የማርቆስ ወንጌልን በተመለከተ የሚከተሉትን ነጥቦች አንስተዋል

 


5. “ከሌሎች ጋር ሲነጻጸር ስለዚህኛው ወንጌል ጸሐፊ ብዙ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ መጽሐፉ በየትኛውም ሥፍራ ስሙን አይጠቅስም፤ …የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚገልፀው ጸሐፊው የክርስቲያን ቤተሰብ አባል የሆነ ዮሀንስ ማርቆስ መሆኑንና የጳውሎስ፣ የበርናስና ምናልባትም የጴጥሮስ ረዳትና ተማሪ ሳይሆን እንዳልቀረ ይገመታል፡፡” (ሜሪል ሲ ቴኒ፣ የአዲስ ኪዳን ቅኝት ገፅ 236)

ተርጓሚዎቹ የደራሲውን ሐሳብ በትክክል ካለመተርጎማቸው የተነሳ ከላይ አሕመዲን የጠቀሱት ክፍል የተሳሳተ ምልከታን ይሰጣል፡፡ ቴኒ የጻፉት የእንግሊዘኛ ጽሑፍ እንዲህ ይነበባል፡- “Traditions identify him as John Mark, the scion of a Christian family in Jerusalem, the assistant and understudy of Paul, Barnabas and perhaps Peter. He was the son of Mary, a friend of the apostles, who is mentioned in Acts 12.”

ትርጉም፡- “በኢየሩሳሌም ከሚኖር ክርስቲያን ቤተሰብ የተገኘ የጳውሎስና የበርናባስ፣ ምናልባትም የጴጥሮስ ረዳትና ደቀ መዝሙር የሆነው ዮሐንስ ማርቆስ መሆኑ በትውፊቶች ተገጿል፡፡ የሐዋርያት ወዳጅ የሆነችው በሐዋርያት ሥራ 12 ላይ የተጠቀሰችው የማርያም ልጅ ነበር፡፡”

በዚህ ቦታ “በምናልባትነት” የተቀመጠው የጴጥሮስ ረዳትና ደቀ መዝሙር የመሆኑ ጉዳይ እንጂ ሌሎች መረጃዎች አይደሉም፡፡ ማርቆስን የተመለከተ በ115 ዓ.ም. የተነገረ ከፓፒያስ የተገኘ መረጃ ኢዮስቢዮስ (375 ዓ.ም.) በጻፈው ጽሑፍ ውስጥ ተጠብቋል፡፡ ይህ መረጃ በቀዳሚነት የተላለፈው ከሽማግሌው ከዮሐንስ (ከሐዋርያው ዮሐንስ) ሲሆን፤ ማርቆስ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ ደቀ መዝሙር ባይሆንም የጴጥሮስ አስተርጓሚ የነበረ መሆኑን፤ ቅደም ተከተል ባይጠብቅም መረጃዎቹን ሳይጨምርና ሳይቀንስ ያለ አንዳች ስህተት በታላቅ ጥንቃቄ መጻፉን ያስነብበናል፡፡[13] የጸሐፊውን ማንነት በተመለከተ አበው ስለሰጡት መረጃ ተዓማኒነት ቴኒ እንዲህ ይላሉ፡-

“የእነኚህ ታሪኮች አስተማማኝነት አጠያያቂ ሊሆን አይችልም፡፡ የሁለተኛው ወንጌል ጸሐፊ ማርቆስ መሆኑን ሁሉም ተስማምተዋል፤ ወንጌሉንም ከጴጥሮስ ስብከት ጋር ያያይዙታል፡፡”[14]

አሕመዲን የጻፉት

“የማርቆስ ወንጌል ደራሲው (ጸሐፊው) በሮማይስጥ ማርቆስ የተባለውን ዮሐንስ ነው፡፡
(የሐዋ. 12:12:25… 15:37)፡፡ መጀመሪያ  የተጻፈው ወንጌል ይህ ሳይሆን አይቀረም፡፡ የቀደሙት የቤተክርስቲያን አባቶች በሮሜ ተጽፎአል፡፡ የተጻፈውም በ60 ዓ.ም. ገደማ ይመስላል ይላሉ፡፡” (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር፣ ገፅ 50)

መጽሐፉ የሚለው

የጠቀሱት የመዝገበ ቃላቱ ገፅ ላይ አሕመዲን ጀበል ያሰፈሩት ሐሳብ በዚህ መልኩ አልተጻፈም፡፡ “ማርቆስ” የሚለው የመዝገበ ቃላቱ ማውጫ ገፅ 50 ላይ የሚገኝ ሲሆን ስለ ጸሐፊው ማንነትና ወንጌሉ ስለተጻፈበት ዘመን እንዲህ ይላል፡-

