ለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ “ብሉይና አዲስ ኪዳን” የሚባለው መጽሐፍ ከየት ተገኘ?

 


አሕመዲን ጥያቄዎቻቸውን ይቀጥላሉ፡-

6. የክርስቲያን ምሑራን እንዲህ ጽፈዋል፡፡ “ከመጀመሪያ ጀምሮ ቤተክርስቲያን አይሁድ ያወቋቸውን የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ተቀበለች፡፡ በሐዋርያት ወይም በሐዋርያት ሥልጣን የተጻፉትን መጽሐፍት ሰብስባ እንደ እግዚአብሔር ቃል ተቀበለቻቸው፡፡ የቤተክርስቲያን አባቶች የአዲስ ኪዳን መጽሐፍትን እየጠቀሱ አስተማሩ፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ በ367 ዓ.ም በጻፈው በፋሲካ ዕለት ቃል በረከት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ሃያ ሰባት ብቻ መሆናቸውን ተናግሮአል፡፡ እንደዚሁም በ397 ዓ.ም በካርታ (በካርቴጅ) የተደረገው ሲኖዶስ ሃያ ሰባቱን መጻሕፍት አጸደቀ፡፡” (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ፣ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኀበር፡፡ ገጽ 35)

በግርጌ ማስታወሻ ደግሞ እንዲህ የሚል ነጥብ አክለዋል፡-

“ከላይ እንዳየነው በዶክተር ፓውል እንዝ የተጻፈው “ታሪካዊ ሥነ-መለኮት አመጣጡና ትንተናው” የሚለው መጽሐፍ አትናቴዎስ በ387 ዓ.ም እንደጻፈ ገልጾዋል፡፡ ነገር ግን የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ጊዜውን 367 ያደርገዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው 27ቱን የአዲስ ኪዳን መጻሐፍት በደብዳቤው ላይ ጻፈ የሚባለው አትናቴዎስ የጻፈበት ጊዜም በውል አለመታወቁን ነው፡፡ ይህንን ነው እንግዲህ የካርቴጅ ጉባኤ ሳይወያይ ያጸደቀው፡፡”

ትክክለኛው ዓመት 367 ሲሆን የመጽሐፉ ተርጓሚዎች 387 ማለታቸው የትየባ ስህተት ነው፡፡ የቅዱስ አትናቴዎስ ጽሑፍ የተጻፈበትን ዘመን በተመለከተ በታሪክ ምሑራን መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት ባለመኖሩ ጠያቂው በተርጓሚዎቹ ስህተት ላይ ተመስርተው ያቀረቡት አንካሳ ሙግት ቦታ የሚሰጠው አይደለም፡፡ ተርጓሚዎቹ ራሳቸው በዚሁ መጽሐፍ ገፅ 30 ላይ “አትናቴዎስ ደግሞ በ367 ዓ.ም. ሁሉንም የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት አስመዘገበ” በማለት ትክክለኛውን ዓመት አስቀምጠዋል፡፡ ጠያቂው ለክርክራቸው የሚመቻቸውን ሐሳብ ለመቃረም እንደ ፌንጣ ከገፅ ገፅ እየዘለሉ ከሚያነቡ መጽሐፉን በሞላ በእርጋታና በሰከነ መንፈስ ቢያነቡ ኖሮ ያለፈውን ስህተትና ይኸኛውን በማገናዘብ ከተሳሳተ ድምዳሜ በዳኑ ነበር፡፡ የካርቴጅ ጉባኤ መወያየት ያላስፈለገው መጻሕፍቱ ከዚያ ቀደም ተቀባይነት ያገኙ ስለነበሩና ለእንግዳ አመለካከቶች ክፍተት ላለመስጠት ኦፊሴላዊ ውሳኔ ማውጣት ስለነበረባቸው ብቻ ስለተሰበሰቡ ነበር፡፡ የመጻሕፍቱ ቀኖናዊነት ቀደም ሲል ስለታመነበት የውሳኔ ቃል እንጂ ውይይት አስፈላጊ አልነበረም፡፡

