ኢየሱስ የእግዚአብሔር አምሳል መሆኑን ይናገራል። ኢየሱስ አምላክ ነው ወይንስ የአምላክ አምሳል?
24. ኢየሱስ አምላክ ነው ወይንስ የአምላክ አምሳል? ቆላስይስ 1፡15 እና 2ኛ ቆሮንቶስ 4፡4 ኢየሱስ የእግዚአብሔር አምሳል መሆኑን ይናገራሉ፡፡ እንዲሁም በዘፍጥረት 1፡26 ላይ ሰው ሁሉ በእግዚአብሔር አምሳል መፈጠሩ ተገልጿል፡፡ ታዲያ ኢየሱስ እንደማንኛውም ሰው የእግዚአብሔር አምሳል ከሆነ ልዩነቱ ምን ላይ ነው? ያው መቼም አምላክ አምላክ ነው፡፡ ክርስትና እንደሚለው ደግሞ ኢየሱስ አምሳሉ ነው፡፡ ኢየሱስ “አምላክም”፣ “የአምላክ አምሳልም” ሊሆን ይችላል? እንዴት ራሱና አምሳሉ አንድ ይሆናሉ?
አሕመዲን በጠቀሷቸው ሁለቱ ጥቅሶች ውስጥ ኢየሱስ የእግዚአብሔር አምሳል መሆኑን ለመግለፅ ጥቅም ላይ የዋለው ቃል “ኤይኮን” የሚል ሲሆን የአንድን ነገር ምስል ወይም ቅርፅ ያመለክታል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር አብን ያየ ማንም እንደሌለ ይናገራል (ዮሐንስ 1፡1-3፣ 14፣ 18፣ ሮሜ 1፡20)፡፡ ነገር ግን የማይታየው እግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ልጁ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለዓለም ራሱን ገልጧል፡፡ በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራል (ቆላስይስ 1፡19፣ 2:9)፡፡ በእርሱና በአብ መካከል የባሕርይ ልዩነት ስለሌለ እርሱን ያየ ሁሉ አብን አይቶታል (ዮሐንስ 14፡8-10)፡፡ እርሱና አብ አንድ ናቸው (ዮሐንስ 10፡30)፡፡ በእርግጥ አሕመዲን አጀንዳቸውን ስለሚያፈርስ ጥቅሱን ለመጻፍ አልደፈሩም እንጂ ቆላስይስ 1፡15 የኢየሱስን አምላክነት በግልፅ ቋንቋ ያስቀምጣል፡- “እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው፤ የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፡፡”
(የብኩርና ትርጉም ጥያቄ ቁጥር 5 ላይ ተብራርቷል፡፡)
ኢየሱስ የእግዚአብሔር አብ አምሳል መሆኑ የተጠቀሰበት አምላክነቱን በማያጠራጥር ሁኔታ የሚገልጥ ሌላ ጥቅስ በዕብራውያን መልእክት ውስጥ ይገኛል፡- “እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ” (ዕብራውያን 1፡3)፡፡
“የባሕርዩ ምሳሌ” ተብሎ የተተረጎመው “ሁፖስታሴዎስ ካራክቴር” የሚል የግሪክ ሐረግ ሲሆን ካራክቴር የአንድን ነገር ትክክለኛ፣ ያልተሸራረፈ፣ ከዚያኛው አካል ያላነሰ፣ እኩል የሆነ ቅጂ የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ “ምሳሌ” ከዚያኛው አካል ጋር በሁሉም ረገድ ፍፁም ተመሳሳይ ነው፡፡ ይህ ቃል ወልድ ከአብ ልዩ መሆኑን፤ ነገር ግን ደግሞ ከአብ ጋር ፍፁም እኩል መሆኑን ከምንም ዓይነት ጥርጣሬ በፀዳ ሁኔታ የሚገልጥ ነው፡፡[2] “እንዴት ራሱና አምሳሉ አንድ ይሆናሉ?” የሚለው የአሕመዲን ጥያቄ እግዚአብሔር አንድ አካል ብቻ አለው በሚል የተሳሳተ ቅድመ ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ የሥላሴን ፅንሰ ሐሳብ የማያውቅ ሰው የሚጠይቀው ከዕውቀት ጉድለት የመነጨ ጥያቄ ነው፡፡