መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው አምላክ ድካምና ሞኝነት ካለበት ምኑን አምላክ ሆነ?

 


  1. ጳዉሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 1፡25 ላይ “ምክንያቱም ከሰው ጥበብ ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባል፤ ከሰውም ብርታት ይልቅ የእግዚአብሔር ድካም ይበረታል፡፡” ብሏል፡፡ እንደዚህ ጥቅስ አባባል እግዚአብሔርም ሞኝነት አለበት፤ ግን የእርሱ ሞኝነት ከሰው ጥበብ ይጠበባል፡፡ ድካምም አለበት፤ ነገር ግን ድካሙ ከሰው ብርታት ይበረታል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው አምላክ ድካምና ሞኝነት ካለበት ምኑን አምላክ ሆነ? ወይስ ይህ ጥቅስ የጳውሎስ ፈጠራ ነው?

ሐዋርያው ምን እያለ እንደሆነ ለመረዳት አውዱን ማንበብ ያስፈልጋል፡-

“የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና፡፡ የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ ተብሎ ተጽፎአልና፡፡ ጥበበኛ የት አለ? ጻፊስ የት አለ? የዚች ዓለም መርማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን? በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች፥ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአልና፡፡ መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፥ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፥ ለተጠሩት ግን፥ አይሁድ ቢሆኑ የግሪክ ሰዎችም ቢሆኑ፥ የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው፡፡ ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና፥ የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና፡፡” (1ቆሮንቶስ 1፡18-25)፡፡

የወንጌል መልእክት በፍልስፍና የተቀመመ ባለመሆኑ ግሪኮች እንደ ሞኝነት ይቆጥሩታል፡፡ አይሁድ ደግሞ መሲሁ እንደማይሞት ስለሚያምኑ እንደ ድካም ይቆጥሩታል፡፡ ሐዋርያው እነርሱ የተናገሩትን በመጥቀስ በምፀት እየመለሰላቸው ነው፡፡ በዘመናዊ አጻጻፍ ቢሆን ኖሮ “ሞኝነት” እና “ድካም” የሚሉት ቃላት የተቃዋሚዎች እንጂ የጳውሎስ ባለመሆናቸው ትዕምርተ ጥቅስ ውስጥ ይገቡ ነበር፡፡ ሐዋርያው “እናንተ ሞኝነት የምትሉት የክርስቶስ መስቀል ከሰው ጥበብ የተጠበበ ነው፤ እናንተ ድካም የምትሉት የክርስቶስ መስቀል ከሰው ኃይል የበረታ ነው” በማለት ምፀታዊ በሆነ መንገድ ምላሽ እየሰጣቸው ነው፡፡ ጠያቂው ይህንን ሙግት ወደ መድረኩ ማምጣታቸው ስለመጽሐፍ ቅዱስ ሥነ ፍታቴ ያላቸው ዕውቀት ጥራዝ ነጠቅ መሆኑን ያሳያል፡፡