የማቴዎስ ወንጌልን በተመለከተ ያነሷቸው ነጥቦች!

 


አሕመዲን የጠቀሱት

ስለ ማቴዎስ ወንጌል በክርስቲያን ምሑራን የሚከተለው ተጽፏል፡-

“የማቴዎስ ወንጌል፡- “ወንጌሉን የጻፈው ማቴዎስ ነው” ያሉት የቀደሙ የቤተክርስቲያን አባቶች ናቸው እንጂ የጻፈው ስም አልተጻፈበትም፡፡ መች እንደተጻፈ አልታወቀም፡፡” ቲቶ (ጥጦስ) በሚባል በሮማ መንግሥት የጦር መሪ እጅ ኢየሩሳሌም የፈረሰችው በ70 ዓ.ም. ሲሆን ወንጌሉ ከዚያ በፊት ወይም ከዚያ በኋላ ተፅፎ እንደሆነ መምህራን አልተስማሙበትም፡፡ በ60 ዓ.ም. እና 80 ዓ.ም. መካከል ሳይፃፍ አይቀርም ይባላል፡፡ (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር፣ ገፅ 41)

መጽሐፉ የሚለው

“እንደ ጥንት ቤ.ክ. ትውፊት የመጀመርያውን ወንጌል የጻፈው ማቴዎስ ነው፡፡ ዛሬ አንዳንድ ሊቃውንት ይህን ሐሳብ ባይቀበሉትም የወንጌሉ አጻጻፍ በጥንቃቄ ከሚጽፍና ከሚሠራ ወደ ወንጌላዊነት ከተለወጠ ቀራጭ አሠራር ጋር ይስማማል፡፡ የማቴዎስ ወንጌል የተጻፈባቸው ዘመናት በብዙ ሊቃውንት የተለያዩ እንደሆኑ ቢጠቀስም አንዳንዶች ማቴዎስ ወንጌሉን የጻፈው ከ50 ዓ.ም. በፊት እንደሆነ ሲያመለክቱ ሌሎች ግን ጸሐፊው የማርቆስን ወንጌል ተመልክቶ ኢየሩሳሌም ከወደቀችበት ከ70 ዓ.ም. በኋላ እንዳዘጋጀው ይናገራሉ፡፡” (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር፣ ገፅ 53)

 

ምርመራ

  • የተጠቀሰው የመዝገበ ቃላቱ ገፅ ላይ አሕመዲን ጀበል ያሰፈሩት ሐሳብ በዚህ መልኩ አልተጻፈም፡፡ “ማቴዎስ” የሚለው ማውጫ ገፅ 52-53 ላይ የሚገኝ ሲሆን አሕመዲን ከጠቀሱት የተለየ ነው፡፡ ሰውየው ያሳዩት የጥንቃቄ ጉድለትና አንባቢያንን ለማሳሳት ያደረጉት ጥረት አሳፋሪ ነው፡፡

 

አሕመዲን የጠቀሱት

ስለ ማቴዎስ ወንጌል ክርስቲያን ምሑራን ሲገልጹ፡- “ከስሙና ከሚሠራው ሥራው በቀር ስለዚህ ሰው በውል የታወቀ ነገር የለም፡፡ ይህ ሰው በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ከሐዋርያት የስም ዝርዝር ውስጥ ከመጠቀሱ በስተቀር፡፡ (የሐዋ. ሥራ 1፡13) ታሪኩን በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ በግልፅ አናገኘውነኘውም፡፡ በአፈ ታሪክ ጽሑፎች ውስጥ ግን የተባሉ ነገሮች መኖራቸውን ልብ ይሏል፡፡ በወንጌሉ ውስጥ ማቴዎስ ጸሐፊው እንደሆነ አልተናገረም፡፡ (ሜሪል ሲ. ቴኒ፣ የአዲስ ኪዳን ቅኝት፣ ገፅ 217)

በመጽሐፉ ውስጥ የሰፈረው ሙሉ ሐሳብ

“በታሪክ የመጀመርያውን ወንጌል እንደጻፈ የሚነገርለት ቀረጥ ሰብሳቢ ወይም ሕዝብን ያማከለ ሙያ የነበረው የሌዊ ልጅ ማቴዎስ ሲሆን ይህ ሰው ከአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት መካከል አንዱ ይሆን ዘንድ ኢየሱስ መርጦታል፡፡ ከስሙና ከሚሠራው ሥራው በቀር ስለዚህ ሰው በውል የታወቀ ነገር የለም፡፡ ይህ ሰው በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ከሐዋርያት የስም ዝርዝር ውስጥ ከመጠቀሱ በስተቀር፡፡ (የሐዋ. ሥራ 1፡13) ታሪኩን በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ በግልፅ አናገኘውም፡፡ በአፈ ታሪክ ጽሑፎች ውስጥ ግን የተባሉ ነገሮች መኖራቸውን ልብ ይሏል፡፡ በወንጌሉ ውስጥ ማቴዎስ ጸሐፊው እንደሆነ አልተናገረም፡፡ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊዎች ማቴዎስ እንደጻፈው ግን አረጋግጠዋል፡፡ በአረማይክ ቋንቋ ይተረጉመው እንደነበረ ጳጲያስ (100 ዓ.ም.) መናገሩን አውሳቢየስ [ኢዮስቢዮስ] (325 ዓ.ም.) የተባለ ሰው ጠቅሷል፡፡ ከአውሳቢያስ 150 ዓመት ቀደም ብሎ የኖረው ኢራኒዮስ የተባለ ሰው ሲገልፅ “ጴጥሮስና ጳውሎስ በሮም እየሰበኩ የቤተ ክርስቲያንን መሠረት በሚጥሉበት ዘመን ማቴዎስ ደግሞ በዕብራውያን ቋንቋ የተጻፈውን ወንጌል ለዕብራውያን አበርክቶ ነበር” ብሏል፡፡ የመጀመርያውን ወንጌል መነሻ በተመለከተ ከእነኚህ ጥንታዊ ገለፃዎች ብዙ ማጠቃለያ አሳቦች ማግኘት ይቻላል፡፡ አንደኛ የማቴዎስ ጸሐፊነት የሚያከራክር አይደለም፤…

