ክርስቲያኖች ስለእምነታቸው አቋም ይዘው ነው መጽሐፍቶችን የመረጡት ወይስ መጽሐፍቶችን ከመረመሩ በኋላ ነው አቋም የያዙት?

 


25. ክርስቲያኖች ስለእምነታቸው አቋም ይዘው ነው መጽሐፍቶችን የመረጡት ወይስ መጽሐፍቶችን ከመረመሩ በኋላ ነው አቋም የያዙት?

ይህ ጥያቄ አሁንም የቤተ ክርስቲያንን አመሰራረት ካለማወቅ የመነጨ ነው፡፡ መጀመርያ ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው በሐዋርያት ትምህርት እና በብሉይ ኪዳናት መጻሕፍት ላይ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን እየሰፋች ስትመጣ ሐዋርያት ትምህርቶቻቸውን በጽሑፍ ማስፈር ስለነበረባቸው ያንን አደረጉ፡፡ እነዚህ መጻሕፍት በክርስቲያኖች ዘንድ ይታወቁ ስለነበር በአጠቃላይ መግባባት ተቀባይነት አግኝተው የአስተምህሮ ምንጭ በመሆን ያገለግሉ ነበር፡፡ ኋላ ላይ የኑፋቄ አስተማሪዎች የራሳቸውን ቀኖና ማዘጋጀት ሲጀምሩ ቤተ ክርስቲያን አቋሟን ግልፅ ለማድረግ ኦፊሴላዊ የሆኑ ጉባኤዎችን በመጥራት ቀኖናዋን አረጋገጠች፡፡ የቤተ ክርስቲያን ትምህርቶች ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋር ሳይፋቱ አብረው የመጡ ቢሆኑም በሃይማኖት መግለጫ መልክ እንዲቀመጡ የተደረጉት ኑፋቄያዊ አስተምህሮዎች በፈጠሯቸው ተግዳሮቶች ምክንያት ነበር፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን አቋም ይዛ ቅዱሳት መጻሕፍትን አልመረጠችም፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትን መርምራ እምነቷን ያስታወቀችበት ሁኔታ ቢኖርም ነገር ግን እምነቷና ቅዱሳት መጻሕፍት የተፋቱበት ጊዜ አልነበረም፡፡