አምላክ እንደሰው ሥራ ሰርቶ ያርፋልን? ድካም ይሰማዋል እንዴ?

 


3. ዘፀአት 31፡17 “በእኔና በእስራኤላውያን መካከል ለዘለዓለም ምልክት ይሆናል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሰማይ ምድርን በስድስት ቀን ሰርቶ፤  በሰባተኛው ቀን ከሥራ ታቅቦ ዐርፎአልና” ይላል፡፡ እንዲሁም በሌላ ስፍራ “ስለ ሰባተኛውም ቀን በአንድ ስፍራ “በሰባተኛውም ቀን እግዚአብሔር ከሥራው ሁሉ ዐረፈ” ብሏልና፡፡” (ዕብራውያን 4፡4)፡፡ አምላክ እንደሰው ሥራ ሰርቶ ያርፋልን? ድካም ይሰማዋል እንዴ? አንዳንድ ክርስቲያኖች “አምላክ ሊያስተምረን ብሎ ነው” ይላሉ፡፡ አምላክ የሚያስተምረው ነቢያትንና መጻሕፍትን በመላክ ነው ወይንስ የደካማውን የሰው ልጅ ባህሪ በመላበስ?

በዚህ ቦታ ጥቅም ላይ የዋለው የዕብራይስጥ ቃል “ሻባት” የሚል ሲሆን ቀጥተኛ ትርጉሙ “ማቆም” ወይም “መተው” የሚል ነው፡፡ ቃሉ እንደየአውዱ በተለያዩ መንገዶች ሊተረጎም ቢችልም ከድካም የተነሳ እረፍት መውሰድን የግድ አያመለክትም፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊያን ይህንን ቃል የተጠቀሙት እግዚአብሔር ደክሞት እንዳረፈ ለማመልከት ሳይሆን እግዚአብሔር የመፍጠር ሥራውን ስላጠናቀቀ ማቆሙን ለማመልከት ነው፡፡[1] ጠያቂው “አምላክ ሊያስተምረን ብሎ ነው” በማለት መልስ የሚሰጡ ክርስቲያኖች ስለመኖራቸው የተናገሯት ነገር ፈጠራ እንዳትሆን እጠረጥራለሁ፡፡ ግንዛቤው ያላቸው ክርስቲያኖች በዚህ መልኩ ምላሽ አይሰጡም፡፡ ጠያቂው የክርስትናን ትምህርት ለመገዳደር መጽሐፍ እስከጻፉ ድረስ ከግለሰቦች ከለቃቀሟቸው “ምላሾ” ሳይሆን ዕውቀቱ ባላቸው ክርስቲያኖች ከተሰጡት ምላሾች በመነሳት ሙግታቸውን ማቅረብ ነበረባቸው፡፡