ማርቆስ ወንጌልን እንደጻፈ የቤ.ክ. አባቶች ይናገራሉ፡፡ በአይሁድ ዘንድ ስሙ ዮሐንስ ሲሆን በሮማውያን ዘንድ ማርቆስ ይባላል፡፡ እናቱ ማርያም ትባላለች፤ ሐ.ሥ. 12፡12፡፡ ቤትዋ በኢየሩሳሌም ነበር፡፡ ምዕመናን በቤትዋ ለጸሎት ይሰበሰቡ ነበር፤ ሐ.ሥ. 12፡12-17፡፡ አጎቱ በርናባስና ጳውሎስ ለስብከት ሥራ ሲጓዙ ማርቆስ ያገለግላቸው ነበር፤ ቆላ. 4፡10፤ ሐ.ሥ. 12፡25፡፡ ከእነርሱ ጋር እስከ ጴርጌ ሄዶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ፤ ሐ.ሥ. 13፡13፡፡ ጳውሎስና በርናባስ በእርሱ ምክንያት ሲለያዩ ማርቆስ ከበርናባስ ጋር ወደ ቆጵሮስ ሄደ፤ ሐ.ሥ. 15፡36-39፡፡ በኋላ ግን ጳውሎስ አመስግኖታል፤ ቆላ. 4፡10፣ 2ጢሞ. 4፡11፣ ፊልሞና 24፡፡ ማርቆስ ከጴጥሮስ ጋር ሰርቷል፤ 1ጴጥ. 5፡13፡፡ ብዙ ሊቃውንት በማርቆስ 14፡51-52 ላይ የተጠቀሰው ወጣት ማርቆስ ነው ይላሉ፡፡ በእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያንን እንደመሠረተ አበው ይናገራሉ፡፡ እስካሁን የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን አባት ይባላል፡፡

የማርቆስ ወንጌል፤ ጸሐፊው ማርቆስ የተባለው ዮሐንስ ነው፡፡ የቀደሙት የቤ.ክ. አባቶች ይህ ወንጌል ለሮማውያን በ60 ዓ.ም. ገደማ በሮም ሳይጻፍ እንዳልቀረ ጠቁመዋል፡፡ የተጻፈውም ሮማውያን ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እንዲያምኑ ነው፤ ወንጌሉ ሮማዊ የሆነ መቶ አለቃ እንዴት እንዳመነ ይተርካል፤ 1፡1፣ 15፡39፡፡ ብዙዎች “ማርቆስ የሐዋርያው ጴጥሮስ የመንፈስ ልጅ ነውና ይህ ወንጌል ጴጥሮስ ያስተማረው ነው” ይላሉ፡፡ (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር፣ ገፅ 50)

አሕመዲን እንዲህ በማለት ይጠይቃሉ፡-

የተጨበጠ ማስረጃ የሌለበት በመላምትና በግምት “የማርቆስ” ወንጌል የአምላክ ቃል ነው፡፡ ማለት ይቻላልን?

የማርቆስ ወንጌል በአርባዎቹ መጨረሻ ወይም ከስድሳዎቹ በፊት እንደተጻፈ የሚያሳዩ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ወንጌሉ ከ70 ዓ.ም. በኋላ እንደተጻፈ የሚያምኑ ወገኖች በ13ው ምዕራፍ ላይ ኢየሱስ ስለ ኢየሩሳሌም ውድቀት በዝርዝር የተናገረው ትንቢት ከከተማዋ ውድቀት በፊት የተጻፈ ሊሆን አይችልም ከሚል ግምት በመነሳት ነው፡፡ የነዚህ ሰዎች ሙግት ሙሉ በሙሉ ያረፈው ኢየሱስ ስለ መጪው ሁኔታ እንደዚያ ዓይነት ዝርዝር ትንቢቶችን ሊናገር አይችልም በሚል እምነት ላይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ግለሰቦቹ በልዕለ ተፈጥሯዊ ኃይል ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ የሚያሳይ እንጂ ኢየሱስ ትንቢቱን ላለመናገሩ ማስረጃ የሚሆን አይደለም፡፡[15] ቀደም ሲል እንደተባለው የሊቃውንት ትኩረት ወንጌላት በተጻፉበት ቁርጥ ያለ ዓመት ላይ ሳይሆን በተጻፉበት ዘመን ላይ በመሆኑ የማርቆስ ወንጌል ከ70 ዓ.ም. በኋላ እንደተጻፈ ብንቀበል እንኳ የመስቀሉ ትውልድ ከማለፉ በፊት ስለሚሆን ስለ ክርስቶስ በሚሰጠው ምስክርነት ላይ ሙሉ በሙሉ ልንተማመን እንችላለን፡፡

