ክርስቶስ እውን አምላክ ከሆነ፣ ወራሽ ነው ወይንስ አስወራሽ?

 


21. ሮሜ 8፡17 ላይ “ልጆች ብንሆንወራሾች ደሞ ነን፣ የክብሩ ተካፋዮች እንሆን ዘንድ በእርግጥ የመከራው ተካፋዮች ብንሆን፣ የእግዚአብሔር ወራሾች፣ ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን፡፡” ይላል፡፡ ክርስቶስ እውን አምላክ ከሆነ፣ እንዲሁም የሥላሴ አንዱ አካል ከሆነ ወራሽ ነው ወይንስ አስወራሽ? ነገ የእግዚአብሔርን ገነት ሊወርስ ነው ማለት ነውን? እንዲህም ሆነ አምላክ ትሉታላችሁን?

መጽሐፍ ቅዱስ በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑት ቅዱሳን ስለሚወርሱት ነገር ሲናገር በእስልምና እምነት ውስጥ ከተጠቀሰው የገነት ዓይነትም ሆነ አንዳንድ ክርስቲያኖች በተለምዶ ከሚያስቡት በእጅጉ የተለየ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ኢየሱስ የአባቱን ግዛት (Dominion) ነው የሚወርሰው፡፡ በስሙ ያመኑት ቅዱሳንም ይህንን ግዛት ከእርሱ ጋር እንደሚካፈሉና እንደሚነግሡ መጽሐፍ ቅዱስ በግልፅ ይናገራል (2ጢሞቴዎስ 2፡12፣ ራዕይ 3፡21፣ ራዕይ 22፡5፣ ኤፌሶን 2፡5-7)፡፡

በነዚህ ጥቅሶች መሠረት ቅዱሳን ከክርስቶስ ጋር በመሆን የአባቱን ግዛት ይወርሳሉ፡፡ ወራሽ መሆን ኢየሱስን አምላክ እንዳይሆን የሚያደርገው ከሆነ በቁርኣን መሠረት የአሕመዲን አምላክ አላህም ወራሽ በመሆኑ አምላክ ሊሆን አይችልም ማለት ነው፡-

“ከከተማም ኑሮዋን (ምቾቷን) የካደችን (ከተማ) ያጠፋናት ብዙ ናት፡፡ እነዚህም ከእነሱ በኋላ ጥቂት ጊዜ እንጅ ያልተኖረባቸው ሲኾኑ መኖሪያዎቻቸው ናቸው፡፡ እኛም (ከእነርሱ) ወራሾች ነበርን” (ሱራ 28፡58)፡፡

“ዘከሪያንም «ጌታዬ ሆይ! ብቻዬን አትተወኝ፡፡ አንተም ከወራሾች ሁሉ በላጭ ነህ ሲል» ጌታውን በተጣራ ጊዜ (አስታውስ)” (ሱራ 21፡89)፡፡[1]

“እኛ ምድርን በእርሷም ላይ ያለውን ሁሉ እኛ እንወርሳለን፡፡ ወደኛም ይመለሳሉ” (ሱራ 19፡40)፡፡

ጠያቂው ወራሽነት ከአምላክነት ደረጃ ዝቅ የሚያደርግ እንደሆነ የሚያምኑ ከሆነ አምላካቸው እውነተኛ አምላክ ላይሆን ነው፡፡

 

 

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች የተሰጠ መልስ ማውጫ