ለምን ዛሬም ድረስ በኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ እና ፕሮቴስታንት የተለያየ መጽሐፍ ቅዱስ አገልግሎት ላይ ዋለ?

 


22. እውን መጽሐፎቹ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፉና ይህንንም የሚያረጋግጡ ከሆነ ለምን ዛሬም ድረስ በኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ እና ፕሮቴስታንት የተለያየ መጽሐፍ ቅዱስ አገልግሎት ላይ ዋለ? ለምንስ ነው ዛሬም ድረስ ስምምነት ላይ መድረስ ያልተቻለው?

ይህ ጥያቄ ሰፋ ያለ መልስ የሚሻ በመሆኑ እኔ ከማምንበት የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትና አቋም አኳያ እንደሚከተለው መልስ እሰጣለሁ፡፡

ቀኖና የሚለው ቃል “ካኖን” ከሚል የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጓሜውም “የመለክያ ብትር” ወይም “ደንብ” ማለት ነው፡፡ ይህ ቃል እስትንፋሰ-መለኮት መሆናቸው የሚታመንባቸውን የቅዱሳት መጻሕፍት ዝርዝር ያመለክታል፡፡ ቀኖናን በተመለከተ በሰፊው የሚናፈሱ የተሳሳቱ አመለካከቶች ከመኖራቸው አንፃር እነዚህን ውዥንብሮች ለማጥራት አንድ መሰራታዊ የሆነ እውነት መጠቀስ ይኖርበታል፡፡ ይህም ቤተ ክርስቲያን የቀኖና ውጤት እንጂ የቀኖና እናት አለመሆኗ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን መሠረት የሐዋርያት እና የነቢያት ትምህርት በመሆኑ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ይህኛው ቀኖና ነው ያኛው ደግሞ ቀኖና አይደለም በማለት ሲለዩ ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችበትን መሠረት በማጤን እንጂ ለቤተ ክርስቲያን መሠረት እያጣሉላት አልነበረም ማለት ነው፡፡ ቀደም ሲል እንደተባለው ቅዱሳን አባቶች የነቢያትና የሐዋርት ምንጭ ያላቸውንና የቤተ ክርስቲያን መሠረት የሆኑትን መጻሕፍት በመለየት አስታወቁ እንጂ አዲስ ነገር አልፈጠሩም፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን የቀኖና ልጅ እንጂ የቀኖና እናት አይደለችም፡፡ ቤተ ክርስቲያን የቀኖና አገልጋይ እንጂ የቀኖና የበላይ አይደለችም፡፡ ቤተ ክርስቲያን የቀኖና ምስክር እንጂ የቀኖና ወሳኝ አይደለችም፡፡ የቀኖና ወሳኙ እግዚአብሔር እራሱ ነው፡፡ እግዚአብሔር በመንፈሱ ምሪት በተጻፉት ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የራሱን “አሻራ” በማስቀመጥ ቀኖናን ወስኗል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ድርሻም ይህ “አሻራ” ያረፈባቸውን መጻሕፍት መለየት ነው፡፡[37]

የመጽሐፍ ቅዱስን ቀኖና በተመለከተ በተለያዩ የክርስትና ቤተ እምነቶች መካከል ልዩነቶች ይታያሉ፡፡ የወንጌላውን አብያተ ክርስቲያናት ቀኖና 66 መጻሕፍትን የያዘ ሲሆን የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን 73 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ 81 መጻሕፍትን የያዙ ናቸው፡፡ በስድሳ ስድስቱ መጻሕፍት ዙርያ በነዚህ የክርስትና ቤተ እማነቶች መካከል ስምምነት ያለ ሲሆን ልዩነቱ የተፈጠረው አፖክሪፋ በመባል በሚታወቁት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዙርያ ነው፡፡ አፖክሪፋ ማለት የተሰወረ ወይም አጠራጣሪ ማለት ሲሆን እነዚህን መጻሕፍት እንደ እስትንፋሰ መለኮት የሚቀበሏቸው ወገኖች ዲዩትሮካኖኒካል (ሁለተኛ ቀኖና) በማለት መጥራትን ይመርጣሉ፡፡ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት እነዚህን መጻሕፍት እንደማይጠቅሙ ወይንም ደግሞ በውስጣቸው ምንም እውነት እንዳልያዙ አይቆጥሯቸውም፡፡ ይልቁኑ በነዚህ መጻሕፍት ውስጥ ብዙ ጠቃሚ እውነቶች እንዳሉና ከሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት ጎን ለጎን ለተጨማሪ እውቀት መነበብ እንሚገባቸው ያምናሉ ነገር ግን በሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት ደረጃ ላይ አያስቀምጧቸውም፡፡ ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ምክንያቶችን ይጠቅሳሉ፡፡ ከነዚህ መካከል አራቱ የሚከተሉት ናቸው፡-

