ኢየሱስ ዋናውን ሐዋርያ ጴጥሮስን ሰይጣን ብሎታል፤ ትንሣኤ ምስክሮች ከነበሩት መካከል አንዷ የነበረችው መግደላዊት ማርያም በሰባት አጋንንት የተያዘች ነበረች!
-
ሐዋርያት ኢየሱስ የሚላቸውን ለመረዳት ሲሳናቸው ነበር (ማርቆስ 4፡13፣ 6፡52፣ 8፡18-17፣ 9፡32፣ ሉቃስ 8፡9 እና 9፡45)፡፡ ኢየሱስ እምነት እንደጎደላቸው ነግሯቸዋል (ማቴዎስ 8፡26)፡፡ ነቅተው እንዲጠብቁ ሲያዛቸው ተኝተው አግኝቷቸዋል (ማቴዎስ 26፡36-43)፡፡ ኢየሱስ ሲያዝ “አናውቀውም” በማለት ክደውታል (ማርቆስ 14፡66-72)፡፡ ከስቅለቱ በኋላ ወደ ቀድሞ ሥራቸው (አሣ ወደማጥመድ) ተመልሰዋል (ዮሐንስ 21፡2-3)፡፡ ኢየሱስን የከዳው ሐዋርያ የነበረው ይሁዳ ነበር (ማቴዎስ 26፡14-16)፡፡ ሰይጣን ሐዋርያ ወደ ነበረው ወደ ይሁዳ ገባ፤ ወደ ጴጥሮስም ለመግባት ሞክሮ ነበር (ሉቃስ 22፡3፣ 31)፡፡ ኢየሱስ ዋናውን ሐዋርያ ጴጥሮስን ሰይጣን ብሎታል (ማቴዎስ 16፡23)፡፡ የኢየሱስ ትንሣኤ ምስክሮች ከነበሩት መካከል አንዷ የነበረችው መግደላዊት ማርያም በሰባት አጋንንት የተያዘች ነበረች፤ ምስክርነቷንም ሐዋርያት አላመኑም (ማርቆስ 16፡9፣ 10)፡፡ ሐዋርያት ሴቶች መቃብሩ ባዶ መሆኑን ሲነግሯቸው ቅዠት መስሏቸው አላመኗቸውም (ሉቃስ 24፡11)፡፡
ጠያቂው ከላይ የተዘረዘሩትን ነጥቦች በመጥቀስ “ታዲያ የነዚህ ሰዎች ጽሑፍና ምስክርነት ይታመናልን?” የሚል ጥያቄ ይሰነዝራሉ፡፡
የታሪክ ተመራማሪዎች የአንድን ጥንታዊ ሰነድ ሐቀኝነት ከሚመዝኑባቸው መንገዶች መካከል አንዱ “የሐፍረት መስፈርት” (The Criteria of Embarrassment) ይሰኛል፡፡ ይኸውም አንድ ሰው ስለ ራሱ ወይም ስለሚወደውና ስለሚያከብረው ሰው እርሱ ራሱ ሊያፍርበትና ሊሸማቀቅበት የሚችለውን ነገር ከጻፈ የታሪኩ ተዓማኒነት ከፍ ያለ ነው የሚል ነው፡፡ አሕመዲን ጀበል በብዙ ሙስሊሞች ዘንድ “የታሪክ ምሑር” ተብለው የሚሞካሹ ሆነው ሳሉ ይህንን መሠረታዊ ግንዛቤ ማጣታቸው አስገራሚ ነው! የሐዋርያት ድካምና ውድቀት ያለ ምንም መሸፋፈን መነገሩ ምስክርነታቸውን እንድናምን የሚያደርግ እንጂ እንድንጠራጠር የሚያደርግ አይደለም፡፡ ይልቁኑ ምንም ድካም ያልነበረባቸው ፍፁማን ሰዎች እንደነበሩ በተጋነነ ሁኔታ ቢጻፍ ነበር ምስክርነታቸውን በጥርጣሬ ማየት ተገቢ የሚሆነው፡፡ ድካማቸውንና ውድቀታቸውን በተመለከተ አብዛኞቹ ሰዎች በማያደርጉት ሁኔታ ሳይዋሹ በግልፀኝነትና በሐቀኝነት እንዲጻፍ ያደረጉ ሰዎች ምስክርነት ካልታመነ የማን ሊታመን ነው?
