ኢየሱስን ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚሉ ሰዎች መንግስተ ሰማያት ካልገቡ ክርስቲያኖች ለምን ኢየሱስ ጌታ ነው ትላላችሁ?
28. ኢየሱስን «ጌታ» ይሉታልን? ይህ ከሆነ መንግሥተ ሰማያት መግባት አይፈልጉምማለት ነው፡፡ ለምን ቢሉ በማቴዎስ ወንጌል 7:20-23 ላይ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፡፡ «በሰማያት ያለውን የአባቱን ፍቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! የሚለኝ ሁሉ መንግስተ ሰማያት የሚገባ አይደለም፡፡ በዚያን ቀን ብዙዎቹ፡- ጌታ ሆይ!ጌታ ሆይ! በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህስ አጋንንትንአላወጣንምን? በስምህ ብዙ ተአምራት –አላደረግንምን? ይሉኛል፡፡ በዚያን ጊዜም ከቶ አላወቅኋችሁም እናንተ ዓመፀኞች ከእኔ ራቁ ብዬ አመሠክርባቸዋለሁ፡፡» ይላል፡፡ ኢየሱስን «ጌታ» የሚለው ማነው? ሙስሊሞች ወይስ ክርስቲያኖች? «አላውቅኋችሁም፣ እመሰክርባቸኋለሁ» ያለውስ ማንን ነው? ክርስቲያኖችን የትኞቹን ክርስቲያኖች? የሚል ጥያቄ ከተነሳ ደግሞ «ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ» ብሎ ኢየሱስ ገልጾታል፤ እና መንግስተ ሰማያት መግባት አይፈልጉም? ለምን ሌላ ትርጉም በመስጠት ራስዎን ያታልላሉ? ኢየሱስን ጌታ ከማለት ውጭ የአምላክን ተእዛዛት መጠበቅና የአምላክን ፈቃድ መተግበር ትተዋል፡፡ ታዲያ እንዴት ተዘናጉ?
ይህ ጥያቄ የአሕመዲን መጽሐፍ ቅዱስን እንደልባቸው የመተርጎም ድፍረት ጣርያ ነው፡፡ በመሠረቱ ጌታ መሆኑን የተናገረው ራሱ ኢየሱስ ነው፡-
“እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ እንዲሁ ነኝና መልካም ትላላችሁ፡፡ እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፥ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል” (ዮሐንስ 13፡13-14)፡፡
“እንዲሁም የሰው ልጅ ለሰንበት እንኳ ጌታዋ ነው አላቸው” (ማርቆስ 2፡28)፡፡ እግዚአብሔር ለራሱ ክብር እና አምልኮ በፈጠራት ቀን ላይ ጌታ መሆን የሚችል ከእርሱ በስተቀር ማነው?
የኢየሱስ ጌትነት መታወጅ የጀመረው በብሉይ ኪዳን ነው፡፡ ዳዊት “ጌታ” ብሎ ጠርቶታል (ማቴዎስ 22፡41-46 ከመዝሙር 110፡1 ጋር ያነፃፅሩ)፡፡ ነቢዩ ሚልክያስ ጌታ ብሎታል (ሚልክያስ 3፡1)፡፡ ገና በማህፀን ሳለ ኤልሳቤጥ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታ “ጌታዬ” ብላዋለች (ሉቃስ 1፡43)፣ መላእክት ጌትነቱን መስክረዋል (ሉቃስ 2፡11)፣ እግዚአብሔር አብ ራሱ ጌታ መሆኑን መስክሯል (ዕብራውያን 1፡10)፡፡ እኔ ባደረኩት ቆጠራ መሠረት በአዲስ ኪዳን ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከ250 ጊዜያት በላይ “ጌታ” ተብሎ ተጠርቷል፡፡ ሰዎች ጌታ ሲሉት አንድም ቀን ተቃውሞ አሰምቶ አያውቅም፡፡ ነገር ግን አሕመዲን የቋንቋ ችግር ያለባቸው ይመስል ኢየሱስ “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፍቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግስተ ሰማያት የሚገባ አይደለም” በማለት የተናገረውን አጣመው በመተርጎም ኢየሱስ “ጌታ አትበሉኝ” ያለ ለማስመሰል ሞክረዋል፡፡ ኢየሱስ እያለ ያለው በተግባር አማኝ ሆናችሁ ካልተገኛችሁ “ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ” ስላላችሁ ብቻ አትገቡም ነው፡፡ ጠያቂው የአገራቸው ቋንቋ ካልገባቸው በእንግሊዘኛ እንዲያነቡት ከታች አስቀምጠናል፡፡[4] በኢየሱስ ስም ትንቢት መናገርም ሆነ ተዓምራትን ማድረግ ለመንግሥተ ሰማያት አያበቃም፡፡ በኢየሱስ ስም ተዓምር ማድረግ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ዋስትና ከሆነ ጌታውን የሸጠው ይሁዳም ሊገባ ነው፡፡ ለመንግሥተ ሰማያት የሚያበቃው የአብን ፈቃድ በመፈፀም እስከ መጨረሻው ድረስ እውነተኛ አማኝ ሆኖ መገኘት ነው፡፡ መፈፀም ያለበት ቀዳሚው የአብ ፈቃድ ደግሞ እርሱ በላከው በአንድ ልጁ ማመን ነው (ዮሐንስ 6፡40)፡፡
አሕመዲን ህሊናቸውን በመጨቆን የእግዚአብሔርን ክቡር ቃል ለማጣመም እስከዚህ ጥግ ድረስ መሄዳቸው በእውነቱ ከሆነ እጅግ አሳፋሪ ነው፡፡ እውነተኛ ክርስቲያኖች አንድ ሰው በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ የሙስሊሞችን መጽሐፍ ሲያጣምም ቢመለከቱ ከመገሰፅ ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ተመሳሳይ ነገር በክርስቲያኖች መጽሐፍ ላይ ሲፈፀም ህሊና ያላቸው ሙስሊሞች ሁሉ ሊቃወሙ ይገባል፡፡ ወዳጆች ሆይ ስለ ነፍስ ጉዳይ ነው እያወራን ያለነው፡፡ አንዳችን የሌላችንን ቅዱስ መጽሐፍ እያጣመምን እንዴት ነው ልንተማመንና አንዳችን ሌላችንን የእውነት አምላክ ወደሆነው ፈጣሪያችን ልንመራ የምንችለው? ፈጣሪ በሀሰት እና በማጭበርበር ደስ ይሰኛልን?