ሙሴ “እኔ ከሞትሁ በኋላ ካዘዝኋችሁም መንገድ ዘወር እንደምትሉ አውቃለሁ” ካለ እንዴት መጻሕፍቶቹን አይሁድ ጠብቀው አቆዩ ይባላል?
28. ዘዳግም 31፡24-29 “ሙሴ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የዚህን ቃል በመጽሐፍ ጽፎ እንዳበቃ የእግዚአብሔርን የኪዳን ታቦት የሚሸከሙ ሌዋውያንን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፣… የቱን ያህል አመፀኞችና አንገተ ደንዳኖች እንደሆናችሁ አውቃለሁና፡፡ እኔ በህይወት ከእናንተ ጋር እያለሁ እንደዚህ ካመፃችሁ፣ ከሞትሁ በኋላማ የቱን ያህል ልታምፁ! …እኔ ከሞትሁ በኋላ ፈፅማችሁ እንደምትረክሱ፣ ካዘዝኋችሁም መንገድ ዘወር እንደምትሉ አውቃለሁና” ይላል፡፡ ታዲያ ሙሴ ይህን ተናግሮ ሳለ እንዴት መጻሕፍቶቹን አይሁድ ጠብቀው አቆዩ ይባላል?
ይህንንስ ቃል ቢሆን ጠብቆ ያቆው ማነው? አይሁዶች አይደሉምን? መጽሐፉን ለውጠውት ቢሆን ኖሮ እንዲህ የሚገስጻቸውንና ክፉዎች መሆናቸውን የሚገልፀውን ክፍል ስለምን ሳይለውጡት ቀሩ? ክፍሉ እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር ቃል አለመታዘዛቸውን እንጂ ቃሉን ስለመለወጣቸው የሚናገር አይደለም፡፡ የቃሉ ጠባቂ ራሱ እግዚአብሔር ነው! እስራኤላውያን ለቃሉ ባይታዘዙም ነገር ግን እንዲለውጡት እግዚአብሔር አልፈቀደም፡፡ ደግሞም በየዘመናቱ እግዚአብሔርን የሚፈሩና የሚያገለግሉት ታማኞች ከሕዝቡ መካከል ጠፍተው አያውቁም፡፡ እስከ ባቢሎን ምርኮ ዘመን ድረስ ነቢያት የነበሩ ሲሆን ከባቢሎን ምርኮ መልስ አይሁድ ጠንካራ የሃይማኖት ማሕበረሰቦች ከመሆናቸው የተነሳ ለቅዱሳት መጻሕፍት ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ያደርጉ ነበር፡፡ አይሁድ በብዙ ክፉ ነገሮች ሊከሰሱ ይችላሉ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ቃል በመለወጥ ሊከሰሱ አይችሉም!
በማስከተል አሕመዲን የአፖክሪፋ መጻሕፍት ሴቶችን በተመለከተ ከሚናገሯቸው ነገሮች በመነሳት ጥያቄዎችን ይሰነዝራሉ፡፡ እኛ የአፖክሪፋ መጻሕፍት ቃለ እግዚአብሔር እንደሆኑ ስለማናምን መልስ ለመስጠት ጊዜ ማጥፋት አያስፈልገንም፡፡ ነገር ግን ጠያቂው ያነሷቸውን ጥያቄዎች እየመለስን የገዛ ሃይማኖታቸው ሴቶችን በተመለከተ ምን እንደሚል በማሳየትና እውነተኛው የእግዚአብሔር ቃል ምን እንደሚል በማስነበብ ርዕሱን እናነፃፅራለን፡፡ ጽሑፉን ለማንበብ እዚህ ጋ ጠቅ ያድርጉ፡፡