የዮሐንስ ወንጌልን በተመለከተ ጸሐፊው ተከታዮቹን ነጥቦች በክርስቲያኖች ከተጻፉ መጻሕፍት የጠቀሱት!

 


3. “በዮሐንስ ወንጌልና በሌሎች ሦስት ወንጌላት መካከል በግልጽ የሚታይ ልዩነት በመኖሩ የወንጌሉ  ተአማኒነት አጠያየቂ እንዲሆን ምክንያት ሆኗል፡፡ መልሱ ያለው ግን በወንጌሉ ምንጭና ዓላማ ላይ ነው፡፡ ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው ትዉፊት መሠረት ይህ ወንጌል የተጻፈው በዘብዴዎስ ልጅ በዮሐንስ እንደሆነ ይታመናል፡፡ የዘብዴዎስ ልጅ ዮሐንስ የመጨረሻው የሕይወት ዘመኑን ያሳለፈው በኤፌሶን ሲሆን ከጌታ ሐዋርያት መካከል የመጨረሻው ሰው ነበር፡፡ ምንም እንኳ ይህ አባባል ተቃውሞ ቢገጥመውም እስከ ዛሬ ድረስ ከተሰነዘሩ ሌሎች መላምቶች ውስጥ ይሄኛው ይበልጥ ተቀባይነት አለው፡፡ በመጀመሪያው ምዕተ ዓመት መጨረሻ አካባቢ ስለ ነበራቸው የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ የሚታወቀው በጣም በጥቂቱ በመሆኑ የዚህን ወንጌል አወቃቀር አስመልክቶ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ እጅግ አስቸጋሪ ሆኖአል፡፡” (ሜሪል ሲ.ቲኒ፣ የአዲስ ኪዳን ቅኝት፣ አሳታሚ፦ የኢትዮጵያ ቃለ ሕወት ቤተክርስታን የኮሚዮኒኬሽንና ስነ ጹሑፍ መምሪያ ገጽ 281)

አሕመዲን ጀበል የምሑራንን አቋም የሚጠቅሱበት መንገድ እጅግ ተዓማኒነት የጎደለው ነው፡፡ የአዲስ ኪዳን ሊቅ የሆኑት ዶ/ር ቴኒ የተለያዩ ምሑራን የሚሰነዝሯቸውን አስተያየቶች ባገናዘበ መልኩ ከላይ የተጠቀሰውን ሐሳብ ቢናገሩም ነገር ግን የዮሐንስ ወንጌል ተዓማኒ መሆኑንና በዮሐንስ በራሱ የተጻፈ መሆኑን በተመለከተ የደረሱበትን ድምዳሜ እንዲህ አስቀምጠዋል፡፡

“አራተኛው ወንጌል የተጻፈው በሐዋርያው ዮሐንስ ሳይሆን ስሙ ዮሐንስ ተብሎ በሚጠራ አንድ ማንነቱ የማይታወቅ ሰው ነው የሚለው ጽንሰ ሐሳብ መሠረት የለሽ ነው፡፡ ከኢራንየስ ዘመን ጀምሮ የነበሩ የቤተ ክርስቲያን አበው እንደመሰከሩት የዚህ ወንጌል ጸሐፊ ወንጌላዊው ዮሐንስ ነው፡፡ የእስክንድርያው ቀለሜንጦስ (190 ዓ.ም.)፣ አርጌንስ [ኦሪጎን] (220 ዓ.ም.)፣ ሂፓላይትስ [ሂጶሊጦስ] (225 ዓ.ም.)፣ ተርቱልያንና [ጠርጡሊያኖስ] (200 ዓ.ም.) የሙራቶራውያን ጽሑፍ (170 ዓ.ም.) በአንድነት የሚስማሙት የዮሐንስ ወንጌል ጸሐፊ የዘብዴዎስ ልጅ ዮሐንስ መሆኑን ነው፡፡”[7]

በተጨማሪም ዶ/ር ቴኒ የወንጌሉ ጸሐፊ የኢየሱስ ደቀመዝሙር የነበረ መሆኑን የሚያሳዩ አራት ማስረጃዎችን ከወንጌሉ ይዘት በመነሳት አስቀምጠዋል፡፡[8] የወንጌሉ ጸሐፊ ዮሐንስ ስለመሆኑ ፅኑ እምነት መኖሩንም አበክረው ይናገራሉ፡፡[9]