  • ከዚህ የምንረዳው ቤተክርስቲያን ከመጽሐፉ ቀድማ መመስረቷን፤ “ብሉይ ኪዳን” የሚባለው ከአይሁድ እንደተገኘና ሃያ ሰባቱ (የአዲስ ክዳን) መጻሕፍት 397 ዓ.ል በካርቴጅ ጉባኤ መጽደቃቸውን ነው፡፡

በእርግጥ ቤተ ክርስቲያን በ33 ዓ.ም. በበዓለ ሃምሳ ዕለት ነበር በሐዋርያት የተመሠረተችው፡፡ በዚያን ወቅት ደግሞ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት አልተጻፉም ነበር፡፡ ሐዋርያት ጌታችን ያስተማራቸውን ትምህርቶችና ታሪኮቹን ከትውስታቸው ያስተምሩ ነበር፡፡ እነዚህን ትምህርቶችና ታሪኮች በመጻሕፍት ማስፈር ያስፈለገው የምዕመናን ቁጥር እየበዛ በመምጣቱ ምክንያት ነበር፡፡ ጠያቂው ቁርኣን ራሱ በጽሑፍ መስፈር የጀመረው እስላማዊው ማሕበረሰብ ከተመሠረተ በኋላ እንደነበር የሚያውቁ አይመስሉም፡፡

  • ለመሆኑ ክርስቲያኖች “ብሉይ ኪዳን” የሚባለውን መጽሐፍ ከአይሁድ ሲቀበሉ (“እነርሱ መጽሐፉን ጠብቀው ስላቆዩ”) በብሉይ ኪዳን ስለ ሥላሴ፣ ስለ ኢየሱስ መሰቀልና ሌሎችም ክርስቲያኖች የሚያምኑባቸውን እንዲሁም “መጽሐፉን ጠብቀው ያቆዩት” አይሁዶች የማይቀበሉትንና ፈጽሞ ሀሰት በማለት የሚያስተባብሉትን እምነት እንዴት “መጽሐፉን ጠብቀው ካቆዩት” ልቀው ክርስትናን በትንቢቱ አረጋግጠው ተቀበሉ? ሃያ ሰባቱን መጻሕፍት የአምላክ ቃላት ናቸው ብሎ በምን መስፈርት ሊቀበሉ ቻሉ?

አይሁድ የኢየሱስን መሰቀል ይቀበላሉ፤ ቁርኣን እንኳ ይህንን ይመሰክራል (ሱራ 4፡57-158)፡፡ ጠያቂው ይህንን ስህተት መስራታቸው በግብታዊነት እንጂ በእርጋታና በማስተዋል እየጠየቁ እንዳልሆነ ያመለክታል፡፡