  1. የአፖክሪፋ መጻሕፍት ነቢያት በነበሩበት ዘመን ሳይሆን በዝምታ ዘመን የተጻፉ ናቸው፡፡ በነቢዩ ሚልኪያስ እና በኢየሱስ ክርስቶስ መካከል የነበረው የ400 ዓመታት ጊዜ “የዝምታ ዘመን” በመባል ይታወቃል፡፡ በነዝያ ዘመናት የተከናወኑ ልናውቃቸው የሚገቡ ታሪኮች ቢኖሩም ነገር ግን እግዚአብሔር የሚናገራቸው ነቢያት ስላልነበሩ በወቅቱ የተጻፉት ጽሑፎች ሁሉ የሰው ስራዎች እንጂ እስትንፋሰ መለኮት ሊሆኑ አይችሉም፡፡
  2. እነዚህ መጻሕፍት ወደ ክርስቲያን ቀኖና የተጨመሩት በቀደሙት የቤተ ክርስቲያን አባቶች ዘመን ሳይሆን በመካከለኛው ዘመን ነበር፡፡ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አባቶች እነዚህን መጻሕፍት የጠቀሷቸው ቢሆንም መንፈሳዊ እሴት እንዳሏቸው ጠቃሚ መጻሕፍት እንጂ እንደ ስልጣናዊ ቃለ እግዚአብሔር አልነበረም፡፡ በ382 ዓ.ም. በሮም የተደረገውን የመሳሰሉ የአፖክሪፋ መጻሕፍት ቀኖናዊ መሆናቸውን የሚናገሩ ጉባኤዎች አካባቢያዊና የተወሰኑ ሰዎች ድምዳሜ እንጂ ቤተ ክርስቲያንን የሚወክሉ አይደሉም፡፡ እንዲያውም ኦሪጎን፣ የኢየሩሳሌሙ ቄርሎስ፣ አትናቴዎስ እና ጀሮምን የመሳሰሉ ታላላቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች አፖክሪፋን ተቃውመዋል፡፡[38] መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ላቲን ቋንቋ የተረጎሙት ቅዱስ ጀሮም እነዚህን መጻሕፍት አፖክሪፋ (የተሰወሩ ወይንም አጠራጣሪ) የሚል ስያሜ በመስጠት ከስድሳ ስድስቱ መጻሕፍት በመለየት ተርጉመዋቸዋል፡፡ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እነዚህን መጻሕፍት በቀኖናነት ያጸደቀችው የተሓድሶ (Reformation) እንቅስቃሴ አንዳንድ አስተምህሮዎችዋን መገዳደር በጀመረበት ዘመን (በ1546 ዓ.ም.) “የትረንት ጉባኤ” በመባል በሚታወቅ የቤተክርስቲያኒቱ ጉባኤ ላይ ሲሆን ለነዚህ አስተምህሮዎች ድጋፍ ሊሰጡ የሚችሉ ሐሳቦች በአፖክሪፋ ውስጥ እንደሚገኙ ስላመነች ቤተ ክርስቲያኒቱን ለሁለት የከፈለውን እንቅስቃሴ ለመቋቋም እንዲጠቅሟት በማለም ነበር፡፡ ነገር ግን በዚያን ዘመንም ቢሆን ካርዲናል ካጄታንን የመሳሰሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት የሪፎርሜሽን እንቅስቃሴን ይቃወሙ የነበሩ ቢሆኑም ነገር ግን የአፖክሪፋ መጻሕፍትን ወደ ቀኖና መጨመር ተቃውመው እንደነበር ታሪክ ይነግረናል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንም ብትሆን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እነዚህን መጻሕፍት በሰላሳ ዘጠኙ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት እና በአዲስ ኪዳን መካከል የተለየ ቦታ በመስጠት ዲዩትሮካኖኒካል (ሁለተኛ የቀኖና መጻሕፍት) የሚል ስያሜ በመስጠት እንዲታተሙ ታደርግ ነበር፡፡ ነገር ግን በ2000 ዓ.