላከ ያመለክታል፡፡ ስለዚህ የቃሉን ትርጉም በትክክል ከተረዳን “ኢየሱስ ከመቀደሱ በፊት ምን ነበር?” ብሎ የሚያስጠይቅ ምክንያት የለም፡፡

 

 

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች የተሰጠ መልስ ማውጫ