የአይሁድ አለማስተዋል የሥላሴ ትምህርት እና ስለ ክርስቶስ የተነገሩት ትንቢቶች በብሉይ ኪዳን ውስጥ አለመኖራቸውን ሊያረጋግጥ የሚችለው እንዴት ሆኖ ነው? አይሁዶች እነዚህን የመጽሐፋቸውን ክፍሎች አልተገነዘቡም ቢባል እንኳ የአይሁድን አለማስተዋል እንጂ የክርስትናን ስህተት መሆን አያሳይም፡፡  ሲጀመር አይሁድ ሁሉ እነዚህን ጉዳዮች አያውቁም ያለው ማን ነው? የመጀመርያዎቹ ክርስቲያኖች በሙሉ አይሁድ እንደነበሩ ለጠያቂው ማን በነገራቸው! አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አይሁድ ነበሩ፡፡ መቶ ሃያዎቹ በአንድ ቤት ሲጸልዩ የነበሩት ደቀ መዛሙርት አይሁድ ነበሩ፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በወቅቱ ታዋቂ በነበረው (እስከ ዛሬ ድረስ በአይሁድ ታሪክ ከተነሱት ሦስት ረበናት መካከል አንዱ በሆነው!) በገማልያል እግር ሥር ተቀምጦ የተማረና እርሱን ሊተካ ይችል የነበረ ታላቅ አይሁዳዊ ምሑር ነበር፡፡ በበዓለ ሃምሳ ቀን ጴጥሮስ ስለ ክርስቶስ የተነገሩትን ትንቢቶች ከብሉይ ኪዳን ጠቅሶ ያሳመናቸው ሦስት ሺህ ሰዎች አይሁድ ነበሩ፡፡ ሽባውን ከፈወሰው በኋላ ያመኑት አምስት ሺህዎቹ አይሁድ ነበሩ (የሐዋርያት ሥራ 2፡1-41፣ 4፡4)፡፡ የመጀመርያዎቹ ክርስቲያኖች በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ውስጥ ሲያመልኩ የነበር፡፡ በዚያን ዘመን ብዙዎቹ አብያተ ክርስቲያናት መነሻቸው የአይሁድ ምኩራቦች ነበር፡፡ ዛሬም በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ አይሁድ ክርስቲያኖች በዓለም ዙርያ ይገኛሉ፡፡ ኢየሱስ ራሱ አይሁዳዊ እንደነበርስ አሕመዲን ጀበል ያውቁ ይሆን? (ዮሐንስ 4፡22፣ ማቴዎስ 1፡1-17)፡፡ እስኪ የገዛ ጥያቄያቸውን መልሰን እናቅርብላቸውና መልስ ይኖራቸው እንደሆን እንይ፡፡ ሙስሊሞች ስለ ነቢያቸው ስለ ሙሐመድ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን ውስጥ እንደተተነበየ ይናገሩ የለምን? ታድያ አይሁዶችም ሆኑ የአዲስ ኪዳን ባለቤቶች የሆንነው እኛ ክርስቲያኖች ያላየነውን “ትንቢት” እንዴት ከኛ ልቀው ሊያዩት ቻሉ? በራሳቸው እምነት መሠረት እንኳ ሙግታቸው ውድቅ መሆኑ ግልፅ ነው!

  • ይህ ራሱ አቋም ከያዙ በኋላ መጻሕፍቱን እንደተቀበሉ አያሳይምን? ይህ ጉባኤ በ397 ዓ.ል መካሄዱ ራሱ ከዚያ በፊት “የትኞቹ መጻሕፍት የአምላክ ቃል ናቸው?” “የአዲስ ኪዳን አካል ናቸው?” የሚለው በውል አለመታወቁን አይገልጽምን?  የኒቂያ ጉባኤ ራሱ የተካሄደው በ325 ነው፡፡ ይህም ማለት ይህ መጽሐፍ በ397 የጸደቀበት የካርቴጅ ጉባኤ ሳይካሄድ 72 አመታት አስቀድሞ ነው፡፡ እምነቱ በ325 ተወሰነ፡፡ መጽሐፋ በ397 ተቀባይነት አገኘ! በ325 ከተወሰነው እምነት ጋር የሚሄደው (የሚስማማውን) ብቻ መርጠው እንደሆነስ?