አሕመዲን የጠቀሱት

“ከአራቱ ወንጌሎች የትኞቹም ስለ ጸሐፊው የሚናገሩት ነገር እንደሌለ ቀደም ብለን ተመልክተናል፡፡ ነገር ግን ይህ መጽሐፍ ከተጸፈ በኋላ ብዙም ሳይቆይ “የዮሐንስ ወንጌል” የሚል ስያሚ ተሰጠው፡፡ በዚህ መንገድ አንባቢያን ጸሐፊው ማን እንደሆነ ሊያውቁ ይችላሉ፡፡ ከጥንት ጊዜ አንስቶ የቤተክርስቲያን መሪዎች የዘብዴዎስ ልጅ የሆነው ዮሐንስ አራተኛውን ወንጌል እንደጻፈ ያምኑ ነበር፡፡ ይህ አመለካከት በአብዛኛው የክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ተይዞ ቆይቷል፡፡ … ዛሬ ግን ብዙ ወንጌላውያን የሆኑ ምሁራን ይህንን ወንጌል ዮሐንስ እንደጻፈው ይጠራጠራሉ፡፡ (ቲም ፌሎስ የአዲስ ኪዳን መምሪያና ማብራሪያ በትምህርተ መለኮት ማስፍፊያ (ት.መ.ማ.) መልክ የተዘጋጀ፣ 1ኛ መጽሐፍ፣ ገፅ 440)

በመጽሐፉ ውስጥ የሰፈረው ሙሉ ሐሳብ

“ከአራቱ ወንጌሎች የትኞቹም ስለ ጸሐፊው የሚናገሩት ነገር እንደሌለ ቀደም ብለን ተመልክተናል፡፡[10] ነገር ግን ይህ መጽሐፍ ከተጻፈ በኋላ ብዙም ሳይቆይ “የዮሐንስ ወንጌል” የሚል ስያሜ ተሰጠው፡፡ በዚህ መንገድ አንባቢያን ጸሐፊው ማን እንደሆነ ሊያውቁ ይችላሉ፡፡ ከጥንት ጊዜ አንስቶ የቤተክርስቲያን መሪዎች የዘብዴዎስ ልጅ የሆነው ዮሐንስ አራተኛውን ወንጌል እንደጻፈ ያምኑ ነበር፡፡ ይህ አመለካከት በአብዛኛው የክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ተይዞ ቆይቷል፡፡ በ115 ዓ.ም. ኢግናቲየስ የተባለ የቤተ ክርስቲያን መሪ ከዮሐንስ ወንጌል ጠቅሶ ጽፎአል፡፡ ከእርሱ በኋላ መጽሐፍ የጻፉት ሌሎች ሰዎች ሐዋርያው ዮሐንስ ይህንን ወንጌል በኤፌሶን ሆኖ እንደጻፈው ገልጸዋል፡፡ በጥንት ጽሑፎች ውስጥ ዮሐንስ ይህንን መጽሐፍ እንደጻፈ የሚያጠራጥር ነገር የለም፡፡ ዛሬ ግን ብዙ ወንጌላውያን ያልሆኑ ምሁራን ይህንን ወንጌል ዮሐንስ እንደጻፈው ይጠራጠራሉ፡፡ ምክንያታቸውም ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ስለመሆኑ የቀረበው ትምህርት በጣም የጠነከረ ስለሆነ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በ100 ዓ.ም. ላይ ከዚህ ደረጃ መድረስ አትችልም የሚል ነው፡፡ … የዘብዴዎስ ልጅ የሆነው ዮሐንስ ይህንን መጽሐፍ እንደጻፈው የሚያስቡ ሰዎች የዘብዴዎስ ልጅ የሆነው ዮሐንስና ሽማግሌው ዮሐንስ አንድ ሰው ነው የሚል አሳብ አላቸው፡፡ ይህ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ያስተማረችው አሳብ ሲሆን ለመጠራጠር የሚያበቃ ምክንያት የለንም፡፡ (ቲም ፌሎስ የአዲስ ኪዳን መምሪያና ማብራሪያ በትምህርተ መለኮት ማስፍፊያ (ት.መ.ማ.) መልክ የተዘጋጀ፣ 1ኛ መጽሐፍ፣ ገፅ 440)

 