ም. በታተመው የሰማንያ አሐዱ እትም ላይ እነዚህን የአፖክሪፋ መጻሕፍት ከሌሎች የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ጋር በመቀላቀል እንዲታተሙ ተደርጓል፡፡
  3. ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት እና የግሪክ ኦርቶዶክስን የመሳሰሉት አብያተ ክርስቲያናት እነዚህን መጽሐፍት እንደ ቃለ እግዚአብሔር የማይቀበሉበት ሌላው ምክንያት ደግሞ እነዚህ መጻሕፍት በአይሁድ ቀኖና ውስጥ የማይገኙ መሆናቸው ነው፡፡ በ90 ዓ.ም. ዮሐናን ቤን ዛካይ በተባለ ረቢ መሪነት በጃምኒያ በተደረገ የአይሁድ ሊቃውንት ጉባኤ ላይ በአይሁድ ታሪክ ውስጥ በቀኖናነት ተቀባይነት እንደነበራቸው ተረጋግጠው እስትንፋሰ መለኮት መሆናቸው ዕውቅና የተሰጣቸው የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሰላሳ ዘጠኙ ብቻ ነበሩ፡፡ የጉባኤው አላማ ቀኖናን ማጽደቅ ሳይሆን የትኞቹ መጻሕፍት በቀኖናነት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ እንደነበሩ ለይቶ ዕውቅና መስጠት እንደ ነበር ልብ ሊባል ይገባል፡፡ የአይሁድ መምህር የነበረው የእስክንድርያው ፋይሎ (20 ዓ.ዓ. – 40 ዓ.ም.) ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚቻልበት ሁኔታ ከሁሉም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የጠቀሰ ሲሆን ከአፖክሪፋ ግን አንድም ጊዜ አልጠቀሰም፡፡ የአይሁድ ጸሐፌ ታሪክ የነበረው ጆሲፈስ ፍላቪየስ (ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን) (30 ዓ.ም. – 100 ዓ.ም.) የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት 22 ብቻ መሆናቸውን በመጥቀስ የአፖክሪፋን መጻሕፍ ውድቅ አድርጓቸዋል፡፡ አይሁድ አንዳንድ መጻሕፍትን እንደ አንድ መጽሐፍ ስለሚቆጥሯቸው እንጂ እነዚህ በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ቆጠራ መሠረት 39 ከሆኑት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የተለዩ አይደሉም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሮሜ 3፡1-2 ላይ እንደጻፈው እግዚአብሔር ብሉይ ኪዳንን በአደራ የሰጠው ለአይሁድ ሕዝብ ነው፡-