ጠያቂው የክርስትና እምነት በኒቅያ ጉባኤ የተወሰነ በማስመሰል የተናገሩት በእጅጉ የተሳሳተ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ያለምንም ኦፊሴላዊ ጉባኤ ቀደም ሲል ተቀብላው የነበረው የሥላሴ ትምህርት አርዮስ በተሰኘ የኑፋቄ አስተማሪ ተግዳሮት ስለገጠመው ነበር ጉባኤ መጥራት ያስፈለገው፡፡ ጉባኤው ቀደም ሲል ቤተ ክርስቲያን የምታምነውን ትምህርት በሥነ መለኮታዊ ቃላት ይበልጥ በማብራራት መግለጫ አወጣ እንጂ አዲስ ነገር አልፈጠረም፡፡ በተጨማሪም የመጀመርያዎቹ ክርስቲያኖች አቋም ከያዙ በኋላ አልነበረም ቅዱሳት መጻሕፍታቸውን ያጸደቁት፡፡ ቀደም ሲል እንደገለፅነው ከኒቅያ ጉባኤ በፊት የነበሩት አባቶች ከ11 ቁጥሮች በተረፈ የአዲስ ኪዳንን ጥቅሶች በሙሉ በጽሑፎቻቸው ውስጥ ጠቅሰዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው መጻሕፍቱ ቀደም ሲል ተቀባይነት እንደነበራቸውና የኒቅያ ጉባኤም ሆነ ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ጉባኤዎች በእነዚህ ላይ ተመስርተው የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ እንዳስታወቁ ነው፡፡ (አርዮስና ሰባልዮስን የመሳሰሉት መናፍቃን እንኳ ክርክራቸውን ያቀረቡት አሁን በእጃችን በሚገኙት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ላይ በመመስረት ነበር!) በሐዋርያት እና በቀደሙት አማኞች ስም የተጻፉ የአፖክሪፋ መጻሕፍት ከሁለተኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ወዲህ መታየት መጀመራቸውንና በተባሉት ሰዎች የተጻፉ አለመሆናቸውን ለዘብተኛም ሆነ አጥባቂ የሥነ መለኮት ሊቃውንት ያለ ልዩነት በአንድ ድምፅ የሚስማሙበት እውነታ ነው፡፡

የቀኖና ምርጫ በአንድ ጀንበር የተከናወነ አልነበረም፡፡ ክርስትና እጅግ ሰፊ በነበረው በሮም ግዛት ውስጥ በመሰራጨቱ ምክንያትና ከበረታው ስደት የተነሳ አንዳንድ መጻሕፍት በሁሉም ስፍራዎች አይታወቁም ነበር፡፡ እነዚህ መጻሕፍት በመላው ክርስቲያን ማሕበረሰብ ዘንድ የተዳረሱት የስደቱ ዘመን ካበቃ በኋላ ሲሆን በጣም ርቀው ይገኙ የነበሩት የተሟላውን ቀኖና ለማግኘት ረጅም ጊዜ ወስዶባቸው ነበር፡፡ እያንዳንዱ የክርስቲያን ማሕበረሰብ መጻሕፍቱን ለመቀበል የየራሱን የማጣራት ሥራ ይሰራ ስለነበር አንዳንድ መጻሕፍት በሁሉም ክርስቲያኖች ዘንድ ወጥ በሆነ ሁኔታ ተቀባይነትን አላገኙም ነበር፡፡ የመጀመርያውን ቀኖና የጠቀሰው የቤተ ክርስቲያን ጸሐፌ ታሪክ የነበረው የቂሣርያው ኢዮስቢዮስ ሲሆን መጻሕፍቱን ለሦስት ይከፍላል፡፡ ሀ) ቀኖናዊነታቸው ከጥርጣሬ በፀዳ ሁኔታ ተቀባይነት ያገኙ 22 መጻሕፍት ሲሆኑ እነዚህም አራቱ ወንጌላት፣ የሐዋርያት ሥራ፣ የጳውሎስ መልዕክቶች (ዕብራውያንን ጨምሮ)፣ 1ዮሐንስ፣ 1ጴጥሮስ እና የዮሐንስ ራዕይ ናቸው፡፡ ለ) አምስቱ ከፍተኛ ተቀባይነት የነበራቸው ሲሆን ጥቂቶች ብቻ ይጠራጠሯቸው ነበር፤ እነዚህም ያዕቆብ፣ ይሁዳ፣ 2ጴጥሮስ፣ 2ዮሐንስ እና 3ዮሐንስ ናቸው፡፡ አምስቱ ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ ነበር እነርሱም የሔርማሱ እረኛ፣ የጳውሎስ ሥራ፣ የጴጥሮስ ራዕይ፣ የበርናባስ መልዕክት[24] እና ዲዳኬ ናቸው (እነዚህ በአዲስ ኪዳን ቀኖና ውስጥ አልተካተቱም)፡፡ ኢዮስቢዮስ የዮሐንስን ራዕይ በወቅቱ ገሚሶቹ ሲቀበሉት ገሚሶቹ ደግሞ ስለማይቀበሉት ምናልባት ከእነዚህ መደብ ሊጨመር እንደሚችል የጠቆመ ሲሆን እርሱ ግን  ሃያ ሰባቱንም እንደሚቀበል ገልጿል፡፡[25]