ይሁዳ ወንጌልን አልጻፈም፤ ስለ ኢየሱስ ትንሳኤም አልመሰከረም፡፡ ከአሥራ ሁለቱ መካከል አንዱ ስለነበረና ኢየሱስን በገንዘብ ስለለወጠ የተቀሩትን የአሥራ አንዱን ምስክርነት እንዳናምን ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡ መግደላዊት ማርያም ከሰባት አጋንንት ነፃ በማውጣት ኢየሱስ ተዓምር ያደረገላት ነፃ የወጣች ሴት በመሆኗ ምስክርነቷ ከማንም በላይ የሚታመን ነው፡፡ ዛሬም በክርስቶስ አምነው ከአጋንንት ነፃ በመውጣት የሚያገለግሉት ብዙ ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይገኛሉ (ኤፌሶን 2፡1-7)፡፡
ጠያቂው “ነቢይ” በማለት የሚከተሏቸው ሰው ከአጋንንት ነፃ እንዳልነበሩ በአንደበታቸው መናገራቸው ሳያሳስባቸው ከአጋንንት ነፃ የወጣችው የመግደላዊት ማርያም ጉዳይ ለምን እንዳሳሰባቸው የሚያስገርም ነው (የመጀመርያውን ምዕራፍ 36ኛ ቁጥር ይመልከቱ)፡፡
ኢየሱስ ሲያዝ ሐዋርያቱ እንዲሸሹ ያደረጋቸው ስለ መሲሁ ተልዕኮ የነበራቸው የተሳሳተ አስተሳሰብ ነበር፡፡ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን በነበረው የአይሁድ አስተሳሰብ መሠረት መሲሁ ጠላቶቻቸውን ድል ነስቶ የሚነግሥ እንጂ በጠላት ተይዞ የሚገደል አልነበረም፡፡ ይህ የተሳሳተ አመለካከት ነው ተስፋ እንዲቆርጡና እንዲበተኑ ያደረጋቸው፡፡ ኢየሱስ ስለ ሞቱ ሲናገር በሰማ ጊዜ ጴጥሮስ ለብቻው ወስዶ ሊገሥፀው የሞከረው ይህ የተሳሳተ አመለካከት ስለነበረው ነበር፡፡ የኢየሱስ ምላሽ ግን “ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል” የሚል ነበር (ማቴዎስ 16፡22-23)፡፡ የእግዚአብሔር ዓላማ ክርስቶስ በመስቀል ሞቶ ዓለምን እንዲያድን ቢሆንም ጴጥሮስ ግን እንደ ዘመኑ አይሁድ ሁሉ መሲሁ እንደማይሰቀል ያምን ስለነበር ኢየሱስ ለመስቀል ራሱን አሳልፎ እንዳይሰጥ በመምከር ሳያውቀው የእግዚአብሔር ፈቃድ ተቃዋሚ ሆኖ ነበር፡፡ “ሰይጣን” የሚለው የዕብራይስጥ ቃል “ተቃዋሚ”፣ “ከሳሽ” ወይም “ተገዳዳሪ” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን “ሰይጣን” የተሰኘውን ክፉ መንፈስ ወይንም ደግሞ ማንኛውንም ተቃዋሚና ተገዳዳሪ የሆነ አካል ለማመልከት ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል፡፡ ዘኁልቁ 22:22፣ 22:32፣ 1ሳሙኤል 29:4፣ 2ሳሙኤል 19:22፣ 1ነገሥት 5:4፣ 11:14፣ 11:23፣ 11:25፣ ወዘተ. በመሳሰሉት ክፍሎች ላይ “ሰይጣንን” በማያመለክት ሁኔታ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን በተለያዩ መንገዶች ተተርጉሟል፡፡ ኢየሱስ ጴጥሮስን በዚህ ሁኔታ ሲገስፀው ተቃዋሚ መሆኑን ለማመልከት ብቻ ፈልጎ ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም ደግሞ ክርስቶስን ከተልዕኮው ለማደናቀፍ የሚፈልገውን የሰይጣንን ሐሳብ በማስተናገዱ ምክንያት የሐሳቡ አመንጪ የሆነው ከበስተጀርባው የሚገኘውን ሰይጣንን ለመገሰፅ ፈልጎ ሊሆን ይችላል፡፡
ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከመቀበላቸው በፊት ብዙ ድካሞች የነበሩባቸው ቢሆኑም መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ግን ድካሞቻቸው በብርታት ተለውጠዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚናገረው በይሁዳ ቦታ የተተካው ማቲያስን ጨምሮ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት መካከል የተፈጥሮ ሞት የሞተው ሐዋርያው ዮሐንስ ብቻ ነበር፡፡ አሥራ አንዱ ግን ስለ እምነታቸው ሰማዕታት ሆነዋል፡፡ በአንድ ወቅት ፈሪዎችና ተጠራጣሪዎች የነበሩ ሰዎች ከመቅፅበት ተለውጠው በድፍረት ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተነስቶ እንደታያቸው በሃይማኖት መሪዎችና በባለ ሥልጣናት ፊት ቆመው እንዲመሰክሩ፣ ምስክርነታቸው እውነት መሆኑን ደግሞ እስከ ሞት ድረስ በመታመን እንዲያረጋገጡ፣ የዓለምንም ታሪክ እስከ ወዲያኛው እንዲለውጡ ያደረጋቸው አንዳች ተዓምር መኖር አለበት! ጌታ ኢየሱስ በመጨረሻዋ ሰዓት ጥለውት ስለሸሹ አልጣላቸውም፡፡ ከትንሣኤው በኋላ እንደገና እንዲመለሱ ዕድልን በመስጠት ይቅር ብሏቸዋል፤ ለታላቅ አገልግሎትም ሾሟቸዋል (ማቴዎስ 28፡18-20፣ ሉቃስ 24፡45-53፣ ዮሐንስ 20፡19-31፣ 21፡15-20፣ የሐዋርያት ሥራ 1-14)፡፡ መንፈስ ቅዱስንም በመላክ ኃይልን ሰጥቷቸዋል (የሐዋርያት ሥራ 2፡1-21)፤ ከዚህ የተነሳ የሐዋርያት አገልግሎት በድንቅ እና በአስገራሚ ተዓምራት የታጀበ ነበር (የሐዋርያት ሥራ 2፡43፣ 3፡1-11፣ 5፡15-16)፡፡ ዲያብሎስ የተሰኘው እርኩስ መንፈስ ከሚታወቅባቸው ነገሮች መካከል አንዱ ክስ ነው፡፡ እግዚአብሔር ኃጢአታቸውን ይቅር ያላቸውንና ከድካማቸው ያነሳቸውን ሰዎች በቀደመው ኃጢአታቸውና ድካማቸው ይከሳቸዋል፡፡ በአሕመዲን ጀበል ጽሑፍ ውስጥም የሚንጸባረቀው ይኸው ነው፡፡