ጸሐፊው ስሙ በተደጋጋሚ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተጠቀሰው ማርቆስ ዮሐንስ ስለመሆኑ በጥንት የቤተ ክርስቲያን አባቶች ጽሑፎች ውስጥ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ምስክርነቶች እናገኛለን፡፡ ኢሬኔዎስ፣ ጠርጡሊያኖስ፣ የእስክንድርያው ቀለሜንጦስ፣ ኦሪጎን፣ ጀሮም እና የሙራቶራውያን ቀኖና የዚህ ወንጌል ጸሐፊ ማርቆስ ዮሐንስ የተሰኘው የሐዋርያው ጴጥሮስ ደቀመዝሙር መሆኑን ይመሰክራሉ፡፡ የወንጌሉ ጸሐፊ ማርቆስ መሆኑን የሚያወሳው ቀዳሚ ምስክርነት ከመጀመርያው ክፍለ ዘመን የተገኘ ሲሆን መስካሪው ብዙዎች ሐዋርያው ዮሐንስ መሆኑን የሚያምኑት “ሽማግሌው ዮሐንስ” ነው፡፡ መረጃው የተገኘው ፓፒያስ ከተሰኘ ሐዋርያዊ አባት ሲሆን ኢዮስቢዮስ በሦስተኛው ክፍለ ዘመን መጀመርያ ላይ በጻፈው የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ መዝግቦታል፡፡[16]

አሕመዲን ጀበል እንዲህ በማለት ይጠይቃሉ፡-

“ወሳኝ” የሚባሉት አራቱ ወንጌላት ይህን ያህል አጨቃጫቂ፣ ስምምነት የሌላቸውና ጸሐፊያቸው እንኳ ያልታወቀ ከሆነ የሌሎች መጽሐፍት እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?

ክርስቲያን ምሑራን በአዲስ ኪዳን ጽሑፎች ላይ የተጋነነ ጥርጣሬ ያላቸውን የለዘብተኛ ሥነ መለኮት ምሑራን (Libral Scholars) አስተያየቶችንም ሆነ የአጥባቂ ሊቃውንት (Conservative Scholars) አስተያየቶችን ያገናዘቡ መረጃዎችን በታማኝነት ለአማኞች ለማስተላለፍ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ከላይ የተጠቀሱትን ዓይነት ጽሑፎች ይጽፋሉ፡፡ ነገር ግን ከክርስትና አኳያ ሲታይ የወንጌላቱን ጸሐፊያን ማንነት እንድንጠራጠር የሚያበቃን ምንም ነገር የለም፡፡ እያንዳንዱ ወንጌል የጸሐፊው ማንነት በሁለተኛውና በሦስተኛ የክርስቲያን ትውልዶች ስለተመሰከረላቸው፤ በተጨማሪም እስካሁን በእጃችን የሚገኙት ቀዳሚያን ጽሑፎች እነዚህ ወንጌላት አሁን በሚታወቁት ሰዎች የተጻፉ እንዳልሆኑ የሚጠቁም ነገር ስለሌላቸው (እንዲያውም በተቃራኒው የጸሐፊያኑን ስሞች ይዘው በመገኘታቸው) ያልተገባ ጥርጣሬና ሥጋት ውስጥ መግባት ምክንያታዊ አይደለም፡፡ አሕመዲን እንዳደረጉት የእነዚህን ክርስቲያን ምሑራን አስተያየቶች ከአውድ ውጪ ካልተረጎምን በስተቀር ወንጌላት አጠራጣሪ እንደሆኑ የሚያሳስብ የተጨበጠ መረጃ የለም፡፡ የፈጠራ ጽሑፎች ተዓማኒነታቸውን ከፍ ለማድረግ ታዋቂ በሆኑት ሰዎች ስም እንደሚጻፉ ይታወቃል፡፡ ከዮሐንስ በስተቀር የተቀሩት ሦስቱ ጸሐፊያን በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የጎላ ተፅዕኖ ስላልነበራቸው እነዚህ መጻሕፍት በተባሉት ሰዎች የተጻፉ ባይሆኑ ኖሮ በእነዚህ ሰዎች ስም መሰየም አስፈላጊ ባልሆነም ነበር፡፡