መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ተአምራትን ድንቅ ነገሮችንና ምልክቶችን በእርሱ በኩል በማድረግ ለናዝሬቱ ኢየሱስ መስክሮለታል” ካለ ታድያ ክርስቲያኖች ለምን ይህን ተቃረኑ?

 


8. የሐዋርያት ሥራ 2፡22 “የእስራኤል ሰዎች ሆይ! ይህን ቃል ስሙ፤ እናንተ እራሳችሁ እንደምታውቁት እግዚአብሔር በመካከላችሁ ተዓምራትን ድንቅ ነገሮችና ምልክቶችን በእርሱ በኩል በማድረግ ለናዝሬቱ ኢየሱስ መስክሮለታል” ይላል፡፡ እነርሱ ምንድን ነው የሚያውቁት ኢየሱስ ተአምራት ያደርገው አምላክ ስለሆነ ነው፡፡ ብለው ነው? በጭራሽ! በመካከላችሁ “ተአምራትን ድንቅ ነገሮችንና ምልክቶችን በእርሱ በኩል በማድረግ ለናዝሬቱ ኢየሱስ መስክሮለታል፡፡” ነው የሚለው ታድያ ክርስቲያኖች ለምን ይህን ተቃረኑ?

እግዚአብሔር አብ ተዓምራትን በእርሱ በኩል በማድረግ ስለ ገዛ ማንነቱ ያስተማራቸው ትምህርቶች ትክክል መሆናቸውን ነው የመሰከረለት፡፡ ኢየሱስ የራሱን ማንነት በተመለከተ የተናገራቸውን ነገሮች በጥንቃቄ ካነበበ በኋላ እንደ ማንኛውም ነቢይ መሆኑን ሊደመድም የሚችል ማንም አይኖርም፡፡ ሐዋርያው ጴጥሮስ ጠያቂው የጠቀሱትን ቃል ከተናገረ በኋላ በማስከተል እንዲህ በማለት የክርስቶስን ጌትነት አወጀ፡- “ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣምና፥ ነገር ግን እርሱ፦ ጌታ ጌታዬን፦ ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው አለ፡፡ እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ” (የሐዋርያት ሥራ 2፡34-36)፡፡ ዳዊት ኢየሱስን “ጌታዬ” ብሎ ከጠራው፤ እግዚአብሔር አብም በእርሱ በኩል ተዓምራትን በማድረግ ጌትነቱን ከመሰከረለት ሙስሊም ወገኖች ጌትነቱን የማይቀበሉበት ምክንያት ምንድነው?