ምርመራ

  • ኢግናጢዮስ በ115 ዓ.ም. ከወንጌሉ ጠቅሶ መጻፉን፣ ከእርሱ በኋላ የነበሩት ሰዎች ዮሐንስ ወንጌሉን በኤፌሶን እንደጻፈ መግለፃቸውን፣ ወንጌሉ በዮሐንስ የተጻፈ መሆኑን የሚያጠራጥር ነገር እንደሌለ፣ ወዘተ. የሚናገሩትን አረፍተ ነገሮች ሆነ ብለው ቆርጠው አውጥተዋል፡፡
  • አሕመዲን ወንጌላውያን ምሑራን እንኳ ሳይቀሩ የዮሐንስ ወንጌል በዮሐንስ እንደተጻፈ የማያምኑ ለማስመሰል “ዛሬ ግን ብዙ ወንጌላውያን የሆኑ ምሁራን ይህንን ወንጌል ዮሐንስ እንደጻፈው ይጠራጠራሉ” በማለት ጽፈዋል፡፡ ነገር ግን “የሆኑ” የምትለዋ ቃል ራሳቸው ፈጥረው የተኳት እንጂ በቦታው ላይ እንደሌለች ልብ ይሏል፡፡ ጽሑፉ በትክክል የሚለው እንዲህ ነው፡- “ዛሬ ግን ብዙ ወንጌላውያን ያልሆኑ ምሁራን ይህንን ወንጌል ዮሐንስ እንደጻፈው ይጠራጠራሉ፡፡”

 

አሕመዲን የጠቀሱት

በዮሐንስ ወንጌል ጸሐፊ ማንነት ላይ የሚደረገው ክርክር የተጻፈበትን ቦታና ጊዜ ይወስነዋል፡፡ ይህ ወንጌል ወደ በኋላ እንደተጻፈ የሚያስቡ ሰዎች ጊዜውን ወደ 150 ዓ.ም. አከባቢ ይወስዱታል፡፡ ሌሎች ደግሞ የዮሐንስ ወንጌል ከ59-70 ዓ.ም. መጀመሪያ የተፃፉት መጽሐፍት አንዱ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ደራሲው አዛውንቱ ዮሐንስ ነው የሚሉትን ጨምሮ አብዛኛዎቹ ምሁራን ከ85-95 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ እንደተጻፈ ይስማማሉ፡፡” (ከላይ የተጠቀሰው መጽሐፍ ገፅ 444)

በመጽሐፉ ውስጥ የሰፈረው ሙሉ ሐሳብ

በዮሐንስ ወንጌል ጸሐፊ ማንነት ላይ የሚደረገው ክርክር የተጻፈበትን ቦታና ጊዜ ይወስነዋል፡፡ ይህ ወንጌል ወደ በኋላ እንደተጻፈ የሚያስቡ ሰዎች ጊዜውን ወደ 150 ዓ.ም. አከባቢ ይወስዱታል፡፡ ሌሎች ደግሞ የዮሐንስ ወንጌል ከ59-70 ዓ.ም. መጀመሪያ የተፃፉት መጽሐፍት አንዱ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ደራሲው አዛውንቱ ዮሐንስ ነው የሚሉትን ጨምሮ አብዛኛዎቹ ምሁራን ከ85-95 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ እንደተጻፈ ይስማማሉ፡፡ በምሑራን እጅ የሚገኘው የዮሐንስ ወንጌል ጥንታዊ ቅጂ በ125 ዓ.ም. የተገለበጠ ነው፡፡” ( ዝኒ ከማሁ፣ ገፅ 444)

ምርመራ

  • በምሑራን እጅ የሚገኘው የዮሐንስ ወንጌል ጥንታዊ ቅጂ በ125 ዓ.ም. የተገለበጠ መሆኑን በመግለፅ ከ150 ዓ.ም. በኋላ እንደተጻፈ የሚገምቱትን ሰዎች መላ ምት ውድቅ የሚያደርገውን አረፍተ ነገር ሆነ ብለው ቆርጠው አስቀርተውታል፡፡

በማስከተል አሕመዲን ጀበል እንዲህ በማለት ይጠይቃሉ፡-

“ስለ ዮሐንስ ወንጌል ካሉት አለመግባባቶች መካከል ለአብነት ከላይ አይተናል፡፡ ነገር ግን ተራው አማኝ እርግጠኛነት እንዲሰማው ስለተደረገ በጭፍን ሲከራከር ይስተዋላል፡፡ ወንጌሉ በማንና መቼ እንደተጻፈ ቁርጥ ያለ መረጃ የሌለበት ተአማኒነቱ አጠያያቂ በሆነበት ሁኔታ “የአምላክ ቃል ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ጻፉት ወዘተ.” ማለት ምን ያህል ያዛልቃል፡፡ የወንጌሉ ተአማኒነት ላይ ጥያቄ እያለ እንዲህ ያለውን መረጃ በመሰወር “ተራውን አማኝ” ማደናገር ለምን አስፈለገ?”

