ሉቃስ 24፡19 “በእግዚአብሔርና በሰው ሁሉ ፊት በተግባርና በቃል ብርቱ ነብይ ስለነበረው ስለናዝሬቱ ኢየሱስ ነው” ይላል፡፡ ሐዋሪያት ኢየሱስን ማን ብለው ገለፁት?
6. ሉቃስ 24፡19 “እርሱም እንዲህ አለ “በእግዚአብሔርና በሰው ሁሉ ፊት በተግባርና በቃል ብርቱ ነብይ ስለነበረው ስለናዝሬቱ ኢየሱስ ነው” ይላል፡፡ እነዚያ ኢየሱስ ተዓምር ሲያደርግ የነበሩና የተመለከቱት ኢየሱስን ማን ብለው ገለፁት? “ነብይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ፡፡” አምላክ ነው ብለው አስበው ነበርን? በጭራሽ ታድያ ክርስቲያኖች እነዚያ ያላመኑትን ምነው ማመናቸው?
አውዱ የሚናገረው ከኢየሱስ ሞት በኋላ ተስፋ ቆርጠው ወደ መንደራቸው ሲሄዱ ስለነበሩት ሁለት ደቀ መዛሙርት ነው፡፡ መሲሁ እንደማይሞት ከሚያምነው የአይሁድ ማሕበረሰብ እንደመምጣታቸው የኢየሱስ ሞት እምነታቸውን ሸርሽሮታል፤ ተስፋም አስቆርጧቸዋል፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ከሙታን ተነስቶ ስለነበረ ወደ እነርሱ ቀርቦ አብሯቸው እያዘገመ ያዋራቸው ጀመር፡፡ ከላይ የተጠቀሰውን ቃል የተናገሩት ለእርሱ ለራሱ ነበር፡፡ ኋላ ግን ክርስቶስ እንደሚሞትና እንደሚነሳ ከቅዱሳት መጻሕፍት እየጠቀሰ ካስረዳቸው በኋላ ወደ ቤታቸው ሲደርሱ ማንነቱን አወቁ፡፡ እርሱ ግን ተሰወረባቸው፡፡ ወደ ኢየሩሳሌምም በፍጥነት ተመልሰው የሆነውን ለሐዋርያት ሲነግሩ ሳሉ ድንገት ኢየሱስ ራሱ በተዘጋ ቤት ውስጥ በመግባት በመካከላቸው ቆሞ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው፡፡ ሉቃስ ታሪኩን ይቀጥልና እስከ ዕርገት ድረስ የነበረውን ሁኔታ በአጭሩ ይነግረናል፡፡ በመጨረሻም እንዲህ በማለት ይደመድማል፡- “ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ ወደ ሰማይም ዐረገ፡፡ እነርሱም፤ ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ” (ሉቃስ 24፡51-52)፡፡ ተስፋ በመቁረጥ ጌትነቱና አምላክነቱ ደብዝዞባቸው ወደ ቀድሞ ኑሯቸው ሲመለሱ የነበሩት ደቀ መዛሙርት እውነቱን ተረድተው ሰግደውለታል፡፡ እኛም እንደ እነርሱ ለጌትነቱና ለአምላክነቱ የሚገባውን ስግደት ብንሰጠው ምኑ ላይ ነው ስህተታችን?