ኦርጂናል መጽሐፍ ቅዱስ እንደሌለ ያውቃሉን?
አሕመዲን ጥያቄዎቻቸውን ይቀጥላሉ፡-
23. ኦርጂናል መጽሐፍ ቅዱስ እንደሌለ ያውቃሉን? ይህንንማ ለነገሩ ክርስቲያኖችም አያስተባብሉም፡፡ ቢኖርማ ለምን ከበርካታ መጽሐፍት መካከል ለመለየት የድምፅ ብልጫ ይደረግ ነበር? ክፍፍል፣ ጭቅጭቅ፣ ልዩነት ይከሰት ነበርን?
ኦሪጅናል ቁርኣን እንደሌለ ያውቃሉን? የመጀመርያዎቹ የቁርኣን ጽሑፎችስ ተሰብስበው መቃጠላቸውን ያውቃሉን? ይህንንማ ለነገሩ ሙስሊሞችም አያስተባብሉም፡፡ ታድያ የኦሪጅናል ቁርኣን አለመኖር ቁርኣንን እንዲጠራጠሩ ካላደረጎት መጽሐፍ ቅዱስን ስለምን ይጠራጠራሉ? ክርስቲያኖች የመጀመርያዎቹን ጽሑፎች እንደ ሙስሊሞች ሰብስበው አላቃጠሉም፡፡ ከማተሚያ ማሽን ዘመን በፊት የተጻፉትን ወደ 1.5 ሚሊዮን የሚሆኑ የአዲስ ኪዳን ገፆችን ጨምሮ ከኦሪጅናሎቹ ላይ የተገለበጡ ኮፒዎች ዛሬ በእጃችን ይገኛሉ፡፡ ሙስሊሞች ግን የመጀመርያዎቹ ቁርአኖች ሆነ ተብለው እንዲወድሙ ስለተደረጉ አሁን ያለው ቁርኣን ከኦሪጅናሉ ጋር እንደሚመሳሰል ለማመን የሚያስችላቸው መሠረት የላቸውም፡፡ ቁርኣንን በአንድ ጥራዝ መሰብሰብ፣ የትኞቹ ሱራዎች መካተት እንዳለባቸው እና ኦሪጅናሎቹን ማቃጠልን በተመለከተ በቀደሙት ሙስሊሞች መካከል ብዙ ጭቅጭቅ፣ ንትርክ፣ አለመቀባበልና ልዩነት ተከስቶ ነበር፡፡ ነገር ግን በወቅቱ ሥልጣን ላይ የነበረው ገዢ ኸሊፋ ኡስማን የራሱን ፍላጎት በኃይል አስፈፅሟል፡፡ (ወደ በኋላ ላይ በሰፊው እንመለከታለን፡፡)