ኢየሱስ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ “ይህ ማነው?” ብለው ሲጠይቁ ነቢዩ ኢየሱስ ነው ካሉ እንዴት አምላክ ይሆናል?

 


17. ማቴዎስ 21፡11 “ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜም ከተማዋ በመላ፤ “ይህ ማነው?” በማለት ታወከች፡፡ አጅቦት የመጣው ሕዝብም፤ “ይህ በገሊላ ከምትገኘው ከናዝሬት የመጣው ነቢዩ ኢየሱስ ነው” አሉ፡፡” ይላል ፡፡ ኢየሱስን አጅቦት አብሮት ሲጓዝ የነበረው ሕዝብ “ነቢዩ ኢየሱስ ” ሲለው ምነው ክርስቲያኖች “አምላክ” ነው ማለታቸው? አምላክ እንዲሰኝ ፈልገው ይሆንን? አምላክነትስ በፍላጎት ይገኛል እንዴ? ከሙስሊሞችና ከክርስቲያኖች ሊዩነት  ውስጥ አንዱ የኢየሱስ ማንነት ጥያቄ ነው፡፡ ለመሆኑ ኢየሱስ ማን ነው? ኢየሱስ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ “ይህ ማነው?” ነበር የህዝቡ ጥያቄ፡፡ ምላሹንም አጅበው አብረው ወደ ኢየሩሳሌም የመጡት አማኞች እንዲህ ሲሉ ነበር የገለጹት “ይህ በገሊላ ከምትገኘው ከናዝሬት የመጣው ነቢዩ ኢየሱስ ነው፡፡” ታዲያ ክርስቲያኖች ኢየሱስን አጅበው አብረው ሲጓዙ ከነበሩት አማኞች በልጠው ነው ነቢይነቱን ያልተቀበሉት?

የተወደዱት ጠያቂያችን “ክርስቲያኖች ኢየሱስ ነቢይ መሆኑን አይቀበሉም”  የሚለውን ቅጥፈት በዚህ ምዕራፍ ከሞላ ጎደል በሁሉም ጥያቄዎች ውስጥ አንፀባርቀዋል፡፡ ይህ ደግሞ ምን ያህል የግንዛቤ እጥረት እንዳለባቸው የሚያሳይ ነው፡፡ አሳዛኙ ነገር አብዛኞቹ ሙስሊሞች መጽሐፍ ቅዱስን በራሳቸው አንብበው ከመረዳት ይልቅ መረጃዎቻቸውን የሚያገኙት ከእንደነዚህ ዓይነት ወገኖች መሆኑ ነው፡፡ ሰውየው የጠቀሱት ጥቅስ የኢየሱስን አምላክነት በግልፅ ከሚናገሩት የአዲስ ኪዳን ክፍሎች መካከል አንዱ መሆኑን አለማስተዋላቸው የሚያስገርም ነው፡፡ በዚያኑ ዕለት “የካህናት አለቆችና ጻፎች ያደረገውን ድንቃ ድንቅ በመቅደስም፦ ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ፥ ተቁጥተው፦ እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን? አሉት፡፡ ኢየሱስም፦ እሰማለሁ፤ ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁምን? አላቸው፡፡” (ቁ.15-16)፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲዘምሩለት የነበሩትን ህፃናት ዝም እንዲያሰኝ በተጠየቀ ጊዜ በቀጥታ በመዝሙረ ዳዊት 8፡2 ለያሕዌ እግዚአብሔር የተነገረውን ጥቅስ በመውሰድ ለራሱ አደረገ፡፡ ይህም የአምላክነቱ ማስረጃ ነው፡፡

በክርስቶስ ዘመን የነበሩት ሕዝቦች የኢየሱስን ማንነት ጠይቀዋል፤ በገባቸው መንገድም ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ነገር ግን ማንነቱን በተመለከተ ከሕዝቡ ምስክርነት ይልቅ እጅግ አስተማማኝ ማስረጃ አለን፡፡ በአንድ ወቅት ኢየሱስ ማንነቱን የተመለከተ ጥያቄ ለደቀ መዛሙርቱ አቅርቦ ነበር፡- “ኢየሱስም ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን፦ ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል? ብሎ ጠየቀ፡፡ እነርሱም፦ አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት፡፡ እርሱም፦ እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው፡፡ ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ፦ አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ፡፡ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ፡፡” አዎን፣ በዘመኑ የነበሩት ብዙ ሰዎች ነቢይነቱ ተረድተዋል፡፡ ነገር ግን ያልተረዱት አንድ ትልቅ ጉዳይ ነበር፤ ኢየሱስ በብሉይ ኪዳን ትንቢት የተነገረለት መሲህ እና የሕያው እግዚአብሔር ልጅ መሆኑን፡፡ ይህንን እውነታ መረዳት የሚችሉት እግዚአብሔር በቅዱስ መንፈሱ ልቦናቸውን ያበራላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር የሙስሊም ወገኖቻችንን የልብ ዓይኖች በመክፈት ኢየሱስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ማመን ይችሉ ዘንድ፣ አምነውም በስሙ ሕይወት ይሆንላቸው ዘንድ ይርዳቸው፡፡