ጠያቂው የአራቱን ወንጌላት ተኣማኒነት አጠራጣሪ ለማስመሰል ምሑራን ስለተጻፉበት ቦታና ዘመን እርግጠኛነት በጎደላቸው ቃላት መናገራቸውን እንደ ማስረጃ ይጠቅሳሉ፡፡ ገፅ የሚሞሉ ረጃጅም ጥቅሶችን የጠቀሱ ሲሆን አብዛኞቹን ሆነ ብለው ከአውድ በመገንጠል እና ሲያሻቸው የራሳቸውን ሐሳብ በመጨመር አንዳንዴም በገፁና በቦታው ላይ የሌለውን የራሳቸውን ቅጥፈት በማከል ጽፈዋል፡፡ ምናልባት የእሳቸውን መጽሐፍ የሚያነቡ አብዛኞቹ ሰዎች የተጠቀሱትን መጽሐፍት አግኝተው እንደማያነቡ አለዚያም እሳቸው ያሉትን አምኖ ከመቀበል ውጪ ገፁን እንደማይገልጡ አስበው ይሆናል፡፡ አንባቢያን በትክክል የተባሉትን ነገሮች ማየት እንዲችሉ ጠያቂው በትክክል ያልጠቀሷቸውን ክፍሎች ከትክክለኞቹ ጥቅሶች ጋር በሳጥን ጎን ለጎን በማስቀመጥ እናሳያለን፡፡
የሉቃስ ወንጌልን በተመለከተ ያነሷቸው ነጥቦች
አሕመዲን የጻፉት ስለ ሉቃስ ወንጌል የክርስቲያን ምሑራን እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፡- “ምናልባት የሉቃስ ወንጌል የተጻፈው በ60 ዓ.ም. ገደማ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ምክንያቱም በዚያን ጊዜ ሉቃስ ክርስቲያን ከሆነ ቢያንስ አሥር ዓመት ወይም ከዚያ በላይ በክርስትና የቆየ ሊሆን ስለሚችልና ኢየሱስን በሥጋ የሚያውቁትን ብዙ ሰዎችን ሊያገኝ ወደሚችልበት ወደ ፖልስታይን ሳይሂድ አልቀረም፡፡ ምናልባትም ጳውሎስ በእስር ቤት በነበረበትን ዘመን ሉቃስ የኢየሱስን ምድራዊ ሕይወትና እንቅስቃሴ ለመመዝገብ ብዙ ጊዜ ሳይወስድበት አልቀረም፡፡ ስለእርሱ ብዙ ከሰማው ተነስቶ ስለ ጳውሎስ ሚስዮናዊ አገልሎትም ብዙ ሳይመረምር አልቀረም፡፡ … የማርቆስን ወንጌል መሠረት በማድረግ ሳይጽፍ እንዳልቀረ ስለሚታመን የሉቃስ ወንጌል የተፃፈው በኋለኛው ዘመን ሳይሆን አይቀርም፡፡ በወንጌሎቹ መካከል ያለው የሥነ ጽሑፍ መመሳሰልን በተመለከተም በሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክርስቶስ ይሰብክ የነበረው አንድ አይነት የሆነ ወንጌል ስብከትን እንደሆነ ለመገመት ይቻላል፡፡ ዮሐንስ ማርቆስ በመጀመሪያ ከበርናባስና ከሳኦል ጋር ወደ አንፆኪያ በሄደ ጌዜ ሉቃስና ማርቆስ እዚያው ተገናኝተው የቆየ ትውውቅ ሳይኖራቸው አይቀርም፡፡ 60ኛው ዓ.ም. የሉቃስ ወንጌል የተጻፈበት ጊዜ ነው ብሎ በርግጠኝነት መናገር ባይቻልም ተቀራራቢው ዓመት ነበር ብሎ መውሰድ ግን ይቻላል፡፡ የሉቃስ ወንጌል የት ቦታ እንደተፃፈ የተሠጠ አንዳችም ፍንጭ የለም፡፡ ምንም እንኳ ታሪኮቹ በቂሣርያ ሊጠናቀሩ ቢችሎም ከፓለስቲና ውጪ ሳይጻፍ እንዳልቀረ ግን ይገመታል፡፡ ሮምን፣ ቂሣሪያን፣ አካይን፣ ትንሹ ኢስያን እና አሌክሳንደራያን ጨምሮ የሚሰጡት ከግምታዊ አስተያየትነት አይዘሉም፡፡” |