በምስራቅ ሃያሰባቱን የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በቀኖናዊነት ለመጀመርያ ጊዜ የጠቀሰው ቅዱስ አትናቴዎስ ሲሆን (367 ዓ.ም.) በምዕራብ ደግሞ በሂፖ ሬጊዩስ (አልጄርያ) (393 ዓ.ም.) እና በካርቴጅ (397 & 419 ዓ.ም.) እነዚሁ መጻሕፍት ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡ የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት የዮሐንስን ራዕይ የተቀበሉት ዘግይተው ሲሆን የሦርያ ቤተ ክርስቲያን 2ጴጥሮስ፣ 2ዮሐንስ፣ 3ዮሐንስ እና ይሁዳን ለመቀበል ከሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ዘግይታለች፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ቤተ ክርስቲያኒቱ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ርቃ የምትገኝ ስለነበረችና እነዚህ መጻሕፍት ስላልደረሷት ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን ቀኖናዊ መጻሕፍቷን እንድታስታውቅ ያደረጓት የተለያዩ ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ ዋነኛው ምክንያት ግን ኑፋቄያዊ ቡድኖች የየራሳቸውን የመጻሕፍት ስብስብ ማዘጋጀታቸው ነበር፤ (ለምሳሌ ያህል መርቂያን/ ማርሲዮን[26])፡፡[27]

ክርስቲያኖች የአዲስ ኪዳንን መጻሕፍት በቀኖናዊነት ለመቀበል የተለያዩ መስፈርቶችን በጥንቃቄ ተጠቅመዋል፡፡ የመጀመርያው መስፈርት “ሐዋርያዊ ሥልጣን” የሚል ነበር፡፡ ይህም አንድ መጽሐፍ ተቀባይነት ማግኘት ያለበት በሐዋርያትና ከእነርሱ ጋር የቀረበ ግንኙነት በነበራቸው ሰዎች የተጻፈ እንደሆነ ነው፡፡ ሉቃስና ማርቆስ ከሐዋርያት ጋር የቀረበ ግንኙነት ስለነበራቸው መጻሕፍታቸው ተቀባይነትን አግኝተዋል፡፡ ሁለተኛው መስፈርት ደግሞ የመጻሕፍቱ ከሌሎች የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ጋር መስማማት ሲሆን ሦስተኛው መስፈርት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለተከታታይ ዘመናት ተቀባይነትን አግኝተው ጥቅም ላይ መዋላቸው ነው፡፡ የቀደሙት ክርስቲያኖች ቀኖናዊ መጻሕፍትን ለመወሰን ጊዜ መውሰዳቸው ሐዋርያዊ ሥልጣን የሌላቸው መጻሕፍት ሾልከው እንዳይገቡ የነበራቸውን ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያሳይ ነው፡፡ እነዚህን መጻሕፍት በአንድ ጥራዝ የመሰብሰቡ ሂደት ጊዜ የወሰደ ቢሆንም ነገር ግን ተቀባይነት ያገኙት በአንድ ጀንበር አዋጅ ሳይሆን ከሐዋርያት ዘመን ተያይዞ በመጣ ሁኔታ ነበር፡፡ ጉባኤዎችም ሆኑ ግለሰቦች ቀኖናን አልፈጠሩም፡፡ ይልቁኑ እውነተኛ ቅዱሳት መጻሕፍት መሆናቸው በዘመናት ተፈትኖ ለተረጋገጡት መጻሕፍት ዕውቅናን ሰጡ እንጂ፡፡[28]