መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ ቅዱስ ከተጻፈ ለምን በቀደምት ቤተ ክርስቲያን በርካታ የቀኖና ጭቅጭቅ ጉባኤ ተደርገ?
21. እውን ክርስቲያኖች እንደሚሉት እያንዳንዱ መጽሐፍት በመንፈስ ቅዱስ መጻፉን ቢያረጋግጡ ኖሮ የትኞቹን መቀበል እንዳለባቸው ለመወሰን ለምን በቀደምት ቤተ ክርስቲያን በርካታ ጭቅጭቅ ጉባኤ ተደርገ? ለምንስ ሰው ሰራሽ መስፈርቱ ለአምላክ ቃል ተቀመጠ? ለምንስ በድምፅ ብልጫ ፀደቀ? ለምን ዛሬም ድርስ የልዩነት ምንጭ ሆነ?
አብያተ ክርስቲያናት ልዩነቶችን ያንጸባረቁት በአዲስ ኪዳን ላይ ሳይሆን በብሉይ ኪዳን ላይ ነው፡፡ የአፖክሪፋ መጻሕፍትን እንደ ቃለ እግዚአብሔር የማይቀበሉትም ቢሆኑ መንፈሳዊ እሴት እንዳሏቸው መጻሕፍት ስለሚቆጥሯቸው ይጠቀሙባቸዋል፡፡ ሙስሊም ወገኖች እንኳ “ሐዲስ ቁድሲ” በመባል የሚታወቁት ሐዲሳት እንደ ቁርኣን ሁሉ የአላህ ንግግሮች በመሆን አለመሆናቸው ላይ ልዩነቶች አሏቸው፡፡ አንዳንዶች ከቁርኣን እኩል የሚቀበሏቸው ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ እንደ ሌሎቹ ሐዲሳት ይቆጥሯቸዋል፡፡
በአዲስ ኪዳን ዙርያ በአብያተ ክርስቲያናት መካከል ምንም ዓነት ልዩነት የለም፡፡ እነዚህንም መጻሕፍት ለማፅደቅ ምንም አይነት ጭቅጭቅ አልተደረገም፡፡ ጥቅም ላይ የዋሉት መስፈርቶችም ቢሆኑ መንፈሳዊ መስፈርቶች እንጂ ሰው ሰራሽ አይደሉም፡፡ በድምፅ ብልጫ የጸደቀ አንድም የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ የለም፡፡ በአዲስ ኪዳን ቀኖና ላይ ምንም ዓይነት ልዩነት የለም፡፡ ጠያቂው ለተናገሯቸው ነገሮች ምንም ዓይነት ማስረጃ ሊጠቅሱ አልቻሉም፡፡