መጽሐፉ የሚለው “ሉቃስ ስለ ጳውሎስና ስለ አሟሟቱ ምንም ዓይነት ተጨማሪ አሳብ ስላልጻፈ የሐዋርያት ሥራን ጽፎ የጨረሰው ጳውሎስ ከእስር ቤት ከመውጣቱና እንደገና ከመታሰሩ በፊት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ስለሆነም የሐዋርያት ሥራ በ63 እና 64 ዓ.ም. መካከል እንደጻፈ ይገመታል፡፡ ይህም የሉቃስ ወንጌል ከዚያ በፊት እንደተጻፈ ያመለክታል፡፡ ስለሆነም ሉቃስ ወንጌሉን ከ59-63 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ እንዳጠናቀቀ ይገመታል፡፡ ሉቃስ የማርቆስን ወንጌል እንደ ምንጭ ተጠቅሟል የሚሉ ምሑራን መጽሐፉ የተጻፈበትን ዘመን ወደ 70 ዓ.ም. ያመጡታል፡፡ እነዚህ ወገኖች እንደሚሉት ይህን ወንጌል እንደ አንዱ ምንጭ አድር ከመጠቀሙ በፊት የማርቆስ ወንጌል ተጽፎ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እስኪሰራጭ ድረስ ጊዜ ሳይወስድ እንዳልቀረ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን የማርቆስ ወንጌል ቀደም ብሎ ተጽፎ ተቀባይነትን ካገኙት ወንጌላት እንደ አንዱ ሆኖ ካገለገለባት በኋላ በሮም የራሱን መጽሐፍ ጽፎ ይሆናል ብለው ይገምታሉ፡፡ ሉቃስ ከ63 ዓ.ም. በኋላ ጽፎታል የሚለው ግምት ግን ይህን ያህል ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ሉቃስ ወንጌሉን የጻፈው በየት ስፍራ እንደሆነ በውል አይታወቅም፡፡ በአማራጭነት የሚጠቀሱት አገሮች 1) ሉቃስ ብዙ ጊዜ ያሳለፈባት ፊልጵስዩስ፣ 2) ጳውሎስ ለሁለት ዓመታት የታሰረባት ቂሣርያ ወይም 3) ጳውሎስ ታስሮ የቆየባት ሮም ናቸው፡፡ ከእነዚህ በአንዱ ሳይሆን እንዳልቀረ ይገመታል፡፡ ሆኖም ሉቃስ ወንጌሉን የጻፈው በቂሣርያ ወይም በሮም በቆየባቸው ጊዜያት ይመስላል፡፡” (ቲም ፌሎስ የአዲስ ኪዳን መምሪያና ማብራሪያ በትምህርተ መለኮት ማስፍፊያ (ት.መ.ማ.) መልክ የተዘጋጀ፣ 1ኛ መጽሐፍ፣ ገፅ 339) |
ምርመራ
- ከ2ኛ የት.መ.ማ. መጽሐፍ ላይ እንደሆነ የጠቀሱት ሁሉ በ1ኛ መጽሐፍ ውስጥ እንጂ በ2ኛ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኝ አይደለም፡፡ 2ኛው መጽሐፍ ከሮሜ ጀምሮ ባሉት መልዕክታት ላይ የተጻፈ እንጂ ወንጌላትን የተመለከተ አይደለም፡፡
- አሕመዲን የጠቀሱት እና በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኘው የሐሳብ መመሳሰል ቢኖረውም በመጽሐፉ ውስጥ የሰፈረ አይደለም፡፡ ጸሐፊው ሐሳቡን በራሳቸው አባባል እንዳሰፈሩ ሳይሆን “ስለ ሉቃስ ወንጌል የክርስቲያን ምሑራን እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፡-” ካሉ በኋላ ተጽፏል ያሉትን ሐሳብ በትዕምርተ ጥቅስ (“”) ውስጥ በማስቀመጥ ስለነገሩን የፈጸሙት ተግባር ከቅጥፈትና ታማኝነትን ከማጉደል ይቆጠራል፡፡
