ጳውሎስ “እኔም ደግሞ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ያለ ይመስለኛል”ብሏል፡፡ እምነት በይመስለኛል ያስኬዳልን?

 


13. የኢየሱስ ተከታዮች ጠላት የነበረው ሳውል (በኋላ ጳውሎስ የተሰኘው) አማኞን አሳዷል፡፡ እንዲታሰሩ ተስማምቷል፡፡ በኋላ ላይ ጳውሎስ “ኢየሱስ ተገልጦልኛል ሐዋርያት ነኝ” ብሎ ስለ ራሱ ተናገረ፡፡ ተቀበሉት፡፡ ግና በ1ኛ ቆሮንቶስ 8፡40 ላይ “እኔም ደግሞ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ያለ ይመስለኛል ፡፡”ብሏል፡፡ እምነት በይመስለኛል ያስኬዳልን?

ሐዋርያው ለምን ይህንን እንዳለ ከመግለጻችን በፊት እስኪ ስለ ጥሪው ያለውን እርግጠኛነት የሚያሳዩ ጥቅሶችን እንመልከት፡-

“ማንም ነቢይ ወይም መንፈሳዊ የሆነ ቢመስለው ይህች የጻፍሁላችሁ የጌታ ትእዛዝ እንደ ሆነች ይወቅ” (1ቆሮንቶስ 14፡37)፡፡

“በኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታንም ባነሣው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ የሆነ እንጂ ከሰዎች ወይም በሰው ያልሆነ ጳውሎስ ከእኔም ጋር ያሉት ወንድሞች ሁሉ፥ ወደ ገላትያ አብያተ ክርስቲያናት፤” (ገላቲያ 1፡1)

“ወንድሞች ሆይ፥ በእኔ የተሰበከ ወንጌል እንደ ሰው እንዳይደለ አስታውቃችኋለሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል እንጂ እኔ ከሰው አልተቀበልሁትም አልተማርሁትምም” (ገላቲያ 1፡12)፡፡

“ለእናንተ ስለ ተሰጠኝ ስለ እግዚአብሔር ጸጋ መጋቢነት በእርግጥ ሰምታችኋል፤ አስቀድሜ በአጭሩ እንደ ጻፍሁ፥ ይህን ምሥጢር በመግለጥ አስታወቀኝ” (ኤፌሶን 3፡2-3)፡፡

“እምነታችሁም በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ እንዳይሆን፥ ቃሌም ስብከቴም መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ ነበረ እንጂ፥ በሚያባብል በጥበብ ቃል አልነበረም” (1ቆሮንቶስ 2፡4-5)፡፡

“እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና” (2ጢሞቴዎስ 1፡7)

“ደግሞም ያተመን የመንፈሱንም መያዣ በልባችን የሰጠን እርሱ ነው” (2ቆሮንቶስ 1፡22)

በሐዋርያው ጳውሎስ ጸሎት አማካይነት ሰዎች የመንፈስ ቅዱስን ስጦታዎች ይቀበሉ ነበር (የሐዋርያት ሥራ 19፡1-7)፡፡ የእርሱ ጽሑፎች ከሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት እኩል እንደሆኑ ሐዋርያው ጴጥሮስ መስክሯል (2ጴጥሮስ 3፡15-16)፡፡ እውነተኛነቱ በድንቅና በተዓምራት ተረጋግጧል፡- “እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ የሚያስገርም ተአምራት ያደርግ ነበር፤ ስለዚህም ከአካሉ ጨርቅ ወይም ልብስ ወደ ድውዮች ይወስዱ ነበር፥ ደዌያቸውም ይለቃቸው ነበር ክፉዎች መናፍስትም ይወጡ ነበር፡፡” (የሐዋርያት ሥራ 19፡11-12፣ በተጨማሪም 14፡8-11፣ 16፡16-18፣ 20፡8-12)፡፡