“እንግዲህ የአይሁዳዊ ብልጫው ምንድር ነው? ወይስ የመገረዝ ጥቅሙ ምንድር ነው? በሁሉ ነገር ብዙ ነው፡፡ አስቀድሞ የእግዚአብሔር ቃላት አደራ ተሰጡአቸው፡፡”

ስለዚህ አይሁድ የትኞቹ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ከእግዚአብሔር እንደሆኑና እንዳልሆኑ ለይተው ያውቃሉ፡፡ የአይሁድ ሕዝብ ቅዱሳት መጻሕፍትን በታላቅ ፍርሃት እና በታላቅ አክብሮት በጥንቃቄ ይዘው እንደቆዩ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ የጥንቃቄያቸውን ብዛት ለመረዳት እና ለማድነቅ እስኪ የሚከተሉትን እውነታዎች ከግምት ውስጥ አግቡ፡

  • የጽሑፍ ሥራው ከመጀመሩ በፊት በእድሜ የሁሉ ታላቅ የሆነ ረቢ ተነስቶ በመቆም አንድ ፊደል እንኳ መቀነስ ወይንም ደግሞ መጨመር ለጥፋት እንደሚዳርጋቸው ጸሐፍቱን ያስጠነቅቃል፡፡
  • ጸሐፍቱ ሥራቸውን እየሰሩ ሳሉ ንጉሥ እንኳ ቢገባ ስህተት ላለመስራት የጀመሩትን ገፅ እስኪጨርሱ ድረስ ቀና ብለው ማናገር እንደ ሌለባቸው ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸዋል፡፡
  • ብሉይ ኪዳን የሚጻፍበት ብራና ከንፁህ እንስሳት ቆዳ በአይሁዳዊ እጅ ብቻ መዘጋጀት አለበት፡፡
  • እያንዳንዱ ወርድ ከ 48 በታች እና ከ 60 በላይ መስመሮች ሊኖሩት አይገባም፡፡
  • ቀለሙ ጥቁር ብቻ መሆን አለበት፣ በተለየ ሁኔታም ይዘጋጃል፡፡
  • ከትውስታ የሚጻፍ ምንም ዓይነት ቃል ወይንም ፊደል መኖር የለበትም፡፡ ጸሐፊው ተኣማኒ የሆነ ኮፒ ከፊት ለፊቱ ማስቀመጥ አለበት፣ ከመጻፉ በፊትም ከፍ ባለ ድምፅ በትክክል ሊያነበው ይገባል፡፡
  • ጸሐፊው ከመጻፉ በፊት አክብሮት በተሞላበት ሁኔታ መጻፍያውን መወልወል አለበት፡፡
  • ጸሐፊው ያሕዌ የሚለውን የእግዚአብሔርን ስም ከመጻፉ በፊት መላ ሰውነቱን መታጠብ አለበት፡፡
  • ጸሐፊው ያሕዌ የሚለውን የእግዚአብሔርን ስም ለመጻፍ አዲስ ብዕር ይጠቀማል፡፡ ያሕዌ የሚለውን ስም የጻፈበትን ብዕር ሌላ ቃል ለመጻፍ አይጠቀምበትም፡፡
  • በአንድ ገፅ ላይ የሚፈጠር አንድ ስህተት ገፁን በሙሉ ያበላሸዋል፡፡ በአንድ ገፅ ላይ ሦስት ስህተቶች ከተገኙ ብራናው በሙሉ ከጥቅም ውጪ ይሆናል፡፡
  • እያንዳንዱ ቃል እና እያንዳንዱ ፊደል ተቆጥሮ ተመዝግቧል፡፡[39]

ስለዚህ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት የብሉይ ኪዳንን ቀኖና በተመለከተ እግዚአብሔር ታማኝ አድርጎ ቆጥሮ ቃሉን በአደራ ከሰጣቸውና እንዲህ ባለ ጥንቃቄና አክብሮት የእግዚአብሔርን ቃል ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲያስተላልፉ ከኖሩት ሕዝቦች ጋር ይስማማሉ፡፡

  1. ጌታችን ኢየሱስ ዕውቅናን የሰጠው ለአይሁድ ቀኖና ብቻ ነበር፡፡ በጌታ ዘመን ብሉይ ኪዳን ሕግ፣ ነቢያት እና መዝሙራት በመባል ለሦስት ተከፍሎ ነበር (ሉቃስ 24፡44)፡፡ በነዚህ ሦስቱ ክፍሎች ውስጥ የአፖክሪፋ መጻሕፍት አልነበሩም፡፡ በተጨማሪም ጌታችን ኢየሱስ “ከአቤል ደም እስከ ዘካርያስ ደም” በማለት ብሉይ ኪዳን ከአቤል ጀምሮ እስከ ዘካርያስ ዘመን ድረስ የሚገኘውን የታሪክ ዘመን እንደሚሸፍን አመላክቷል (ማቴ 23፡35፣ ሉቃ 11፡51)፡፡ ይህም ከዘፍጥረት ጀምሮ እስከ መጨረሻዎቹ ነቢያት ድረስ የሚገኘው ዘመን ነው፡፡ ነቢዩ ዘካርያስ እና ነቢዩ ሚልኪያስ በአንድ ዘመን የኖሩ ሲሆኑ ከእነርሱ በኋላ እስከ ክርስቶስ ዘመን ድረስ የነበረው ዘመን የዝምታ ዘመን በመባል ይታወቃል፡፡ በይሁዳ መልዕክት ቁጥር 14-15 ላይ ከአፖክሪፋ መጻሕፍት መካከል አንዱ የሆነው መጽሐፈ ሄኖክ መጠቀሱ መጽሐፉ ትምህርት ሰጪ የሆነን መልዕክት በውስጡ የያዘ መሆኑን የሚያመለክት እንጂ መጽሐፉ ሙሉ በሙሉ እውነት መሆኑን የሚያመለክት አይደለም፡፡ የጌታ ሐዋርያት ለተደራሲያኖቻቸው ትምህርት ሊሰጡ የሚችሉ የግሪክ ጽሑፎችንና ሌሎች የአይሁድ መጻሕፍትን እንኳ ሲጠቅሱ እንመለከታለን፡፡ ይህ ጽሑፎቹን እስትንፋሰ መለኮት አያደርጋቸውም፡፡