አሕመዲን የጠቀሱት “የጳውሎስ የወንጌል አገልግሎት ባልደረባ የነበረው ሉቃስ የዚህ ወንጌል ደራሲ መሆኑን ሁሉም የጥንት የቤተ ክርስቲያን አባቶች በአንድ ድምፅ ይስማሙበታል፡፡ ምሑራን ሉቃስ የዚህ ወንጌል ጸሐፊ መሆኑን መጠራጠር የጀመሩት ባለፉት 100 ዓመታት ውስጥ ብቻ ነው፡፡ እነዚህ ምሑራን ጥርጣሬያቸውን ያቀረቡት ከሉቃስ ዘመን በኋላ ስለ ተነሱት የቤተ ክርስቲያን ችግሮች የሚዘግቡ አሳቦች በመጽሐፉ ውስጥ እንደሚገኙ በመግለፅ ነው፡፡ … እንደ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮች ሁሉ ስለ ሉቃስም ያለን መረጃ የተወሰነ ነው፡፡” (ቲም ፌሎስ፣ የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ በትምህርተ መለኮት ማስፋፍያ (ት.መ.ማ) መልክ የተዘጋጀ፣ 2ኛ መጽሐፍ፣ ገጽ 336 |
በመጽሐፉ ውስጥ የሰፈረው ሙሉ ሐሳብ “የጳውሎስ የወንጌል አገልግሎት ባልደረባ የነበረው ሉቃስ የዚህ ወንጌል ደራሲ መሆኑን ሁሉም የጥንት የቤተ ክርስቲያን አባቶች በአንድ ድምፅ ይስማሙበታል፡፡ ምሑራን ሉቃስ የዚህ ወንጌል ጸሐፊ መሆኑን መጠራጠር የጀመሩት ባለፉት 100 ዓመታት ውስጥ ብቻ ነው፡፡ እነዚህ ምሑራን ጥርጣሬያቸውን ያቀረቡት ከሉቃስ ዘመን በኋላ ስለ ተነሱት የቤተ ክርስቲያን ችግሮች የሚዘግቡ አሳቦች በመጽሐፉ ውስጥ እደሚገኙ በመግለፅ ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ሉቃስ የዚህ ወንጌል ደራሲ አለመሆኑን የሚያሳይ ጠንካራ መረጃ አልተገኘም፡፡ እንደ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮች ሁሉ ስለ ሉቃስም ያለን መረጃ የተወሰነ ነው፡፡ ከሦስቱ የጳውሎስ መልእክቶች እንደምንረዳው፣ ሉቃስ በሙያው ሐኪም የነበረ ሲሆን፣ የጳውሎስ የቅርብ ጓደኛና የሥራ ባልደረባ ነበር፡፡ ሉቃስ ሌሎች ስደትን ፈርተው ገሸሽ ባሉ ጊዜ ከጳውሎስ ያልተለየ ሰው ነበር፡፡ ከዚህ ውጪ ስለ ሉቃስ የምናውቃቸውን ነገሮች የምናገኘው ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ነው፡፡ (ዝኒ ከማሁ፣ ገፅ 336) |
ምርመራ
- አሁንም ከአንደኛ መጽሐፍ የጠቀሱትን ከሁለተኛ መጽሐፍ እንደሆነ በመግለፅ ስህተታቸውን ደግመዋል፡፡
- ሉቃስ የዚህ ወንጌል ደራሲ አለመሆኑን የሚያሳይ ጠንካራ መረጃ አለመገኘቱን የሚናገረውን አረፍተ ነገር ሆነ ብለው ቆርጠው አውጥተዋል፡፡
- ሉቃስ የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የቅርብ ወዳጅና በሙያው ኀኪም እንደነበረ የሚናገረውን ክፍል ቆርጠው በማስቀረት የማይታወቅ ሰው ለማስመሰል ጥረት አድርገዋል፡፡