ታዲያ በዚህ ቦታ “ይመስለኛል” በማለት ጥርጣሬን በሚያሳይ ቃል ስለምን ተናገረ? ሐዋርያው ጳውሎስ ብዙ ጊዜ በምፀታዊ ንግግር ለተቃዋሚዎቹ መልስ የመስጠት ልማድ ነበረው፡፡ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የእግዚአብሔር መንፈስ እንዳለባቸውና ነቢያት እንደሆኑ በትዕቢት የሚናገሩ፣ ደግሞም አለን በሚሉት መንፈሳዊ ዕውቀት የሚታበዩ ወገኖች ነበሩ፡፡ ሐዋርያው ምፀታዊ በሆነ መንገድ ለእነርሱ ምላሽ ለመስጠት እንጂ የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ላይ እንዳለ ጥርጣሬ ስላለው አይደለም (8፡1-3፣ 14፡37)፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስን ለመንቀፍ እንዲህ የተጣደፉት አሕመዲን የጥንት ሙስሊሞች ሐዋርያው ጳውሎስ እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይ መሆኑን መመስከራቸውን ቢሰሙ ምን ይሉ ይሆን? መቼስ ለገዛ መጻሕፍታቸው እንግዳ ስለሆኑ እኛው እናሳያቸው እንጂ፡፡

ኢብን ኢስሐቅ የተሰኘው ቀዳሚውን የሙሐመድ ግለ ታሪክ የከተበ ሙስሊም እንዲህ ሲል ጽፏል፡-

“ዒሳ የመርያም ልጅ የላካቸው ደቀ መዛሙርትና ከእነርሱ በኋላ የመጡት በአገሪቱ ውስጥ የነበሩት እነዚህ ነበሩ፡- ደቀ መዝሙሩ ጴጥሮስና ከእርሱ ጋር ደግሞ ጳውሎስ ወደ ሮም ተላኩ፡፡ (ጳውሎስ ከተከታዮቹ መካከል ሲሆን ደቀ መዝሙር አልነበረም፡፡) እንድርያስና ማቴዎስ ወደ በላዔ-ሰብዕ ምድር፤ ቶማስ በምስራቅ ወደሚገኘው ወደ ባቤል ምድር፤ ፊልጶስ ወደ ካርቴጅና ወደ አፍሪካ፤ ዮሐንስ የዋሻዎቹ ወጣቶች ምድር ወደሆነው ወደ ኤፌሶን…”[34]

የኢብን ኢስሐቅ ጽሑፍ ሳሂህ አል-ቡኻሪ እና ሳሂህ ሙስሊምን ከመሳሰሉት ሐዲሳት እንኳ የሚቀድም የሙሐመድ ግለ ታሪክ ነው፡፡ በቅንፍ ውስጥ የተቀመጠው ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የእርሱ ተከታይ እንዳልነበረ በትክክል የሚገልፅ በመሆኑ ስህተት የለበትም፡፡

የእስልምና ጀማሪ የሆኑት ሙሐመድ ሐዋርያው ጳውሎስ የጻፈውን ከጠቀሱ በኋላ የአላህ ቃል መሆኑን መመስከራቸውንስ አሕመዲን ጀበል ያውቁ ይሆን?

“ነገር ግን፦ ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ተብሎ እንደተጻፈ፥ እንዲህ እንናገራለን” (1ቆሮንቶስ 2፡9)፡፡

ከላይ የተጠቀሰው ሐዋርያው ጳውሎስ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የተጠቀሱትን የእግዚአብሔር ተስፋዎች በራሱ አባባል ጨምቆ ያስቀመጠበት ዓረፍተነገር ሲሆን ከእርሱ በሚቀድም በየትኛውም ምንጭ ውስጥ በዚህ መልኩ ተጽፎ አይገኝም፡፡ ሙሐመድ እንዲህ ጠቅሰውታል፡-

“አቡ ሁራይራ እንዳስተላለፈው ነቢዩ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አላህ እንዲህ አለ ‹እኔ ለታማኝ ባርያዎቼ ዓይን ያላየችውን፣ ጆሮ ያልሰማውን የሰው ልብ ሊያስበው የማይችለውን (አስደናቂ ነገሮች)› አዘጋጅቻለሁ፡፡››”[35]

አሕመዲን ጀበልን የመሳሰሉት ሙስሊም ጸሐፊያን በጌታ ተጠርቶ እስከ ሞት ድረስ በመታመን ሰማዕት የሆነውን ቅዱስ ሐዋርያ ለማብጠልጠል አንደበታቸውን ከመክፈታቸው በፊት የገዛ ምንጮቻቸውን ማጥናት ነበረባቸው፡፡