ከበርካታ መጽሐፍቶች መካከል ዛሬ የሚገኘውን ሲመርጡ የአምላክን ቃል በምን ሚዛን ለዩት?
24. ከበርካታ መጽሐፍቶች መካከል ዛሬ የሚገኘውን ሲመርጡ የአምላክን ቃል በምን ሚዛን ለዩት? እውነትና ሐሰት የሚለውን አምላካዊ አስተምህሮት የሚረጋገጠው ያ የሚመረጠው መጽሐፍ ሆኖ ሳለ ለምን ወደ ድምፅ ብልጫ ተገባ?
ኡስታዝ አሕመዲን ቅጥፈት ይብቃዎት! ድምፅ ብልጫ የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ ቀደም ሲል እንደተገለጸው የቀኖና ውሳኔ ረጅም ዘመናትን የፈጀ ሂደት እንጂ በአንድ ጀምበር የድምፅ ብልጫ የተወሰነ አልነበረም፡፡ የመጀመርያዋ ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው በሐዋርያት ትምህርትና በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ላይ ነበር፡፡ የሐዋርያት ትውፊትና የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ስለነበሯት ሚዛን አልባ አልነበረችም፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለመቀበል ጥቅም ላይ ውለው የነበሩት መመዘኛዎች ሐዋርያዊ ሥልጣን፣ ከሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት ጋር ያላቸው ተግባቦት እና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበራቸው ታሪካዊ ተቀባይነት የሚሉትን የመሳሰሉት መንፈሳዊና ምክንያታዊ መስፈርቶች ስለነበሩ ተመሳስለው የተጻፉ ሌሎች የፈጠራ ጽሑፎች ሾልከው ሊገቡ አልቻሉም፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን ሀሰተኛ ነቢያት እንደነበሩት ሁሉ በአዲስ ኪዳን ዘመንም ስላሉ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረጓ ትክክል ነበር (2ጴጥሮስ 2፡1)፡፡