አሕመዲን የጠቀሱት “ሉቃስ አይሁድ አልነበረም አንድን ሙሉ መጽሐፍ የጻፈ ብቸኛው አህዛብ ያደርገዋል፡፡ የት ተወልዶ እንዳደገ አናውቅም፡፡ በተጨማሪም ሉቃስ ጥሩ የታሪክ ጸሐፊ ነበር፡፡ ምንም እንኳ ኢየሱስን በዓይኑ ባያየውም፣ ሉቃስ እንደ አንድ የታሪክ ጸሐፊ ስላመነበት ስለ ክርስቶስ ጥንቃቄ የተሞላበት ጥናት አድርጓል፡፡ … ሉቃስ ይህንኑ መረጃ ለማግኘት የተጠቀመባቸውን መንገዶችን ይዘረዝርልናል፡፡ አንደኛው፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገሩ መዛግብትን አገላብጧል፡፡ ምናልባት ከእነዚህ መዛግብት መካከል የማቴዎስና የማርቆስ ወንጌላት ይገኙበት ይሆናል፡፡ ሁለተኛው፣ የዓይን ምስክሮችና የተከበሩ የቤተክርስቲያን መሪዎችን ቃለ መጠይቅ አድርጓል፡፡ …ሁሉንም መረጃ ካሰባሰበና ታሪኮቹን ፈር ካስያዘ በኋላ፣ ሉቃስ ስለ ክርስቶስ በሚጽፈው መጽሐፍ ውስጥ የትኞቹ መካተት እዳለባቸው ወሰነ፡፡”(ከላይ የተጠቀሰው መጽሐፍ ገፅ 337) |
በመጽሐፉ ውስጥ የሰፈረው ሙሉ ሐሳብ “ሉቃስ አይሁድ አልነበረም አንድን ሙሉ መጽሐፍ የጻፈ ብቸኛው አህዛብ ያደርገዋል፡፡ የት ተወልዶ እንዳደገ አናውቅም፡፡ የምዕራብ ቱርክ ሰው ቢሆንም በአንጾኪያ አካባቢ እንዳደገ የሚያስረዳ መረጃ አለ፡፡ ሐኪም እንደመሆኑ ፣ ሉቃስ የግሪክን ባሕል እንደተማረ ምንም አያጠራጥርም፡፡ በተጨማሪም ሉቃስ ጥሩ የታሪክ ጸሐፊ ነበር፡፡ ምንም እንኳ ኢየሱስን በዓይኑ ባያየውም፣ ሉቃስ እንደ አንድ የታሪክ ጸሐፊ ስላመነበት ስለ ክርስቶስ ጥንቃቄ የተሞላበት ጥናት አድርጓል፡፡ እርሱ ስደትና ሞትን መቀበል ካለበት ጽናቱ በተራ ወሬ ላይ ሳይሆን በእውነተኛ መረጃ ላይ እንዲደገፍ ፈልጎ ነበር፡፡ ሉቃስ ይህንኑ መረጃ ለማግኘት የተጠቀመባቸውን መንገዶችን ይዘረዝርልናል፡፡ አንደኛው፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገሩ በጽሑፍ የሰፈሩ መዛግብትን አገላብጧል፡፡ ምናልባት ከእነዚህ መዛግብት መካከል የማቴዎስና የማርቆስ ወንጌላት ይገኙበት ይሆናል፡፡ ሁለተኛው፣ የዓይን ምስክሮችና የተከበሩ የቤተክርስቲያን መሪዎችን ቃለ መጠይቅ አድርጓል፡፡ ለምሳሌ ሉቃስ የኢየሱስ እናት ከሆነችው ከማርያም ጋር በመነጋገሩ ምክንያት ታሪኳን ብቻ ሳይሆን በልቧ ውስጥ ስለነበረው ነገር ገልጾአል (ሉቃስ 2፡19)፡፡ ሁሉንም መረጃ ካሰባሰበና ታሪኮቹን ፈር ካስያዘ በኋላ፣ ሉቃስ ስለ ክርስቶስ በሚጽፈው መጽሐፍ ውስጥ የትኞቹ መካተት እዳለባቸው ወሰነ፡፡ እንደ ሌሎቹ የወንጌላት ጸሐፊዎች ሁሉ ታሪክን ብቻ አልጻፈም፡፡ ይልቁንም ስለ ክርስቶስ ለማስተማር ፈልጎ ነበር፡፡ ይህንንም ያደረገው ሰዎች ለእምነታቸው ጽኑ መሠረት እንዲኖራቸውና ክርስቶስን መከተል ማለት ምን ማለት እንደሆነ እርሱን እንዲያውቁ ለማድረግ ነበር፡፡ ሉቃስ መረጃውን በሚሰበስብበትና በሚጽፍበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ይመራው ነበር፤ ዛሬ በእጃችን ያለው ወንጌል በሰው የተጻፈ ታሪክ ብቻ ሳይሆን መንፈስ ቅዱስ እያንዳንዳችን እንድናውቅ፣ እንድናምንና ከሕይወታችን ጋር እንድናዛምድ የሚፈልገውን እውነት ሁሉ እንዲጽፍ አድርጎታል፡፡” ዝኒ ከማሁ፣ ገፅ 337 |
