የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንዶች አሉ የተባሉ ሰዎች እስካሁን አሉ?

 


11. በማቴዎስ 16፡28 ላይ “እውነት እላችኋለሁ፣ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንዶች አሉ” ይላል፡፡ ነገር ግን እንኳን ኢየሱስ ተመልሶ ሲመጣ ሊያዩ ይቅርና ያኔ ከነበሩት ውስጥ አንዱም ሰው ያን ክፍለ ዘመን የተሻገረ የለም፡፡ በዚያው ክፍለ ዘመን ሞትን ያልቀመሰ የለም፡፡ ሁሉም ያኔ ጥንት ነው! ከ1900 ዓመታት በፊት ነው ሁሉም ያለቁት፡፡ ታድያ ጥቅሱ ስህተት ነውን?

ጥቅሱ ስህተት አይደለም፡፡ ስህተቱ ያለው በጠያቂው መረዳት ውስጥ ነው፡፡ ማቴዎስ 16፡28 የክርስቶስን መለኮታዊ ክብር መገለጥ የሚያመለክት እንጂ ዳግመኛ ምፅኣቱን የሚያመለክት አይደለም፡፡ ይህ ቃል ከስድስት ቀናት በኋላ እንደተፈጸመ በማቴዎስ 17፡1-3 ላይ እንዲህ ተጽፎ እናነባለን፡-

“ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው፡፡ ፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ፡፡ እነሆም፥ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው…”

2ጴጥሮስ 1፡16-18 ላይ የተጻፈው ቃልም ይህንኑ የሚረጋግጥ ነው፡-

“የእርሱን ግርማ አይተን እንጂ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መምጣት አስታወቅናችሁ፡፡ ከገናናው ክብር በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚል ያ ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ተቀብሎአልና፤ እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን፡፡”

በተጨማሪም ይህ ትንቢት በበዓለ ሃምሳ እለት የክርስቶስ መንግሥት በምድር ላይ በሚታይ ሁኔታ መመሥረቱን የተመለከተ ሊሆን ይችላል (የሐዋርያት ሥራ 2)፡፡