መጽሐፍ ቅዱስ በአርባ ሰዎች የተጻፉ መጻሕፍት ስብስብ አይደለምን?
አሕመዲን ጥያቄያቸውን ይቀጥላሉ፡-
7. የክርስቲያን ምሑራን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ጽፈዋል፡-“መጽሐፍ ቅዱስ ፤ የተቀደሰ ወይም የተለየ ማለት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የቅዱሳን መጻሕፍት መዝገብ ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን ናቸው፡፡ ብሉይ ኪዳን በ 1400-400 ከክርስቶስ በፊት በልዩ ልዩ ቦታዎች፣ አርባ በሚያህሉ ልዩ ልዩ ጸሐፊዎች እንደተጻፈ ይነገራል፡፡”(የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገብ ቃላት፤ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ መኅበር ገጽ 34)፡፡ አርባ ሰዎች የጻፉት የመጻሕፍቶች ስብስብ ከክፍለ ዘመናት በኋላ በአንድነት ተጠረዘ፡፡ እንዲያው የአንዱ መጽሐፍ ጸሐፊ “በመንፈስ ቅዱስ ተነድቶ” መጽሐፉን ቢገልጽ ይህ በሌሎች 39ኙ ሰዎች ተጽፈው በኋላ ላይ በአንድነት አብረው የተጠረዙትን ሁሉንም ሊወክል ይችላልን? መጽሐፍ ቅዱስ በአርባ ሰዎች የተጻፉ መጻሕፍት ስብስብ አይደለምን?
መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ሰዎች፣ በተለያዩ ዘመናት፣ በተለያዩ ቦታዎች የተጻፈ መጽሐፍ ሆኖ ሳለ ማዕከላዊ መልዕክቱ አንድ መሆኑ መለኮታዊነቱን ከሚያሳዩ ነገሮች መካከል አንዱ ነው፡፡ ከአንድ ግለሰብ ምስክርነት ይልቅ የአርባ ሰዎች ምስክርነት ይታመናል፡፡ አንድ ግለሰብ እርስ በርሱ የተስማማ አንድ መጽሐፍ ማዘጋጀት ይችላል፡፡ ነገር ግን የማይተዋወቁ፣ በክፍለ ዘመናት የተራራቁና በቦታ የማይገናኙ 40 ሰዎች ወጥ መልእክት ያለው መጽሐፍ ማዘጋጀት በእጅጉ ከባድ ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ግን በአንዱ የእግዚአብሔር መንፈስ ተመርተው ስለጻፉ ይህንን ማድረግ ተችሏቸዋል፡፡ እኛ ክርስቲያኖች ሁሉም ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው እንደጻፉ ስለምናምን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን መጻሕፍት ሁሉ ያለ ምንም ልዩነት በእኩል ሁኔታ እንቀበላለን፡፡ ጠያቂው አንድ መጽሐፍ እውነተኛ መሆን የሚችለው በአንድ ግለሰብ የተጻፈ እንደሆነ ብቻ ነው የሚሉ ይመስላሉ፡፡ እስላማዊ “አመክንዮ” በእጅጉ አስገራሚ ነው፡፡
- ለአብነት “የማቴዎስ ወንጌልን የጻፈው ቀረጥ ሰብሳቢው ማቴዎስ ነው” ተብሎ ይታመናል፡፡ ነገር ግን በቀላሉ በእርሱ እንዳልተጻፈ መረዳት ይቻላል፡፡ በማቴዎስ 9፥9 ላይ “ኢየሱስ ከዚያ ቦታ ተነስቶ ሲሄዱ ሳለ ማቴዎስ የተባለውን ቀራጭ በቀረጥ መቀበያ ስፍራ ተቀምጦ አየውና “ተከተለኝ” አለው፡፡ ማቴዎስም ተነስቶ ተከተለው” ይላል፡፡ ማቴዎስ ይህን ቢጽፍ “ተቀምጦ አየው”፡፡፡፡ ሳይሆን “ተቀምጬ አየኝ”፣ “ተነስቶ ተከተለው” ሳይሆን “ተነስቼ ተከተልኩት” ወዘተ. እያለ ነበር የሚጽፈው፡፡ እንዴት ራሱን ሦስተኛ ወገን አድርጎ ያቀርባል?
ስለ ራስ በሦስተኛ ወገን መጻፍ በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በጥንት ሥነ-ጽሑፎች ውስጥ የተለመደ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን አጻጻፍ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በቁርኣንም ውስጥ እናገኛለን፡፡ አላህ በቁርኣን ውስጥ ኁልቁ መሳፍርት በሌላቸው ቦታዎች ላይ ራሱን እንደ ሦስተኛ ወገን ይጠቅሳል፡፡ አንዳንድ ጊዜ አንደኛና ሦስተኛ ተውላጠ ሥሞችን እያቀያየረ ከመናገሩ የተነሳ ቁርኣንን ለመጀመርያ ጊዜ የሚያነብ ሰው ከአንድ በላይ ማንነት እንዳለው እስኪመስለው ድረስ ግራ ሊጋባ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ያህል እስኪ የሚከተሉትን ጥቅሶች እንመልከት፡-
“ያ ባሪያውን ከተከበረው መስጊድ ወደዚያ ዙሪያውን ወደ ባረክነው ወደ ሩቁ መስጊድ በሌሊት ውስጥ ያስኼደው (ጌታ) ጥራት ይገባው፡፡ ከተዓምራቶቻችን ልናሳየው (አስኼድነው)፡፡ እነሆ እርሱ (አላህ) ሰሚው ተመልካቺው ነው፡፡” (ሱራ 17፡1)
“ጌታህም እርሱ በእርግጥ አሸናፊ አዛኝ ነው፡፡ ጌታህም ሙሳን «ወደ በደለኞቹ ሕዝቦች ኺድ» በማለት በጠራው ጊዜ (አስታውስ)፡፡” (ሱራ 26፡8-9)
“አላህ በነሱ ይሳለቅባቸዋል፤ በጥመታቸውም ውስጥ የሚዋልሉ ሲኾኑ ያዘገያቸዋል፡፡” (ሱራ 2፡14)
“እርሱ ያ በምድር ያለውን ሁሉ ለእናንተ የፈጠረ ነው፡፡ ከዚያም ወደ ሰማይ አሰበ፤ ሰባት ሰማያትም አደረጋቸው፡፡ እርሱም በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነው፡፡” (ሱራ 2፡28)
አንድ ሰው ራሱን በሦስተኛ ወገን ማመልከቱ የመልእክቱ ተናጋሪ እርሱ አለመሆኑን የሚያረጋግጥ ከሆነ በተመሳሳይ በነዚህ የቁርኣን ጥቅሶች ውስጥ ተናጋሪው አላህ ከሆነ ለምን በሦስተኛ ወገን ራሱን ይጠቅሳል?