ምርመራ
- ምንጩን በተመለከተ ስህተታቸውን ለሦስተኛ ጊዜ ደግመዋል፡፡
- ሉቃስ በአንጾኪያ አካባቢ እንዳደገ የሚያሳይ መረጃ መኖሩን የሚናገረውን አረፍተ ነገር ቆርጠው አውጥተዋል፡፡
- በክርስትና እምነቱ የነበረው ፅናት በተራ ወሬ ላይ ሳይሆን በእውነተኛ መረጃ ላይ የተደገፈ እንዲሆን መፈለጉን የሚናገረውን አረፍተ ነገር ቆርጠው አውጥተዋል፡፡
- ሉቃስ በጽሑፍ የሰፈሩ መዛግብን በመረጃ ምንጭነት መጠቀሙን የሚናገረውን ሐረግ ቆርጠው አውጥተዋል፡፡
- ሉቃስ የጌታን እናት ማርያምን ማነጋገሩንና ከእርሷ መረጃ ማግኘቱን የሚናገረውን አረፍተ ነገር ቆርጠው አውጥተዋል፡፡
- ሉቃስ መረጃዎቹን ሲያሰባስብ መንፈስ ቅዱስ ይመራው እንደነበርና በመንፈስ ቅዱስ ምሪት መጻፉን የሚናገረውን ክፍል ቆርጠው አስቀርተውታል፡፡
አሕመዲን የጠቀሱት
የመጽሐፍ ቅድስ መዝገበ ቃላት እንዲህ ይላል፡- “የሉቃስ ወንጌል የተጸፈው በ60 ዓ.ም. ገደማ ይመስላል፡፡” (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ ገጽ 5) |
መጽሐፉ የሚለው ሉቃስ ወዳጁ ለሆነው ቴዎፍሎስ በአክብሮት ሲጽፍ ያላያቸውን ነገሮች ካዩአቸው የዓይን ምስክሮች አረጋግጦ በብዙ ጥንቃቄ ተርኳል፡፡ የአጻጻፉ ዘዴ የተማረና በድርሰት ልዩ ሙያ ያለው ሰው መሆኑን ያሳያል፤ ሉቃ. 1፡1-4፤ ሐ.ሥ. 1፡1-3፡፡ ሉቃስ የጻፈው ታሪክ የአርኪኦሎጂ ምርመራ ትክክለኛ መሆኑን ያሳያል፡፡ ጳውሎስ በሮም ታስሮ ሳለ “የሐዋርያትን ሥራ” በ64 ዓ.ም. ገደማ ከጻፈው ወንጌሉን ደግሞ ከዚህ በፊት በ62 ዓ.ም. ገደማ የጻፈ ይመስላል፡፡ (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ ገፅ 15) |
ምርመራ
- ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት “ገፅ 5” በማለት የጠቀሱት በተባለው ገፅ ላይ አይገኝም፡፡ ስለ ሉቃስ የሚናገረው ክፍል ገፅ 15 ላይ ይገኛል፡፡
- የተጻፈውን ቃል በቃል ካለመጥቀሳቸውም በላይ 62 ዓ.ም. የሚለውን ወደ 60 ዓ.ም. ለውጠውታል፡፡
- ይህ ክፍል ሉቃስ ከዓይን ምስክሮች አረጋግጦ እንደጻፈ፣ የተማረና በድርሰት ልዩ ሙያ የነበረው ሰው እንደሆነና እርሱ የጻፈው ታሪክ በአርኪኦሎጂ ምርመራ ትክክል መሆኑ የተረጋገጠ እንደሆነ ስለሚናገር አሕመዲን ጀበል ለሚነዙት ፕሮፓጋንዳ እጅግ አውዳሚ ነው፡፡ ለዚህ ነው ሊጠቅሱት ያልወደዱት፡፡