የሜሪል ቴኒ መጽሐፍም ሆነ የት.መ.ማ. መጻሕፍት ለአጠቃላይ አማኞች የተዘጋጁ በመሆናቸው “መረጃ መሰወር” የሚለው የአሕመዲን ጀበል ክስ መሠረተ ቢስ ነው፡፡ የቴኒ መጽሐፍ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ጥቅም ሲባል ተተርጉሞ በመጻሕፍት መደብሮች ውስጥ እየተሸጠ ይገኛል፡፡ የት.መ.ማ. መጻሕፍት ደግሞ ትምህርተ መለኮትን ለእያንዳንዱ አማኝ በቤቱ ለማድረስ በማለም የተዘጋጁ ናቸው፡፡ እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ እያንዳንዱ አማኝ ጋር እንዲደርሱ ታልመው በተዘጋጁ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙ ሐሳቦችን ከጠቀሱ በኋላ እነዚህኑ ጉዳዮች “በመሰወር” እና አማኞችን “በማደናገር” ክርስቲያን መሪዎችን መወንጀል እንዲሁም የእነዚህን ሊቃውንት ጽሑፎች በመቆራረጥ እና ዓላማቸውን በማጣመም የወንጌሉ ተዓማኒነት ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ማስመሰል በእውነቱ ከሆነ ከአንድ የሃይማኖት አስተማሪ የማይጠበቅ ነውረኛ ተግባር ነው፡፡ አፀፋ መመለስ ባይሆንብንም የቅዱስ መጽሐፋቸውን ተዓማኒነት በተመለከተ አማኞቻቸውን እያደናገሩ የሚገኙት እነማን እንደሆኑ ከአፍታ በኋላ ስለምንመለከት እውነቱ ግልፅ ይሆናል፡፡

የዮሐንስ ወንጌል ዘግይቶ እንደተጻፈ የሚናገሩ የለዘብተኛ ሥነ መለኮት ሊቃውንት የተጨበጠ የሰነድ ማስረጃ ኖሯቸው ሳይሆን ሥነ መለኮታዊ ይዘቱ ከፍ ያለ በመሆኑ እንዲህ ያለ የተደራጀ ሥነ መለኮት ያለው ጽሑፍ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን የተጻፈ ሊሆን አይችልም ከሚል ግምት በመነሳት ነው፡፡ ነገር ግን በሃምሳዎቹ ውስጥ በሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደተጻፈ ሊቃውንት በአንድ ድምፅ የሚስማሙበት የሮሜ መልዕክት[11] ከዮሐንስ ወንጌል የጠለቀ ሥነ መለኮታዊ ይዘት የሚታይበት በመሆኑ ይህ ሙግት አሳማኝ አይደለም፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ በግብፅ ነጅ ሐማዲ በተባለ ስፍራ የተገኘው p52 ወይም “ጆን ሪላንድ ፐፓይረስ” የሚል መጠርያ የተሰጠው የዮሐንስ ወንጌል ክፍል ወንጌሉ ዘይግይቶ በሁለተኛው ክፍለ ዘመን እንደተጻፈ የሚናገሩትን ወገኖች መላ ምት ሙሉ በሙሉ ውድቅ ያደርጋል፡፡ ዮሐንስ 18፡31-33፣ 37-38 የያዘው ይህ ጽሑፍ መጠኑ አነስተኛ ቢሆንም ዕድሜው በ114-138 ዓ.ም. መካከል መሆኑ ስለተረጋገጠ ወንጌሉ በአንደኛው ክፍለ ዘመን የተጻፈ መሆኑን ከጥርጣሬ በፀዳ ሁኔታ ያረጋግጣል፡፡ በትንሹ ኢስያ የተጻፈ መጽሐፍ በ114-138 ዓ.ም. መካከል በወዲያኛው የሜድትራንያን ባሕር ጫፍ በሚገኙ ትንንሽ ከተሞች ውስጥ የሚዘዋወር ከሆነ በአንደኛው ክፍለ ዘመን ለመጻፉ ምንም ጥርጥር የለውም![12]