የይሁዳ ሰዎች እግዚአብሔር ከነርሱ ጋር ስለሆነ ኮረብታማውን አገር ከያዙ እግዚአብሔር አብሯቸው እያለ እንዴት ከረባዳው ምድር ማስወጣት ተሣናቸው?

 


18. መሳፍንት 1፡19 “እግዚአብሔር ከይሁዳ ሰዎች ጋር ነበር፤ ስለዚህ ኮረብታማውን አገር ያዙ፤ ነገር ግን በረባዳው ምድር የሚኖሩት ሰዎች ከብረት የተሠሩ ሠረገሎች ስለነበሯቸው ከዚያ አሳደው ሊያስወጧቸው አልቻሉም” ይላል፡፡ የይሁዳ ሰዎች እግዚአብሔር ከነርሱ ጋር ስለሆነ ኮረብታማውን አገር ከያዙ እግዚአብሔር አብሯቸው እያለ እንዴት ከረባዳው ምድር ማስወጣት ተሣናቸው? ጥቅሱ እንደ ሚለው ከብረት የተሠሩ ሠረገሎች ስለነበሯቸው? አምላክ “ከብረት የተሰሩ ሰረገሎች” ይበግሩታልን? እውን አምላክ የሚሳነው ነገር አለን?

እግዚአብሔር ከእኛ ጋር አለ ማለት ሁሉንም ነገር ማድረግ እንችላለን ማለት አይደለም፡፡ የይሁዳ ሕዝቦች በእግዚአብሔር እርዳታ ኮረብታማውን አገር ይዘውታል፡፡ ነገር ግን ረባዳውን አገር ላለመያዛቸው የብረት ሰረገሎች እንደ ምክንያት ቢጠቀሱም እንዲይዙት የእግዚአብሔር ፈቃድ አልሆነም፡፡ ምክንያቱን ደግሞ እግዚአብሔር አስቀድሞ ለሕዝቡ አስታውቋል፡- “አምላክህም እግዚአብሔር እነዚህን አሕዛብ በጥቂት በጥቂቱ ከፊትህ ያወጣቸዋል፤ የምድረ በዳ አራዊት እንዳይበዙብህ አንድ ጊዜ ታጠፋቸው ዘንድ አይገባህም፡፡” (ዘዳግም 7፡22)፡፡