ቴኒ፣ የአዲስ ኪዳን ቅኝት፣ ገፅ 217-218

ምርመራ

  • የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊዎች ወንጌሉን ማቴዎስ እንደጻፈው ማረጋገጣቸውን፣ 100 ዓ.ም. አካባቢ ፓፒያስ ወንጌሉ በማቴዎስ የተጻፈ መሆኑን መናገሩን፣ 150 ዓ.ም. አካባቢ ኢሬኔዎስ ተመሳሳይ ምስክርነት መስጠቱን፣ የወንጌሉ ጸሐፊ ማቴዎስ መሆኑ የማያከራክር መሆኑን፣ ወዘተ. የሚገልፁትን አረፍተ ነገሮች በሙሉ ቆርጠው ጥለዋል፡፡
አሕመዲን የጠቀሱት

ወንጌሉ የተጻፈበት ስፍራ እንጾኪያ ሊሆን ይችላል፡፡ … በተጨማሪም በአንጾኪያ የነበረችይቱ ቤተክርስቲያን በአመዛኙ አሕዛብን በውስጧ በማቀፏ የመጀመሪያ ብትሆን ወንጌሉም የት ተጻፈ ለሚለው ሁነኛ ማረጋገጫ ባይገኝለትም ከአንጾኪያ የተሻለ ተስማሚ ቦታግን አይታሰብም፤ … ስለዚህ ወንጌሉ ከ50-70 ዓ.ም. ባሉ ጊዜያት መካከል ሳይጻፍ እንዳልቀረና በአንጾኪያ  ቤተ ክርስቲያ ውስጥ በሚሰሩትና በዚያች ቤተ ክርስቲያን በሆኑቱ መካከል እንደተሰራጨ ይገመታል፡፡ (ከላይ የተጠቀሰው መጽሐፍ፣ ገፅ 220)

በመጽሐፉ ውስጥ የሰፈረው ሙሉ ሐሳብ

ወንጌሉ የጻፈበት ስፍራ እንጾኪያ ሊሆን ይችላል፡፡ እንደ ጵጲያስ እና ኢግናትየስ [ኢግናጢዮስ] በመሳሰሉ ጥንታዊ የአባቶች ጽሑፍ ውስጥ የተጠቀሱ የወንጌል ጥቅሶች ከማቴዎስ ወንጌል ጋር እጅግ በተቀራረበ ሁኔታ የሚስማሙ ሲሆን ይህ የመጀመርያው ወንጌል ሳይሮ አይሁድ [የሦርያ አይሁድ] ቤተ ክርስቲያን ዘንድ እጅግ የተወደደ እንደነበረ ያሳያል፡፡ በተጨማሪም በአንጾኪያ የነበረችይቱ ቤተክርስቲያን በአመዛኙ አሕዛብን በውስጧ በማቀፏ የመጀመሪያ ስትሆን ወንጌሉም የት ተጻፈ ለሚለው ሁነኛ ማረጋገጫ ባይገኝለትም ከአንጾኪያ የተሻለ ተስማሚ ቦታግን አይታሰብም፤ በተጨማሪም በከተማዋ የአረማይክና የግሪክ ቋንቋ መነገሩንም ልብ ይሏል፡፡ ስለዚህ ወንጌሉ ከ50-70 ዓ.ም. ባሉ ጊዜያት መካከል ሳይጻፍ እንዳልቀረና በአንጾኪያ  ቤተ ክርስቲያ ውስጥ በሚሰሩትና በዚያች ቤተ ክርስቲያን በሆኑቱ መካከል እንደተሰራጨ ይገመታል፡፡ (ቴኒ፣ ገፅ 220)

በማስከተል አሕመዲን እንዲህ በማለት ይጠይቃሉ፡- “ታዲያ እንዴት በግምትና በ”ሊሆን ይችላል”አፈታሪክና የክርስቲያን ምሁርራን ራሳቸው ባላወቁትና ባልተስማሙበት ፅሁፍ እንዴት ‹‹የአምላክ ቃል ነው እመኑ›› ይባላል?”

የማቴዎስ ወንጌል በሐዋርያው ማቴዎስ እንደተጻፈ የሚያረጋግጡትን መረጃዎች ቆርጠው በመጣል ስለ ማቴዎስ ግለ ታሪክ በአዲስ ኪዳን ውስጥ አለመጻፉን በተመለከተ የተባለውን ብቻ ስለጠቀሱ እንጂ ሙሉ መረጃው ዓላማቸውን የሚደግፍ አይደለም፡፡ የጸሐፊያኑን ሐሳብ ቆራርጠው በማቅረብ ከፈጠሩት የተሳሳተ ምስል በመነሳት የጠየቁት ይህ ጥያቄ መሠረት አልባ መሆኑ ከላይ በሳጥኖቹ ውስጥ በንፅፅር በቀረቡት መረጃዎች ተጋልጧል፡፡